የወያኔ ኢፍትሃዊ አገዛዝ ያንገሸገሸው መምህር የኔሰው ገብሬ እንደ ቱንዚያዊው ሞሃመድ ቡአዚዚ ራሱን በእሳት አጋይቶ ገደለ
አረመኔው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና በደል ህሊናው ሊሸከመው ከሚችለው በላይ መሆኑን በመግልጽ የኔሰው ገብሬ የተባለ የደቡብ ተወላጅ እራሱን በእሳት አጋይቶ መግደሉን የግንቦት7 ድምጽ ሬዲዮን ጨምሮ ሌሎች በርካታ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የኔሰው ገብሬ በመባል የሚታወቀው መምህር በዳውሮ ዞን በተርጫ ከተማ ለበርካታ አመታት ነዋሪ ሲሆን የወያኔው አገዛዝ ሆድ አደር የዞንና የወረዳ ምክር ቤት ባለስልጣናት ተብየዎች በአንድነት ተሰባስበው በቅርቡ በዋካ የተፈጠረውን ችግር በሚወያዩበት ወቅት፣ በራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ ራሱን እያቃጠለ ወደ ስብሰባ አዳራሹ መግባቱ ታውቁአል።
አረመኔው የወያኔ አገዛዝ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቱኒዚያ ሙሃመድ ቡአዚዝ በራሱ ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ለቱኒዚያዊያን ብሎም ለሰሜን አፍሪቃዊያን የነጻነት ጮራን ከፈነጠቀ ወዲህ ተመሳሳይ ህዝባዊ አመጽ ኢትዮጵያ ውስጥ መነሳቱ አይቀሬ መሆኑን በመገንዘቡ በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች በህዝብ ላይ ማለቂያ የሌለው በደልን እየፈጸመ እንደሆነ በስፋትና በተደጋጋሚ ሲዘገብ መቆየቱ ይታወቃል::
ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ሪፖርተሮቹን በመጥቀስ እንደዘገበው መምህር የኔሰው ራሱን በዕሳት እያጋይየ ወደ አዳራሽ ውስጥ ሲገባ የተመለከቱት ለወያኔው አገዛዝ ያደሩ ሆዳም የክልሉ ባለስልጣናት በመደናገጣቸው ከመምህሩ ለመራቅ ጥረት ያደርጉ ነበር ብሎአል። ኢሳት በዘገባው የኔሰው ገብሬ በከተማው ውስጥ ከሚታወቁት በሳል ምሁራን መካከል አንዱ እንደሆነ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩ ገልጾ “ፍትህ እና ዲሞክራሲ በሌለበት አገር መኖር ሰልችቶኛል፣ በዚህ ሁኔታ በህይወት መቀጠል አዳጋች ነው” በማለት ይናገር እንደነበር ገልጠዋል ብሉአል።፡ ኢሳት አክሎም መምህሩ በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት ከስራ ተባሮ እንደነበርና ወደ ስራ ለመመለስ ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ እንዳልተሳካለትም ታውቋል።
መምህር የኔሰው ገብሬ እፍትሃዊነትን በመቃወም በራሱ ላይ እርምጃ በወሰደበት ሰ ዓት እስፍራው የነበሩ የአይን እማኞች እንደገለጹት መምህሩ የወረዳና ዞን ምክር ቤት ሹሞች ስብሰባ ከሚያካሂዱበት ቦታ ሂዶ ወያኔ በአገራችንና በህዝባችን ላይ የሚፈጽመውን ግፍና መከራ እየተመለከትኩ መኖር ስልችቶኛል እያለ በራሱ ላይ ነዳጅ አርከፍክፎ በማቃጠሉ ወደ ዋካ ሆስፒታል ለህክምና እርዳታ ቢወሰድም ክፉኛ በመጎዳቱ ህይወቱ ሊተርፍ እንዳልቻለና ባለፈው ሰኞ ህይወቱ አልፎ በማግሥቱ ማክሰኞ ህዳር 5 እንደተቀበረ ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የተነሳውና እስካሁንም ውጥረቱ ያልረገበው የዋካና አካባቢው ህዝባዊ አመጽ አሁንም ባለበት መልኩ እንደቀጠለ መሆኑንና በአካባቢው የተሰማራው ልዩ ሀይል አሁንም ከስፍራው አለመልቀቁን ዘጋቢያችን ከአካባቢው ያሉ እማኞችን በስልክ በማነጋገር በላከልን ሪፖርት ገልጾአል።
ቀደም ብሎ በዋካ ከተማ ከተነሳ መብት ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ የተደረገውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ “የህዝቡ ጥያቄ ፍትሐዊ ቢሆንም፣ የወያኔ አገዛዝ ግን አስፈላጊውን መልስ ሊሰጥ አልቻለም” በሚል ምክንያት፣ የቶጫ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበረው ፈቃዱ ወልደሩፋኤልና ፣ የዞኑ አቃቢ ህግ የሆነው ከበደ ካሳ በራሳቸው ፈቃድ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ኢሳትን መዘገቡ ይታወሳል።
ይህ በዚህ እንዳለ በዘረኛው ወያኔ ኢፍትሃዊ አገዛዝ በመማረር እራሱን በኢሳት ያጋየው ወጣት የኔሰው ገብሬ አሟሟት ዜና በአገሪቱ ውስጥ እንዳይሰማ ለመከላከል ከዋካ ዞን ጋር የሚያገናኝ የስልክ መስመር በትክክል እንዳይሰራ መደረጉ ታወቀ::
የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በመላው አገሪቱ በዘረጋው ኢፍትሃዊነት በሙስናና በስልጣን ብልግና የተጨማለቁ የዞን አስተዳዳሪዎች በህዝብ ላይ እያደረሱ ያሉትን እስራትና ወከባ በመቃወም ባለፈ አርብ ህዳር 1 ቀን እራሱን በ እሳት ያጋየው ወጣት መምህር የኔሰው ገብረ ዜና በመላው አገሪቱ እንዳይሰራጭና ህዝባዊ ተቃውሞ እንዳይቀሰቅስ ስጋት የገባው የወያኔ ባለሥልጣናት የዋካ ዞን የስልክ መስመር መዝጋታቸውን የግንቦት 7 ዘጋቢ ከስፍራው በላከልን ዜና ገለጸ።
ወጣት የኔሰው ገብሬ በራሱ ላይ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት በዳውሮ ወረዳ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ በሃይል ለመጨፍለቅ ሲባል የታሰሩ እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱና ህዝብ ላነሳው ጥያቄ ተገቢው ምላሽ እንዲሰጥ ከክልሉና ከዞኑ ተወጣጥቶ በመስተዳድሩ ጽ|ቤት ስብሰባ ላይ ለነበረው የወያኔ ተላላኪዎች ቡድን ጥያቄ አቅርቦ እንደነበረ የተናገሩት የግንቦት 7 ምንጮች ፤ በአጸፋ ከባለሥልጣናቱ ለተሰጠው ትዕብታዊ ምላሽ “ፍትህ እና ነጻነት በሌለበት አገር ከመኖር ሞት ይሻላል እያለ በራሱ ነዳጅ እርከፍክፎ ክብሪት ስጪር በስርዓቱ ላይ የተንገፈገፉ ሚሊዮኖች አርማውን አንስተው እራሳቸውን ነጻ እንደሚያወጡ ጮክ ብሎ በእርግጠኝነት እየተናገረ እንደነበር ገልጸዋል።
የዚህ ዜና በአገርና በውጪ መዛመት ሊያስከትለው የሚችለውን መዘዝ የተገነዘበው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ፤ የኔሰው ገብሬ ህይወት ካለፈበት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ቀን ድረስ የዋካ ዞን ስልኮች ሆን ተብሎ መልዕክት እንዳይቀበሉ መደረጋቸውን ዘጋቢያችን ማረጋገጡን ገልጾአል።
በቱኒዚያ ለተቀሰቀሰውና እንደሰደድ ኢሳት በሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ለተሰራጨው የጸረ አምባገነኖች ህዝባዊ አመጽ ዋናው ምክንያት፤ ሞሃመድ ቡአዚዚ የተባለ አንድ ቱንዚያዊ ወጣት “የግፍ አገዛዝ ይብቃ” በሚል በራሱ ላይ ነዳጅ አርከፍክፎ ማቃጠሉ ዜና በመላው አገሪቱና ከዚያም በላይ በአለም መሰራጨቱ የቀሰቀሰው ቁጣ እንደሆነ ይታወቃል።
ቱኒዚያዊው ሞሃመድ ቡአዚዚ በራሱ ላይ በፈጸመው ቃጠሎ ሆስፒታል ገብቶ በነበረበት ወቅት የወቅቱ አምባገነን ፕሬዝዳንት የነበሩት ዚን እልአቢዲን ቤን አሊ ሆስፒታል ድረስ ሂዶ ጎብኚቶት እንደነበረና የቀብር ሥነሥርዓቱም በደማቅ ሁኔታ እንዲፈጸም ፈቅዶ እንደነበረ ሲታወቅ፤ የፋሽስቱ መለስ ዜናዊ አገዛዝ ግን ህዝብ ለማፈን በዋካ ዞን የመደበው የፈደራል ፖሊሲ ሆስፒታል በር ላይ በማቆም የየኔሰው ህይወቱ እስኪያልፍ ዘመድ ጓደኛ እንዳይጎበኘው ከመከልከሉም በላይ ህይወቱ ካለፈ ቦኋላ የቀብር ሥነሥር ዓቱ ላይ ማንም እንዳይገኝ እንዳደረገ የግንቦት7 ዘጋቢ አረጋግጦአል።
ወያኔ የስልክ ግንኙነት ለማወክ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም አንዳንድ መረጃዎች አፈትልከው እየወጡ በመሆናቸው ከመምህር የኔሰው ገብሬ ሞት በሁዋላ የአካባቢው ወጣቶችን መረጃዎችን ለውጭ አገር የመገናኛ ብዙሀን ሰጥታችሁዋል በሚል እየተዋከቡ መሆናቸው ተያይዞ የደረሰን ዜና አመልክቶአል። ወያኔ ዜናው እንዳይዛመት ለመከላከል የስልክ መስመሮችን ሆን ብሎ እያወከ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወያኔን የሰብ አዊ መብት ጥሰቶችንና ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊዎችን የማዋከብ ዘመቻ በማስረጃ እያጋለጠ ያለው የቢቢሲ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ቢሮን ጨምሮ ሌሎች የአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሀን የመምህር የኔሰው ገብሬን አሟሟት ሰፊ የዜና ሽፋን መስጠት መጀመራቸው ታውቆአል።
ኢፍትሃዊነትን ተቃውሞ የገዛ ህይወቱን በ እንዲህ አይነት ጭካኔ የቀጠፈው የኔሰው ገብሬ የወያኔ አገዛዝ አሰቃቂነት አመልካች መሆኑን ከህዝብ እየደረሱ ያሉ አስተያየቶች ያመለክታሉ።
ነጻነትና ፍትህ ፈላጊው የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህን ወጣት አርበኛ አርማ በማንሳት በክብር መሞት ነጻነት ከሌለው ህይወት የሚመረጥ መሆኑን ለፋሽስቱ መለስ ዜናዊና በዙሪያው ለተኮለኮሉት ራስ ወዳዶች ማሳየት ይኖርበታል።