ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ተማሪ ህጻናት የፖለቲካ ስልጠና እንዲወስዱ እያስገደደ ነው ተባለ

“ሂውማን ራይትስ ዋች” የተባለው አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባወጣው ሰፊ ሪፖርት፣ ዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በትምህርት ቤቶች የፖለቲካ ትምህርት በማስተማር እና ተማሪዎች የፓርቲ አባል እንዲሆኑ በማስገደድ አለማቀፍ ስምምነቶችን እየጣሰ ነው ሲል ከሷል።

ድርጅቱ ተማሪ ህጻናት ሊማሩ በሚገባበት ሰዓት የፖለቲካ ስልጠና በግዳጅ እየተሰጣቸው ነው ብሏል። በጎንደር፣ በደሴ፣ በባህር ዳር፣ በአዋሳ፣ በዲላ፣ በይርጋአለም፣ በአምቦ እና በአርባ ምንጭ ያሉ መምህራን እና ተማሪዎች በአንድ ወቅት ለአንድ ሳምንት ያህል ትምህርት ተቋርጦ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ላይ ስልጠና መሰጠቱን መስክረዋል። በስልጠናው መጨረሻ ላይም ህጻናቱ አገራቸውን የሚወዱ ከሆነ ገዢውን ፓርቲ እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

ከአስራ አራት አመት በላይ የሆኑት ተማሪዎች በሙሉ የአምስት ቀኑን ስልጠና እንዲሳተፉ ግዳጅ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ለያንዳንዳቸውም በቀን 25 ብር ውሎ አበል እንደተከፈላቸው ሪፖርቱ ገልጿል። በአዋሳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ፓርቲውን እንዲቀላቀሉ ከተጠየቁት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆኑት አባል ሆነዋል ያለው “ሂውማን ራይትስ ዋች”፤ ከነዚህ ውስጥ ቃላቸውን የሰጡት ተማሪዎች የአባልነት ካርድ ካልያዝን ዩኒቨርሲቲ መግባት አንችልም ከሚል እና ሌላም ፍራቻ ጥሪውን እንደተቀበሉ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ፥ አገዛዙ ህጻናቱ በመደራጀት የስለላ መረብ እንዲፈጥሩ እያደረገ መሆኑን ሪፖርቱ አትቷል።

የወያኔ አገዛዝ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የመንግስትን ተቋማት እና የህዝብን ገንዘብ ህገ-ወጥ በሆኑ መንገዶች በመጠቀም በጉቦ እና በግዳጅ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላትን መሰብሰቡ ይታወቃል። ይህ አይነቱ አሰራር አገዛዙ ውስጥ ውስጡን የሚሰማው በራስ ያለመተማመን ነጸብራቅ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፤ በግዳጅ አባል ያደረጋቸው ሚሊዮኖች የመቀበሪያውን ጉድጓድ ቆፋሪዎች ይሆናሉ በማለት ግምታቸውን ይሰነዝራሉ።