የኔሰው ገብሬ: ነፃነትን በእሳት የተቀዳጀ ሰማዕት!!!

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በመምህር የኔሰው ገብሬ አስደንጋጭ መስዕዋትነት ምክንያት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ይገልፃል። የመምህር የኔሰው ገብሬ መሰዋት ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹና ለዳውሮ ዞን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ መሪር ሃዘን ነው።

በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት በዳውሮ ዞን የሚገኘው የዋካ ከተማና አካባቢው ህዝብ በአስተዳደር በደል፣ በኑሮ ውድነትና በወረዳ አከላለል መነሻነት ከወር በላይ የዘለቀ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ ነው። የዞኑ ካድሬዎች “በእያንዳንዳችሁ በር ላይ ድንኳን ይተከላል፤ ሞት በአየር ላይ ይዘራባችኋል!” እያሉ ቢያስፈራሩም ህዝቡ ግን “የመብት ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ወደኋላ አንልም” ብሎዓል።

ዋካ በመለስ ዜናዊ ሠራዊት ተወራለች። የዋካ አዛውንቶችና ወጣቶች ታስረዋል፤ እየታሰሩም ነው። ተሰቃይተዋል፤ እየተሰቃዩም ነው። ሆኖም ግን ትግላቸውን ቀጥለዋል። ከእነዚህ ወጣት ታጋዮችና የበደል ሰለባዎች አንዱ ትውልዱ ጅማ የሆነው መምህር የኔሰው ገብሬ ነበር።

መምህር የኔሰው ገብሬ ከሥራ ተባሯል፤ ታስሯል፤ ተንገላቷል። ታስሮ ከብዙ ስቃይ በኋላ ሲፈታም ስለታሰረበትም ሆነ ስለተፈታበት ሁኔታ የሚነግረው አላገኘም። የሰው ልጅ በዘፈቀደ እየታሰረ የሚሰቃይበት ሥርዓት ተወግዶ፤ ፍትህ የሰፈነባትን ኢትዮጵያ ለማየት ጓጉቷል።

ኅዳር 1 ቀን 2004 ዓ.ም. መምህር የኔሰው፣ በእርሱ ላይ እንደደረሰው ሁሉ ያለአግባብ የታሰሩ ወዳጆቹ ወደ ሚቀርቡበት የወረዳው ፍርድ ቤት አመራ። ወዳጆቹ ይፈታሉ ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር። ሆኖም ዳኛው የታዘዙትን ተጨማሪ ቀጠሮ የመስጠት ውሳኔ አስተላለፉ። የየኔሰው ትዕግሥት ገደቡ አለፈ። ከፍርድ ቤቱ እንደወጣ ወደ አካባቢው አስተዳደር ቢሮ ሄደ። ባለስልጣኖቹ ስብሰባ ላይ ናቸው። የአስተደደሩ ቢሮ በረንዳ ላይ “በደል በዛ!!! ፍትህ በሌለበት አገር መኖር አልችም!!! በዚህ ሁኔታ መኖር ኑሮ አይባልም!!! ግፍና መከራ እያየሁ መኖር አልችልም!!!” እያለ ቤንዚን በራሱ ላይ አርከፍክፎ እሳት ለኮሰ።

መምህር የኔሰው በቂ የህክምና እርዳታ ቀርቶ ጠያቂ እንኳን በወጉ አጠገቡ እንዳይደርስ በፓሊስ እንደተከለከለ ኅዳር 4 ቀን 2004 ዓ.ም. በተርጫ ሆስፒታል ውስጥ ህይወቱ አለፈች።

ኅዳር 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ኢትዮጵያም አንድ በፍትህ እጦት የተከፋና የተቆጣ ልጇን አጣች።

በመምህር የኔሰው ቀብር ላይ መገኘት የሚያሳስር ወንጀል መሆኑ በመለስ ዜናዊ ካድሬዎች ቢነገርም፣ በርካታ ህዝብ የመጨረሻውን አሸኛኘነት አደረገለት። ኅዳር 5 ቀን የመምህር የኔሰው ገብሬ አስከሬን መቃብር ውስጥ አርፎ “ግብዓተ-መሬት” ቢፈፀምም፣ ታሪኩ ግን ከመቃብር በላይ ውሎ በመላው ዓለም እየናኘ ነው።

የመምህር የኔሰው አሟሟት የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ አስከፊነት መገለጫ ሆኗል። መምህር የኔሰው የፍትህ ዋጋ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ማሳያ ሆኗል። መምህር የኔሰው በህይወት እያለም፤ እየሞተም፤ ከሞተም በኋላ መምህር ሆኖ አስተምሮናል። መምህር የኔሰው፣ “እየኖርን ነን” እያልን እራሳችንን እያታለልን ላለነው ሁሉ ከፍ ያለ የሞራል እዳ ጥሎብን አልፏል።

በ1997 ምርጫ ማግሥት ባለቤታቸውን ከአጋዚ ወታደሮች ለማስጣል በመሞከራቸው በመትረየስ እሩምታ የተገደሉት የወ/ሮ እቴነሽ ይማም ልጅ “እናቴን ቅንጅት ነው የገደላት ብለሽ መስክሪ” ተብላ እንደነበር ሁላችንም እናስታውሳለን። እንዲሁም የትምህርት ቤት ዩኒፎርማቸውን እንደለበሱ፤ የደብተርና እስክርቢቶ ቦርሳዎቻቸውን እንዳነገቡ፣ የተደፉት እነ ህፃን ነቢዩ ሳይቀሩ “ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ ነው የተገደሉት” መባሉ መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም።

ዛሬም የመለስ ዜናዊ የውሸት ፋብሪካዎች መምህር የኔሰው ገብሬ የአዕምሮ ህመምተኛ ነበር እያሉ ማስወራት ጀምረዋል። የዋካ ነዋሪዎች ግን በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ “ለፍትህ መቆም እብድ ያሰኛል?” እያሉ እየሞገቷቸው ነው። በአንፃሩም መምህር የኔሰው የእውቀት ጥማት የነበረው፤ ከፍተኛ የማንበብ ፍቅር የነበረው ወጣት እንደነበር ወዳጆቹ ሁሉ ይመሰክራሉ።

ለመሆኑ የመምህር የኔሰው መስዋዕትነት ለትግላችን ያለው አንደምታ ምንድነው? መምህር የኔሰው በመስዋዕትነቱ ያስተላለፈው መልዕክት ምንድነው?

የመምህር የኔሰው መልዕክት ግልጽ ነው። ፍትህና ነፃነት በሌሉበት፤ መብት በተረገጠበት ሁኔታ መኖር ኑሮ አይባልም። የባርነት ኑሮ፤ ኑሮ አይደለም። እውነቱን ለመናገር ባለፉት ሃያ ዓመታት ኢትዮጵያዊያን እየኖርን ያለነው “ኑሮ” ኑሮ አይደለም። ዓይኖቻችን እያዩ፤ ጆሮዎቻችን እየሰሙ አንድ ጠባብ፣ ዘረኛና ትዕቢተኛ የሆነ ትንሽ ቡድን፣ መላዋን ኢትዮጵያ ጠፍንጎ አስሮ እያለባትም፤ እያዋረዳትም ነው። አገራችን በአንድ ቡድን ስትመዘበር መከላከል አቅቶን በድናችንን እየኖርን ነው። ባርነት ይለመዳል። እኛም ለሃያ ዓመታት ባርነትን ተለማምደናል። መምህር የኔሰው የለኮሳት እሳት ካላነቃችን መቼም ላንነቃ እንችላለን።

የመምህር የኔሰው መስዕዋትነት ለሁላችንም የእግር እሳትና የልብ ህመም ነው። እሳቱ ይፍጀን!!! ህመሙ ይመመን!!! እናም የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝን “በቃህ!!!” የማለት ድፍረት ይኑረን::

በቃን!!! እኛም እንደየኔሰው ፍትህና ነፃነት በሌሉባት አገር ውስጥ መኖር አንፈልግም!!! መለስ ዜናዊንና ዘረኛ ቡድኑን ከሥልጣን አስወግደን የነፃነት አየር መተንፈስ እንሻለን፤ እናደርገዋለንም!!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!