ብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን የኑሮ ደረጃቸው እያሽቆለቆለ ነው ብለው እንደሚያምኑ ታወቀ

ሰማንያ በመቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የኑሮ ደረጃቸው ከጊዜ ወደጊዜ እያሽቆለቆለ እንጂ እየተሻሻለ ነው ብለው እንደማያምኑ የሌጋተም ኢንስቲቱዩት የብልጽግና መለኪያ ሪፖርት አስታወቀ።

ከሁለት አመታት በፊት ጀምሮ በየአመቱ የሚወጣውና የአለም አገራትን የብልጽግና ደረጃ የሚለካው ሪፖርት፣ ኢትዮጵያን ከ110 አገራት ውስጥ 107ኛ ላይ በማኖር ድህነት የተንሰራፋበት አገር መሆኗን አመልክቷል።

ሪፖርቱ ከአምስት ኢትዮጵያውያን አራት የሚሆኑት የአገሪቱ ኢኮኖሚ እድል ይፈጥርልናል ብለው ተስፋ አያደርጉም ብሏል። የወያኔ አገዛዝ የኢትዮጵያውያንን ኑሮ እንዳሻሻለ እና እራሱ የሰረቀውን ምርጫ ያሸነፈበት ምክንያትም ህዝቡ አገሪቱን እንዳለማ በመረዳቱ ነው ሲል በተደጋጋሚ እንደሚደሰኩር ይታወቃል። የሌጋተም የብልጽግና መለኪያ ሪፖርት ግን 83 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን አገዛዙ የድሃውን ችግር ለመቅረፍ በሚያደርጋቸው ሙከራዎች አልረኩም ብሏል።

ሪፖርቱ በተጨማሪም፥ በንግድ እድል፣ በአስተዳደር፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በደህንነት እና በግለሰብ ነፃነት እጅግ ዝቅተኛ የሆነን ደረጃ በወያኔ ቁጥጥር ስር ለምትገኘው ኢትዮጵያ ሰጥቷል። የወያኔን አገዛዝ የአስተዳደር ብቃት የሌለው ሲል ያወገዘው ሲሆን፤ የግል ነጻነትን ለዜጎች በመስጠት ኢትዮጵያን ከመቶ አስሩ አገራት መቶ ዘጠኝ ላይ አስቀምጧታል።