ሲረገጥ የሚታገስ ሲጫኑት የሚሸከም መሬት ብቻ ነዉ!

የኢትዮጵያን ህዝብ ከተቀረዉ የአፍሪካ ህዝብ ከሚለዩት ዋና ዋና ባህሪዮች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ለአገሩ ዳር ድንበር፤ ለመሬቱና ለሐይማኖቱ የሚሰጠዉ ልዩ ቦታ ነዉ። ይህንን ልዪ ባህሪዩን ደግሞ እንኳን ወዳጆቹ ጠላቶቹም በዉል ተገንዝበዉለት ሳይወዱ በግድ በታሪክ መዝግበዉ ያስቀመጡትና ቢፍቁት ቢፍቁት የማይደበዝዝ ሃቅ ነዉ። የቀድሞዉ መሪዎቻችን ህዝቡ አገሩንና አንድነቱን ከወራሪ እንዲከላከል ጥሪ ሲያደርጉ አገርህን ሊቀማህ፤ መሬትህን ሊወርስና ሐይማኖትህን ሊያረክስ የመጣብህን ጠላት ለመከላከል ዛሬ ነገ ሳትል ተከተለኝ እያሉ ነበር። ለኢትዮጵያ ህዝብ መሬት የኤኮኖሚ ኃብት ብቻ ሳይሆን የባህሉ መገለጫ፤ የጥንት አባቶቹ ቅርስ መተላለፊያ፤ የዜግነቱ ዋስትናና የህልዉናዉ መሠረት ነዉ። ስለሆነም ኢትዮጵያ የምትባል አገር በታሪክ ታዉቃ መኖር ከጀመረችበት ግዜ ጀምሮ ኢትዮጵያዉያን መሬታቸዉን በየዘመኑ ከመጣ ጠላት ሲከላከሉ ቆይተዉ ዛሬ ላይ ደርሰዋል። ባለፉት ሃያ አመታት ወያኔ እራሱ ጭሮ ካመጣዉ ችግር ዉጭ አገራችንን የወረረ የዉጭ ኃይል የለም። ሆኖም እኛ ኢትዮጵያዉያን አንድነታችንን፤ መሬታችንን፤ ሐይማኖታችንንና ሰብዓዊ ክብራችንን በተመለከተ “ነፃ አወጣናችሁ” የሚሉን የወያኔ ዘረኞች ያደረሱብን በደል አንዳንዴ የዉጭ ጠላት ምን አደረገን የሚያሰኝ ነዉ።

የወያኔ መንጋ የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ ትኋን ተጣብቶት ኃብቱንና ቅርሱን መቦጥቦጥ የቻለዉ የገበሬዉን መሬት የራሱ ንብረት ማድረግ በመቻሉ ነዉ። ወያኔ የጻፈዉ ህገ መንግስት መሬት የመንግስትና የህዝብ ንብረት ነዉ ይላል፤ ሆኖም የወያኔን ፀባይና አገራችን ዉስጥ ምላሽ ያላገኘዉን የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ የተገነዘበ ማንም ሰዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሬት የህዝብና የመንግስት ሳይሆን የወያኔ የግል ንብረት መሆኑን በሚገባ ያዉቃል። ብዙ አለም አቀፍና የአገር ወስጥ የእርሻ ጠበብቶች የኢትዮጵያ ገበሬ የመሬቱ ባለቤት ካልሆነ ኢትዮጵያ ከድህነትና ከጥገኝነት አትላቀቅም ብለዉ በተደጋጋሚ ወያኔን መክረዋል ። ይህንን የአዋቂዎች ምክር ጆሮ ዳባ ልበስ ያለዉ ወያኔ ግን ከድጡ ወደማጡ እንዲሉ ጭራሽ የከተማዉንም መሬት ከባለቤቱ ቀምቶ የራሱ ለማድረግ ከህዝብ ጋር ግብግብ ተያይዟል። ወያኔ አዲሱ የመሬት አዋጅ የመሬትን ባለቤትና ተጠቃሚ መብትና ግዴት ያረጋግጣል ብሎ ህዝብን ለመደለል ቢሞክርም የአዋጁ አላማ ግን ከተሜዉን መሬት አልባ በማድረግ ይህንን ጧትና ማታ እረፍት የነሳዉን ህብረተሰብ እጅና እግሩን አስሮ ጭጭ ለማሰኘት ነዉ። የኢትዮጵያን ህዝብ ወያኔ ይህንን ከሰሞኑ ያወጀዉን የከተማ መሬት አዋጅ ተግባራዊ ሲያደርግ ዝም ብሎ ከተመለከተ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የገጠሩ አርሶ አደርና የከተማዉ ሠርቶ አደር መሬት አልባ ይሆናሉ። እንግዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ መሬት አልባ ሆነ ማለት ደግሞ ከታሪኩ፤ ከባህሉ፤ ከአባቶቹ ቅርስና ፈጣሪ ከሰጠዉ ንብረቱ ጋር ተላቀቀ ማለት ነዉ። ይህ የዛሬዉን ትዉልድ ብቻ ሳይሆን መጪዉን ተከታታይ ትዉልድ ደግሞ ደጋግሞ የሚገድል የወያኔ ሴራ በተግባር ሲተረጎም የኢትዮጵያ ህዝብ ዝም ብሎ ይመለከታል የሚል ብዥታ የለንም። ሆኖም በዚህ በታሪካችን እጅግ በጣም ወሳኝ በሆነ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ ወጣት፤ሽማግሌ፤ ሴትና ወንድ ሳይል ሃያ አመት ሙሉ እምቆ ያቆየዉን ህዝባዊ ቁጣ አሁን ካልተወጣዉ ሌላ ከዚህ የተሻለ ግዜ ሊመጣ እንደማይችል ከማስጠንቀቅ ወደኋላ አንልም።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ኢትዮጵያ ዉስጥ አዲስ የመሬት ባለቤት፤አዲስ የፋብሪካ ባለኃብት፤አዲስ የቢዝስ ህብረተሰብና በአጠቃላይ አዲስ የከበርቴ መደብ ለመፍጠር በብሔራዊ ደረጃ ዕቅድ አዉጥቶ መንቀሳቀስ ከጀመረ አመታት የተቆጠሩ ሲሆን በተለይ ከ1997 ዓም ጀምሮ ይህንን ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ጥድፊያዉን ተያይዞታል። መለስ ዜናዊ በ1997ቱ ምርጫ የደረሰበትን ሽንፈት አልቀበልም ማለቱ ብቻ ሳይሆን ድምፄ ይከበርልኝ ብሎ መብቱን የጠየቀን ህዝብ በጭካኔ መጨፍጨፉ ምንግዜም ቢሆን የማይረሳን መጥፎ ትዝታ ነዉ። የሚገርመዉ መለስ ዜናዊ በ1997ቱ ምርጫ የደረሰበትን ሽንፈት የሚያላክከዉ በራሱ ምግባረ ብልሹነትና አምባገነንነት ላይ ሳይሆን “የደርግ ርዝራዥ” እያለ በሚጠራዉ የከተማዉ ነዋሪ ህዝብ ላይ ነዉ። ከዚህ በመነሳት ይመስላል ወያኔ የከተማዉን ነዋሪ ህዝብ ለመበቀል የከተማ መሬት ሊዝ የሚል አዲስ አዋጅ በማወጅ በህግ ሽፋን ከተሜዉን ኢትዮጵያዊ መሬት አልባ ለማድረግ ቁጭ ብድግ ማለቱን የጀመረዉ። ወያኔ ይሀንን የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘምና ዬኔ የሚላቸዉን ሁሉ የመሬት ባለቤት ለማድረግ ያወጀዉን አዋጅ ፍትሃዊ አዋጅ እያለ ህዝብን ለመሸንገል ቢሞክርም የአዋጁ ዋና አላማ ከተሜዉን መሬት አልባ በማድረግ ይህንን ጧትና ማታ እረፍት የነሳዉን ህዝብ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ ነዉ።

ወያኔ እያንዳንዱን የገጠር ነዋሪ “ምን በላህ” እና “ምን ጠጣህ” ብሎ መጠየቅ በሚያስችለዉ ደረጃ መቆጣጠር የቻለዉ የገጠሩ ህዝብ የደም ስር የሆነዉን መሬት ሙሉ በሙሉ መዳፉ ዉስጥ ማስገባት በመቻሉ ነዉ። የወያኔ መሪዎች የመሬት በመንግስት ይዞታ ስር መሆን የሚጠቅመዉ ገበሬዉን ነዉ ብለዉ ቢወተዉቱም እንደዚህ አይነቱ የመሬት ይዞታ የወያኔን በጠመንጃ የተያዘ ስልጣን ከማራዘም አልፎ ደሃዉን የኢትዮጵያ ገበሬና ሠራተኛ ጠቅሞ አያዉቅም ለወደፊትም አይጠቅምም። የወያኔ ካድሬዎች በየገጠሩ እየዞሩ እኛን ካልመረጥከን ከቤት ንብረትህ ትፈናቀላለህ፤ማዳበሪያ፤ምርጥ ዘርና የብድር አገልግሎች አታገኝም እያሉ በማስፈራራት ፓርቲያቸዉ በሚገርም ሁኔታ 99.6% የፓርላማ መቀመጫ እንዲያሸንፍ ማድረግ የቻሉት የገጠሩ መሬት የፓርቲያቸዉ ንብረት በመሆኑ ነዉ። አመፀኛዉ መለስ ዜናዊ ግን በዚህ የረካ አይመስልም፤ ስለሆነም የ1997ቱ ዉጤት በምንም መልኩ እንዳይደገም የከተማዉን ህዝብ ልክ እንደገጠሩ አርሶ አደር ከመሬቱ አፈናቅሎ የህወሀት ጥገኛ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል።

እንደ ታማኝ ፈረስ በመለስ ዜናዊ ልጓም ተለጉሞ ግራና ቀኝ የሚዘለዉ የኢትዮጵያ ፓርላማ በቅርቡ እወክለዋለሁ የሚለዉን የከተማ ነዋሪ ህዝብ ከመሬቱና ከቤቱ ነጥሎ ንብረት አልባ የሚያደርግ አዲስ አዋጅ አጽድቋል። ይህ አዋጅ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነዉ ወያኔ በጠመንጃ የጨበጠዉን ሥልጣን ዘለአለማዊ ለማድረግ ካቀዳቸዉ ዕቅዶች አንዱ ነዉ። እዚህ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በዉል እንዲገነዘበዉና ከወዲሁ እንዲያስብበት የምንፈልገዉ እጅግ አደገኛ የሆኑ ብዙ የሆኑ የወያኔ ዕቅዶች አሉ። እነሱም።

አንደኛ- ወያኔ በጋምቤላ፤በኦሮሚያ፤በቤንሻንጉልና በሌሎችም የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች መሬትን ከባለቤቱ ነጥሎ ለባዕዳን በመሸጥና በማከራየት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ባለቤትነት የማይሰማዉና ወያኔን እንዳከበረ የሚኖር ለአካባቢዉ ባዕድ የሆነ የመሬት ባለቤት መደብ እየፈጠረ ነዉ። የዚህ ሴራ ዋነኛዉ አላማ ደግሞ ገበሬዉን የወያኔና የዚህ በመፈጠር ላይ ያለ ባዕድ ባለ ኃብት መደብ ጥገኛ በማድረግ ከመብቱና ከነፃነቱ ይልቅ “ከእጅ ወደ አፍ” ወደሆነ ኑሮዉ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ለማድረግ ነዉ። ዛሬ ወያኔ ይህንን በገጠር የጀመረዉን የመሬት ቂሚያ በከተማዉም ለመጀመር አዋጅ አዉጇል።

ሁለተኛ- ወያኔዎች ባለፉት ሃያ አመታት አፎርት የሚባል በኢትዮጵያ ህዝብ ደምና እምባ የተገነባ የኤኮኖሚ መዋቅር በመገንባት መለስ ዜናዊ “ወርቃማዉ ዘር” እያለ በሚጠራዉ የአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ የሚመራ እጅግ በጣም ግዙፍ የሆነ ባለ ኃብት መደብ ፈጥረዋል። ይህ መለስ ዜናዊ ሆን ብሎ ጠፍጥፎ የሰራዉ መደብ ደግሞ ካለመለስ ዜናዊ እራሱን ችሎ መቆም ስለማይችል የመለስ ዜናዊን ስርአት የሚቃወሙትን ኃይሎች ሽንጡን ገትሮ ከመዋጋት ወደኋላ የሚል አይደለም።

ሦስተኛ – ባለፉት አስር አመታት ዉስጥ ትምህርታቸዉን ጨርሰዉ ወደ ስራ አለም ለተሰማሩትና ኤፎርትን የመቀላቀል ዕድል ላላገኙ የትግራይ ገዢ መደብ አባላትና ቤተሰቦቻቸዉ ሌላ አዲስና ረቂቅ የሆነ የገንዘብና የንብረት መዝረፊያ መንገድ ተዘጋጅቷል። ይህ ወያኔ አዲስ መጥ ጓዶቹን ለማበልጸግ የቀየሰዉ ዘዴ ቀንና ማታ ሰርቶ ለልጆቹ የቋጠረዉን አብዛኛዉን ኢትዮጵያዊ የሚያደኸይ ነዉ። ለምሳሌ በአገራችን ታይቶ የማይታወቀዉ የሸቀጥ ዋጋ ንረትና መቆሚያ ቦታ ያጣዉ የብር ዋጋ መዋዠቅ ወያኔ የፀና ኢትዮጵያዊነት ስሜት ያላቸዉን ባለኃብቶች እያቀጨጨ ባምሳያዉ የፈጠራቸዉን አዲስ ባለኃብቶች የሚያፋፋበት የረቀቀ ዘዴ ነዉ። ሌላዉ ወያኔ የአገራችንን አንጡራ ኃብት በጉጅሌዎቹ ከሚያስዘርፍበት መንገድ አንዱ በጉምሩክ መስሪያ ቤቶች በኩል የሚደረገዉ አይን ያወጣ ዝርፊያ ነዉ። ጉዳዩ እንደዚህ ነዉ። የጉምሩክ መስሪያ ቤት ለአገር ግንባታ ስራ በሚል ሽፋን ለተወሰነ ግዜ የልማት ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ አገር ቤት ማስገባት እንደሚቻል የዉስጥ መመሪያ ያወጣል። መመሪያዉ የዉስጥ መመሪያ ይባል እንጂ የመመሪየዉን መዉጣት የሚያዉቁት ወያኔ ዬኔ የሚላቸዉና ከዉስጥም ዉስጥ የሆኑ የወያኔ እልፍኝ አስከልካዮች ብቻ ናቸዉ። አነዚህ የወያኔ እልፍኝ አስከልካዮች ለአገር ልማት ጠቀመም አልጠቀመ ያሰኛቸዉን ያክል ዕቃ ከቀረጥ ነፃ ወደ አገር ዉስጥ ካስገቡ በኋላ ህግ አክባሪዉ ነጋዴ በቀረጥ ነፃዉ ንግድ መሳተፍ ሲጀምር ግዜዉ አልፏል ተብሎ ይባረራል። ዛሬ በዚህ አይነቱ ወገናዊ አሰራር በሚሊዮንና በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያካበቱ ወያኔ ሠራሽ ነጋዴዎች ቁጥር የትየለሌ ነዉ።

ለመሆኑ ወያኔ እነዚህን የኢትዮጵያ ህዝብ በቃ ያላቸዉን የኤኮኖሚና የፖለቲካ ፖሊሲዎች ህዝብ አናት ላይ እንደ ጫና የሚጭነዉ ለምንድነዉ ? መልሱ ቀላል ነዉ። ጥያቄዉን ለመመለስ ብዙ መመራመር የሚያስፈልግም አይመስለንም። የህወሀትን በተለይም የመለስ ዜናዊን የኋላ ታሪክ መለስ ብሎ መመልከቱ ይበቃል። መለስ ዜናዊ አብዛኛዉን የወጣትነት ዘመኑን የኖረዉ ጫካ ዉስጥ ነዉ፤ ይህ የጫካ ሰዉ ቤ/ክርስቲያኑ አልባኒያ ጥምቀቱ ማርክሲዝም ሌኒንዝም ነዉ። መለስ ዜናዊ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተግባር የሚተረጉማቸዉ ፖሊሲዎች እዚያዉ ጫካ ዉስጥ ማርክሲዝም ሊኒንዝምን ሲያጠና ያረቀቃቸዉ ፖሊሲዎች ናቸዉ። ከማርክሲዝም ሌኒንዝም መሠረታዊ የፍልስፍና መሠረተ ሃሳቦች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ ደግሞ የፖለቲካ ስልጣንን ለመቆጣጠር ኤኮኖሚዉን ተቆጣጠር የሚል ለመሆኑ አንድ ሰሞን ደርሶብናልና ከኛ ከኢትዮጵያዉያን በላይ የሚያዉቅ ያለም አይመስለንም።

ወያኔ በቅርቡ አርቅቆ ለህዝብ ይፋ ያደረገዉን የከተማ መሬት ሊዝ አዋጅ ፍትሃዊና ጤናማ የመሬት ገበያ ለመፍጠር ያስችላል እያለ በነዚያ እሱ ብቻ በሚጨፍርባቸዉ ሬዲዮ፤ ቴሌቪዥንና ጋዜጣ ላይ እየደነፋ ህዝብ አዋጁን እንዲቀበል ለማስፈራራት ሞክሯል። የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ከማይገሰሱ የሰዉ ልጆች የተፈጥሮ ነፃነቶች ዉስጥ አንዱ የዜጎች የግል ንብረት የመያዝ መብት መሆኑን በሚገባ ያዉቃል፤ ደግሞም ይህ መሠረታዊ የሆነ የዜጎች መብት እየተረገጠ እንኳን ስለ አገር እድገትና ልማት በወጉ ደረቅ እንጄራ በልቶ ስላማደርም ማዉራት እንደማይቻል የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ካወቀ ቆይቷል። ደግሞስ መሬትን ጨምሮ አብዛኛዉ የአገሪቱ ንብረት በህወሀት ፓርቲ አባላትና በጥቂት የአንድ ዘዉግ አባላት ብቻ በተያዘበት አገር እንኳን “ነፃ ገበያ” ገበያ የሚባል ነገር እራሱ እንዴት ሊኖር ይችላል? ነፃ ገበያ ማለት ዜጎች በነፃነት በሚኖሩበት አገር ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸዉ ዕቃና አገልግሎትን እየተለዋወጡ በጋራ የሚያድጉበት የኤኮኖሚ ፅንሰ ሃሳብ አንጂ መለስ ዜናዊ ላሰኘዉ ህጋዊ ሽፋን እየሰጠ ያላሰኘዉን ደግሞ እጁን እያሰረ አንዱን ኃብታም አንዱን ደሃ የሚያደርግበት የመርገም ስርዐት አይደለም።

የኢትዮጵያ ገበሬ ለብዙ አመታት ለመኳንንቱ፤ለባላባቱና ለጭቃ ሹም የላቡን ዉጤት እየገበረ ኖሯል። በዚህ ስርዐት ዉስጥ መኳንንቱ ሰርግና ምላሽ እየደገሰ ደሃዉን ገበሬ የመለማኛ መሳሪያዉ አደርጎት ቆይቷል። ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ይህንን አስከፊ የሆነ ስርዐት ለመቀየር ፈቃደኛ ያልነበሩት የሳቸዉ ስርዐት ከፊዉዳሉ የመሬት ይዞታ ዉጭ በራሱ መኖር እንደማይችል ስለሚያዉቁ ነበር። ዛሬም እድገት፤ ትራንስፎርሜሺንና የህዳሴ ግድብ እየተባለ ብዙ ቢተረክም አገራችን ኢትዮጵያ አንድ በልቶ የጠገበን ከሃዲ በሌላ ለመብላት አፉን በከፈተ ከሃዲ ከመተካት ዉጭ ህዝብ አሜን ብሎ የተቀበለዉ የስርዐት ለዉጥ ማየት አልቻለችም። ዛሬ በግልጽ እንደምናየዉ የቀድሞዎቹ የፊዉዳል መኳንንት በአሁኖቹ የወያኔ ሹማምንት የቀድሞዎቹ የፋብሪካ ከበርቴዎች ደግሞ በዛሬዎቹ የኤፎርት ባለንብረቶች ተተክተዋል። በፊዉዳሉ ስርአት ዉስጥ የራሰቸዉን ህዝብ ሰጥ ለጥ ብሎ ለገዢዎች ሰግዶ እንዲኖር ያስገድዱት የነበሩት ባላባትና ምስለኔዎች በዛሬዎቹ ኃ/ማሪያም ደሳለኝን፤ ግርማ ብሩን፤ ሽፈራዉ ሽጉጤን፤ አዲሱ ለገሰንና ሬድዋን ሁሴንን በመሳሰሉ ወዶ ገባ ምስለኔዎች ተተክተዋል። የአፄ ኃ/ሥላሤ ስርዐት ከፊዉዳሉ የመሬት ግኑኝነት ዉጭ መኖር እንዳልቻለ ሁሉ የመለስ ዜናዊ ስርዐትም መሬትን ጨምሮ የአገሪቱን ዋና ዋና ኃብት ካልተቆጣጠረ መኖር እንደማይችል በሚገባ ያዉቃል፤ ስለዚህም ነዉ የገጠሩ መሬት አልበቃ ብሎት የከተማዉንም መሬት የግሉ ለማድረግ ጎንበስ ቀና ማለት የጀመረዉ።

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ሃያ አመት ሙሉ መሬቴን ስጡኝ ብለህ ብትጮህም መለስ ዜናዊ ግን የመሬትን ጉዳይ አታንሱብኝ ብሎ ጭራሽ የመሬት ይዞታን ህገ መንግስቱ ዉስጥ ሸጉጦት መሬቴን ብሎ የጠየቀን ሁሉ በህገ መነግሰቱና በሀግ መንግሰታዊ ስርዐቱ ላይ የተነሳ ጠላት ነዉ እያለ ሲያስርና ሲገድል ቆይቷል። ዛሬ በግልጽ እንደምናየዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ መሬት የመንግስት ንብረት መሆኑ የጠቀመዉ የኢትዮጵያን ገበሬ ሳይሆን የወያኔን ገዢ መደብ አባላትና የህንድ፤ የቻይናና የሼክ መሐመድ አላሙዲንን ኩባንያዎች ብቻ ነዉ። በቅርቡ ከወደ ጋምቤላ እንደተሰማዉ ደግሞ የጋምቤላን ገበሬ ህይወት ይለዉጣል ተብሎ አገር የሚያክል ትልቅ መሬት የተሰጠዉ ካራቱሪ የሚባል የህንድ ኩባንያ አገራቸዉ ዉስጥ መሬት አጥተዉ የተቸገሩ የህንድ ገበሬዎችን በብዛት አስመጥቶ የእርሻ ስራ ለመጀመር ዝግጅቱን ጨርሷል። ይህንን ለማወቅ ደግሞ ጠንቋይ መቀለብ የሚያስፈልግ አይመስለንም። በለምለምነቱ የታወቀዉን የጋምቤላ፤የኦሮሚያና የቤንንሻነጉል ክልል መሬት በዘመናዊነት ስም ለህንድ ኩባንያዎች የሸለመዉ መለስ ዜናዊ የከተማዉን መሬት ደግሞ በእንዱሰትሪ ዘመናዊነት ስም ለቻይና መሸለሙ የማይቀር ይመስላል። መለስ ዜናዊ እጅና እግሩን ስላሰረዉ ብቻ እራሱን መቀለብ የተሳነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የሁሉም ነገር ቁልፍ የሆነዉን የፖለቲካ ሥልጣን ለወያኔ፤የገጠሩን መሬት ለህንድ የከተማዉን መሬት ደግሞ ለቻይና ሰጥቶ እሱ እራሱ እንዴት እንደሚኖርና ምን ላይ እንደሚኖር ካሁኑ ለይቶ ካላወቀ መጪዉ ዘመን ያበቃለት የባርነት ዘመን መሆኑን ካሁኑ እንዲገነዘበዉ አደራ እንላለን።

“የዘፈን ዳር ዳሩ እስክስታ ነዉ” እንደሚባለዉ ወያኔ እስከዛሬ የወሰዳቸዉ እርምጃዎች ዬት እንዳደረሱንና ዛሬም እየወሰደ ያለዉ እርምጃ ወዴት እንደሚወስደን በሚገባ የተገነዘብን ይመስላል። የወያኔ ጥረት በአንድ በኩል ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ ወያኔያዊ ስርአቱ እንዲቀጥል ማድረግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እሱ እራሱ ሆን ብሎ የፈጠራቸዉን ተቋማት በመጠቀም በገጠርና በከተማ ለወያኔ ስርዐት ታማኝ የሆኑና በስርአቱ ላይ ምንም አይነት ጥያቄ የማያነሱ የባለንብረቶች መደብ መፍጠር ነዉ። ይህንን ዕቅዱን ደግሞ ታዛዥ ለሆነና የፖለቲካ ፍላጎት ለሌለዉ የባዕድ ኃይል በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ስፋት ያለዉ ትልቅ መሬት በመስጠትና የኢትዮጵያን ገበሬ ከመሬቱ ነጥሎ የዚህ ባዕድ አካል ጥገኛ በማድረግ ተግባራዊ እያደረገ ነዉ።

ወያኔዎች ለእኛ መብትና ነፃነት የሚታገሉ ወንድሞቻችንን የዘር አካል እንደ ፊኛ ሲያፈነዱ፤ የሴቶች እህቶቻችንን ጡት እንደ ገመድ እየጎተቱ ሲያሰቃዩና ለምለም መሬታችንን ለባዕዳን ሲሸጡ ምንም ያደረግነዉ ነገር ባለመኖሩ የልብ ልብ ተሰምቷቸዉ ዛሬማ ጭራሽ ከተሜዉን በገዛ መሬቱ ላይ ገባር ሊያደርጉት ነዉ። እነ መለስ ዜናዊ እስከዛሬ የበደሉን አልበቃ ብሏቸዉ ዛሬማ “ምናባታቸዉ ይሆናሉ” በሚል ንቀት ተወልደን ለወግ ማዕረግ የበቃንበትን መሬት ከኛ ቀምተዉ እነሱ በአምሳያቸዉ ለፈጠሩት ባለኃብት ሊያከፋፍሉ ነዉ። አባቶቻችን ጅላጅል ልጅ የአባቱን መሬት በባለጋራ ሲያስቀማ “የልጅ ደንጋዛ የአባቱን መሬት ያጋዛ” ይሉ ነበር። የዚህ ዘመን ትዉልድ የሆንከዉ ኢትዮጵያዊ ወገናችን ሆይ ይህንን መለስ ዜናዊ የደገሰልህን ድግስ ከነመሶቡ ካልገለበጥከዉ የሚጠብቅህ ዕጣ ሳትወድ በግድ የእናትና አባትህን መሬት የወያኔ ከበርቴ ሲገዛዉ ቆሞ መመልከት ብቻ ነዉ። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዉያን እትብታቸዉ በተቀበረበት እናት አገራቸዉ ውስጥ ይቅርና ተሰድደዉ በሚኖሩበት የባዕድ አገር ዉስጥም ቢሆን በፍጹም ሊቀበሉት የማይገባ ለልጅ ልጆቻችን የሚተላለፍ ሐፍረት ነዉ።

ባለፉት ሃያ አመታት ስለ መለስ ዜናዊ ካወቅናቸዉ ብዙ ነገሮች ዉስጥ አንዱ መለስ ዜናዊ የለየለት ቂመኛ ስዉ መሆኑን ነዉ። ይህ ቂመኛ ሰዉ ጥርሱን ከነከሰባቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የከተማዉ ነዋሪ ህዝብ ነዉ። መለስ ዜናዊ ከተሜዉን በተለይም የአዲስ አበባን ከተማ ነዋሪዎች የሚኮንነዉ አንድም በፍራቻ አንድም “እንዴት ተደፈርኩ” ከሚል የቂም በቀል መንፈስ በመነሳት ነዉ። መለስ ዜናዊን እጅግ ካስደነገጡትና ሁሌም በፍርሃት ተሸብቦ እንዲኖር ካደረጉት ክስተቶች አንዱ የአዲስ አበባ ህዝብ “ሱናሚ” እያለ የሚጠራዉና ሚያዝያ 30 1997 ዓም ቅንጅትን በመደገፍ የተካሄደዉ ታላቅ ሠላማዊ ሠልፍ ነዉ። ካይሮ ጣሂሪር አደባባይ ላይ የተካሄደዉን ህዝባዊ ቁጣ የተመለከተዉ መለስ ዜናዊ የ1997ቱ ሱናሚ እንዳይደገም የተለያዩ እርምጃዎችን ወስዷል። ከነዚህ እርምጃዎች ዉስጥ አንዱ የከተማዉን ነዋሪ መሬት ቀምቶ ከተሜዉ ጧትና ማታ እጅ እየነሳ የሚኖር ጥገኛ እንዲሆን ማድረግ ነዉ። ይህ ከሰሞኑ ጆሯችን ዉስጥ የገባዉ የከተማ መሬት አዋጅ ተግባራዊ ሲሆን ደግሞ መለስ ዜናዊ ጋምቤላ ዉስጥ ካሳየን “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል” አይነት የሰቆቃ ትርኢት ዉጭ ሌላ ምንም ሊያሳየን የሚችለዉ ነገር አይኖርም። ሞኞች ሆነን ከደጃፋችን ላይ ሞፈር ማስቆረጥ ወይም ደጃፌን አላስነካም ብሎ በጀግንነት መቆም ግን የመለስ ዜናዊ ጉዳይ ሳይሆን የእኛ የኢትዮጵያዉያን ጉዳይ ነዉ። መብትና ነፃነታችንን የምናስከብረዉ፤ እንደ ሰዉ በአገራችን ተከብረን የምንኖረዉና ልጆቻችንን አሳድገን በሠላም የምንጦረዉ ይህ ሁሉ እንዳይሆን እንቅፋት የሆነብንን የመለስ ዜናዊን ስርዐት ሌሎች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም በቃ ብለን በህዝባዊ አመፅ ስናስወገወድ ብቻ ነዉ።