የወያኔ አገዛዝ ከአማራ ህዝብ ተጨማሪ መሬት ሊወስድ መሆኑ ተዘገበ
ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ከአማራ ህዝብ ተጨማሪ መሬት ለመንጠቅ እየተሰናዳ ነው ሲል ከኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን-ኢሳት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
አገዛዙ ከዋግ ሕምራ ዞን መሬት ቆርጦ ለትግራይ ክልል ለመስጠት በእንቅስቃሴ ላይ ነው ያለው ዘገባ፤ የዚህም ምክንያቱ 80 በመቶ የሚሆነው የተከዜ ተፋሰስ በዋግ ሕምራ ማረፉና በዞኑ አንድ ወረዳ የወርቅ ማእድን መገኘቱ ነው ብሏል።
ዘረኛው አገዛዝ ከዚህ ቀደም በለምነቱ የሚታወቀውን ወልቃይት ጠገዴ ከአማራ ህዝብ በጉልበት ነጥቆ ነባር ነዋሪዎቹን ለስደት በመዳረግ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ የትግራይ ገበሬዎችን በስፍራው ማስፈሩ እና ማስታጠቁ ይታወቃል። በተመሳሳይ ሁኔታም የትግራይ ገበሬዎች በዋግ ህምራ እንዲሰፍሩ እና ቤት እንዲሰሩ መደረጉን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ጥያቄ ማንሳት ሲጀምሩም ሰፋሪዎቹ ገበሬዎች እንዲታጠቁ መደረጉን ዘገባው አትቷል።
የተከዜ ግድብ ሲታቀድ 80 በመቶው በትግራይ ክልል እንዲሆን ታስቦ ነበር የሚለው ዘገባ፤ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ሲሆን ግን ዋናው የሃይል ማመንጫ ተርባይንና ሃያ በመቶ ተፋሰስ ብቻ በትግራይ ክልል በመሆኑ፤ ወያኔ የተቀረውን ተፋሰስ ከአማራ ክልል ለመውሰድ እንቅስቃሴ ጀምሯል ሲል አስረድቷል።
በተያያዘ ዜናም በተከዜ ግድብ ምክንያት በእርሻ ምርታቸው ላይ ጉዳት ለደረሰ የዋግ ህምራ ገበሬዎች እስካሁን ድረስ ካሳ አለመሰጠቱን፤ ለትግራይ ክልል ገበሬዎች ግን ከሁለት አመት በፊት መከፈሉን ዘገባው አክሎ ገልጿል።
ዘረኛው አገዛዝ የዋግ ህምራን መሬት ለመወሰድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በሚመለከት የህዝቡን ቅሬታ ለፌዴራል ጉዳዮች ያቀረቡ የአማራ ክልል መስተዳደር ሰዎች “አርፋችሁ ተቀመጡ” መባላቸውን እና፤ አንዳንድ የወያኔ ባለስልጣናትም “ቦታው የትግራይ ክልል ነው” እያሉ በይፋ እንደሚናገሩ ለማወቅ ተችሏል።