የወያኔ አገዛዝ ሃሰተኛ ክስ የመሠረተባቸው የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ጋዘጤኞች ፍርድ ቤት ተብዬው የድራማ ችሎት ፊት ቀረቡ

ላለፉት 20 አመታት በአገራችንና በህዝባችን ላይ በፈጸመው ወንጀል ተረብሾ ህዝብ በማሸበር ላይ የሚገኘው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በሆነው አንዷለም አራጌ የክስ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል የከሰሳቸው 24 የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት፣ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ አክቲቪስቶች የክስ ቻርጅ በመለስ ዜናዊ ቀጭን ት ዕዛዝ በሚዘወረው የከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ፊት በትናንትናው ዕለት ረቡዕ ጠዋት ቀርቦ እንደተነበበ የዜና ምንጮቻችን ከስፍራው ከላኩልን ሪፖርት ለማወቅ ተችሎአል።

እንደዜና ምንጫችን ዘገባ ረቡዕ ጠዋቱ 3፡40 ሰዓት ላይ በካቴና ታስረው ወደ ችሎት የቀረቡት በሀገር ውስጥ የሚገኙት ከተራ ቁጥር 1 እስከ ተራ ቁጥር 8 ያሉት ተከሳሾች ብቻ እንደሆኑና ሌሎቹ ከሀገር ውጪ ይኖራሉ የተባሉት በጋዜጣ ተጠርተው እንዳልቀረቡ ከሳሽ አቃቤ ህግ አስረድቶአል፡፡

በችሎቱ ላይ የቀረቡት ተከሳሾች በሙሉ ሰውነታቸው የመጎሳቆልና የመክሳት ምልክት የታየባቸው ቢሆንም የፈጠራ ክስ ቻርጁ ሲነበብላቸው ሁሉም የፌዝ ፈገግታ በማሳየት በክሱ ላይ ተቃውሟቸውንና በፍርድ ሥርዓቱ ላይ እምነት የሌላቸው መሆናቸውን አሳይተዋል ተብለዋል።

በወያኔ ጌቶቻቸው የታዘዙትን ፍርድ ከመስጠታቸው በፊት በአገሪቱ ህግ ያለ ለማስመሰል ድራማ ማሳየትን ሙያ ያደርጉ የፍርድ ቤቱ ዳኞች የተከሳሾችን የግል ሁኔታ በጠየቁበት ወቅት አንደኛ ተከሳሽ የሆነው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አንዷለም አራጌ ሥራው የሙሉ ሰዓት ፖለቲከኛ ብሎ መመለሱን ፣ 5ተኛው ተከሳሽ ክንፈሚካኤል ደበበ በረደድ (አበበ ቀሲቶ) ደግሞ በበኩሉ “ለሰው ልጆች ፍትህና ሠላም መስፈን የምንቀሳቀስ ሠላማዊ ታጋይ ነኝ” በማለት ራሱን ማስተዋወቁ ተዘግቦአል።

ወያኔ የሱዳን ጸጥታ ሰራተኞችን በገንዘብ ሃይል ገዝቶ ከተሰደደበትና በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ሥር በስደተኝነት ተመዝግቦ ከሚኖርበት ሱዳን አገር በጉልበት ተይዞ መጥቶ እስር ላይ የሚገኘው 8ተኛ ተከሳሽ የሆነው አንዷለም አያሌው ገላው ደግሞ “ለጊዜው ሥራ የለኝም፣ ከምኖርበት ካርቱም የስደተኛ ጣቢያ ነው ተይዤ የመጣሁት፤ ስለዚህ አድራሻ የለኝም፣ ቀደም ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላ ሳለሁ የተሰጠኝን ቤት ባለቤቴንና ሁለት ልጆቼን አስወጥተው በአሁኑ ሰዓት የት እንዳሉ እንኳ አላውቅም” በማለት መመለሱን ለማወቅ ተችሎአል።

አቃቤ ሕግ ተብዬው የወያኔ ቃል አቀባይ ቀደም ብሎ ባቀረበው የክስ ቻርጅ ላይ እርማት አለኝ በማለት ፍርድ ቤቱን በመጠየቁ በተሰጠው እድል በ24ቱም ተከሳሾች ላይ አቅርቦት የነበረውን 1ኛ ክሥ፣ ከ1ኛ ተከሳሽ እስከ 22ተኛ ተራ ቁጥር ባሉት ተከሳሽ ላይ ብቻ ይጽናልኛ በተራቁጥር 23ና 24 የተጠቀሱት ከክሱ ውጪ ይሆኑልኝ በማለቱ የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅና ማኔጂንግ ኤዲተር መስፍን ነጋሽና ዐብይ ተክለማርያም ከአንደኛው ክስ ውጪ እንዲሆኑ ተደርጎአል፡፡

ዐቃቤ ህግ ባቀረበው የክስ ቻርጅ ላይ በሁለተኛው ክሥ ከተከሳሽ ተራ ቁጥር 1 እስከ 18 ድረስ የሚለውን በ21ኛ እና በ22ተኛ ተራ ቁጥር ተከሳሾችም ላይ እንዲካተት ያደረገ ሲሆን፣ በ2ተኛው ክሥ 2ተኛ መስመር ላይ ከ2 እስከ 6ተኛ ተራ ቁጥር የሚለው ላይ 7ተኛ ተራ ቁጥርም በክሱ ላይ እንዲካተት አድርጓል፡፡

የተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው በክሱ አቀራረብ ላይ ተቃውሟቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በተከሳሾች ላይ የቀረበው ክስ፣ በሽብርተኝነት፣ በሀገር መክዳትና የስለላ ተግባር ሲሆን፣ ይህም ከእድሜ ልክ እስከ ሞት ፍርድ ድረስ የሚያስቀጣ ቢሆንም ዐቃቤ ህግ ባቀረባቸው የክስ ቻርጅ ላይ ይህን የሚያመለክት የህግ መርሆዎችን የማያሟላ ተራ አሉባልታ እና ተከሳሾቹ በህገ መንግሥቱ መሠረት በህግ ተቋቁሞ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላት እና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በመጠቀም የሚሰራ የጋዜጠኝነትና የፖለቲካ ትንታኔ ሥራዎች የሚያከናውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በህጋዊ ሥራዎቻቸውና በግል መብታቸው ነው የተከሰሱት በማለት አብራርተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ተብየው የወያኔ ካድሬዎች ስብስብ አሸባሪ ብሎ በቅርቡ ከወሰነው የግንቦት 7 አመራር አባላት ጋር አንድ ላይ መከሰሳቸው ዐቃቤ ህግ ሆን ብሎ በተከሳሾቹ ላይ ጉዳት ለማድረስና ጫና ለመፍጠር ነው ሲሉ ጠበቆች አክለዋል፡፡

ዐቃቤ ህግ ባቀረበው የክሥ ቻርጅ ላይ ከአሸባሪ ጋር በመገናኘት፣ ድጋፍ በመስጠት፣ ሀገር በመክዳት፣ በመሰለል የሚሉ ቃሎች አሉ ያሉት የተከላካይ ጠበቆች ነገር ግን ወንጀሉ የተፈጸመበትን ጊዜና ቦታ አላስቀመጠም በማለት ሰፊ ህጋዊ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ህግን ክስና የተከላካይ ጠበቆችን መቃወሚያ ካደመጠ በኋላ በክሥ ቻርጁ ላይ ብይን ለመስጠት ለዛሬ ሃሙስ ህዳር 14 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን በቀጠሮው መሠረተ በዛሬው ዕለት ጉዳዩ በድጋሜ ታይቶአል።

በዚሁ መሠረት በዛሬው ህዳር 14 ቀን 2004 ዓም ከቀኑ በ9 ሰአት በዋለው ችሎት ላይ ሁሉም እስረኞች እጆቻቸው በካቴና ታስሮ ፍርድ ቤቱ ፊት መቅረባቸው ተዘግባኦል።

በዛሬው ዕለት ተካሂዶ የዋለውን የፍርድ ቤት ድራማ ለመታዘብ በመቶዎች የሚቆጠሩ የ እስረኞች ቤተሰቦች ፤ የትግል አጋሮችና አድናቂዎች የተገኙ ቢሆንም ፖሊሶች ግን 20 ሰዎችን ብቻ እንደሚያስገቡ በመግለጣቸው አብዛኛው ህዝብ ሁኔታውን በውጭ ሆኖ ለመከታተል ተገዶአል።

ከመለስ ዜናዊ የተሰጠውን ብይን አስቀድሞ የተገነዘበውና ሂደቱን ህጋዊ ለማስመሰል ብቻ ደፋ ቀና እያለ ያለው የይስሙላው ፍርድ ቤት በዛሬው ውሎው ከአንደኛውና ከአራተኛው ክሶች በስተቀር ሌሎች ክሶች መሰረተ ቢስ ናቸው፣ አንደኛውና አራተኛውም ክሶች ቢሆኑ መሻሻል የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ አቃቢ ህግ ክሱን አሻሽሎ ለህዳር 20 ቀን ይዞ እንዲቀርብ በማለት ወስኖ እንዳሰናበታቸው ለማወቅ ተችሎአል። በተራ ቁጥር አንድ እና አራት ላይ የሰፈሩት ወንጀሎች ሽብር ለመፈጸም ማቀድና ከኤርትራ መንግስት ጋር አብሮ መስራት የሚሉት ናቸው።

የፖለቲካ እስረኞቹን ክስ ለመከታተል ከተለያዩ ኢምባሲዎች የመጡ ዲፕሎማቶችና የውጭ ጋዜጠኞች በብዛት በቦታው መገኘታቸውንም ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል።

መለስ ዜናዊ አስተማማኝ የሆኑ መረጃዎችን በእጃችን ሳንይዝ አንድም ሰው አላሰርንም በማለት እንደአሻንጉሊት ለሚመለከታቸው ፓርላማ ተብዬ ስብስብ በቅርቡ ተናግሮ እንደነበር ቢታውስም እስካሁን በታዬው የፍርድ ቤት ሄደት ይህ ነው ሊባል የሚችል ተጨባጭነት ያለው አንድም ማስረጃ ለማቅረብ አለመቻሉ ድህረ ምርጫ 97 ከታየው የፖለቲካ ክስ የባሰ የሚያሳፍር ድራማ እየተሰራ መሆኑን የራሱ ካድሬዎች እየተናገሩ ነው።