ለፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ የተገነባው ሐውልት እንዲፈርስ መወሰኑ ተዘገበ
ከበርካታ ወራት በፊት በቦሌ መድሃኔአለም ቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ለፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ የተተከለው ሃውልት እንዲፈርስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አስተላልፏል ሲል ደጀ ሰላም የተባለው ድረ-ገጽ ዘግቧል።
የቤተክርስቲያኒቱ ፓትሪያርክ የሆኑት አቡነ ጳውሎስ ባለፈው ሐምሌ ወር የአስራ ስምንተኛ አመት በአለ ሲመታቸውን ሲያከብሩ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ሐውልት ማስተከላቸው ይታወሳል። በወቅቱ ከየቤተክርስቲያናቱ በተሰበሰበ መዋጮ የተገዛ እና 3.4 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መኪና በስጦታ መልክ እንደተሰጣቸውም ይኸው የመረጃ ድረ-ገጽ ዘግቦ ነበር።
ቤተክርስቲያኒቱን በሚመለከቱ ዘገባዎች ላይ የሚያተኩረው ደጀ-ሰላም፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2003 ዓ/ም በርካታ ውሳኔዎችን እንዳስተላለፈ እና ከነዛም ውስጥ አንዱ የሃውልቱ መፍረስ እንደሆነ ገልጿል። በየአጥቢያው አብያተ ክርስቲያኑ የተሰቀሉት የፓትሪያርኩ ፎቶግራፎች እንዲነሱም ውሳኔ ተላልፏል ብሏል።
የወያኔ አገዛዝ “ከሁለት ወራት በፊት በአቡነ ጳውሎስ የተበላሸ አሰራር ህዝቡ ለአመጽ ለመነሳሳት በቋፍ ላይ ነው በሚል ቤተክርስቲያኒቱ በአስቸኳይ ችግሩዋን እንድትፈትሽ አሳስቦ” ነበር ሲል ከየኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን – ኢሳት – ያገኘነው ዘገባ ያስረዳል።
ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ ከወያኔ ጋር ጥብቅ የሆነ የጥቅም እና የመንደር ልጅነት ትስስር እንዳላቸው እና ያንንም ተጠቅመው በሳቸው ላይ ሂስ የሚያቀርቡትን ዝም የማሰኘት ልምድ እንዳላቸው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።