የለጋሾች ቡድን ዋልጌን ባያሰለጥንብን፤ ይህ ብቻውን ለኢትዮጵያ ታላቅ ውለታ ነው

ትዕቢተኛና ጉልበተኛ ኪስ አውላቂዎች ባዶ ኪስ ሲያጋጥማቸው ተበዳዩን ሰድበው፣ ደብድበውና አዋርደው የሚሸኙበት አጋጣሚ አለ። በኪስ አውላቂዎቹ እምነት “መናጢ” ተብለን ላለመሰደብና ላለመመታት ዘወትር ኪሶቻችንን በገንዘብ ሞልተን ለኪስ ማውለቅ “ሥራቸው” ተመቻችተን መገኘት ይኖርብናል። በፍርሃት፣ በይሉኝታም ይሁን በጨዋነት ይህንን የሚያደርጉ አይጠፉም። እየተሳደቡ የሚለምኑ፤ እየለመኑ የሚሳደቡ ባለጌ ዋልጌዎች ደግሞ አሉ። ተገቢ እንዳልሆነ እያወቁ አንዳንዶች በይሉኝታም ይሁን እምነታቸው አስገድዷቸው ለምነውና አባብለው ገንዘብ ይሰጧቸዋል። ኪስ አውላቂዎቹና ዋልጌዎቹ በዚህ ተበረታተውና ተዝናንተው ኪስ ማውለቃቸውን እና እያስፈራሩ መለመናቸውን ይቀጥላሉ። እንዲህ ዓይነቱ ብልሹ ሥነምግባር ከግለሰብ አልፎ የቡድን መለያ ባህርይ ሊሆን ይችላል። ባልታደሉ አገሮች ደግሞ እንዲህ ዓይነት ቡድኖች የመንግሥትን ሥልጣን ይዘው በህዝብና በአገር ላይ ሰልጥነው፤ ሰቆቃን በገፍ እያመረቱ ነው።

ኢትዮጵያ አገራችን የገጠማት ፈተና ይህ ነው። የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ በባህርዩ ከላይ የገለጽነውን ዓይነት ዋልጌ ኪስ አውላቂ ነው። ጉዳታችንን የከፋ ያደረገው ደግሞ በፍርሃት፣ በይሉኝታም ይሁን በጨዋነት ኪሱን ሞልቶ ለመሰረቅ የተዘጋጀ፤ እየተሰደበ ሲለመን እየለመነ የሚሰጥ አካል መኖሩ ነው። ይህ አካል የልማት ለጋሽ ቡድን (Development Assistance Group) ይሰኛል። የዋልጌዎቹ መሪ መለስ እየተሳደበ ሲለምን፤ የለጋሾቹ ቡድን እያባበለ ሲሰጥ እነሆ ሁለት አስርት ዓመታት ሊሞሉ ነው። ከረዥም ጊዜ ብሄራዊ ጥቅም አኳያ ከታየ የለጋሽ ቡድኑ ተግባር ከጥቅሙ ጉዳቱ ይበልጣል፤ ማስፈራራት ልመናን ውጤታማ እንደሚያደርግ ወንበዴዎቻችንን አስተምሮብናልና!!!

ለቀና ዓላማ እንኳን ቢሆን ከሌቦች ጋር መመሳጠር፤ ከውሸታሞች ጋር መደራደር ምን ያህል ራስን እንደሚያዋርድ ከለጋሾቹ ቡድን የተሻለ ምሳሌ አናገኝም። የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ወንጀሎች እየተጋለጡ ሲመጡ የለጋሾቹ ቡድን አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። እናም እራሱን ነፃ ለማውጣት እሱም ፊት ለፊት መዋሸት ጀምሯል።

የሰብዓዊ መብቶች ጠባቂ ዓለም ዓቀፍ ድርጅት (Human Rights Watch) የመለስ ዜናዊ አገዛዝ እንደምን አድርጎ እርዳታን ለፓርቲ ሥራ እንደሚያውል ያጋለጠበትን ሪፓርት በመቃወም የለጋሾቹ ቡድን ያወጣውን መግለጫ በጥንቃቄ ያነበበ ሰው ቡድኑ ወደ የት እያመራ እንደሆነ መገመት አያቅተውም። የመግለጫው ይዘት ለምኖ ከመስጠትም ሆነ አውቆ ለዝርፊያ ከመመቻቸት እጅግ ያለፈ ነው። መግለጫው የለጋሾቹ ቡድን የደረሰበትን የሞራል ወለፈንዲ (absurdity) ጥልቀት ያሳያል። መለስ ተቃዋሚዎችን አስሮና አንገላቶ ባልሰሩት ስህተት ይቅርታ ጠይቀው ራሳቸውን እንዲያዋርዱ እንደሚያደርግ ሁሉ የለጋሾቹ ቡድንም የገዛ ራሱን እንዲያዋርድ ያስገደደው መሆኑን ያሳያል።

መለስ በሞት አፋፍ ያሉ ድሆችን በመያዣነት ይዞ “እኔ በምፈልገው መንገድ ካልሰጣችሁኝ ይህን ሁሉ ህዝብ ሲሞት ታያላችሁ” እያለ የለጋሾቹን ቡድን ያስፈራራል። ክፉ ላለማየት የለጋሾቹ ቡድን ከክፋት ጋር ይተባበራል። “የልማት መንግሥት መሆኔን ካልመሰከራችሁልኝ በሊማሊሞ በኩል ሂዱ” ሲላቸው እውነት እየመሰላቸው “እንደፈቀድህ ይሁንልህ፤ ይችን ብቻ ለረሃብተኛ እንድናደርስ ፍቀድልን” ይሉታል። እናም ለእርዳታው ፍሰት መሳለጥ ሲባል ቡድኑ ስለመለስ ልማታዊነት የሃሰት ምስክርነት ይሰጣል።

ችግረኛን ለመርዳት ሲባል ከግፈኛ ጋር ማበር ለአስቸኳይ ጊዜ ርዳታ አሳማኝ ምክንያት ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ለረዥም ጊዜ የልማት ትብብር ግን ፈጽሞ ተቀባይነት ያለው ጉዳይ አይደለም። በኛ ግምገማ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የለጋሾች ቡድን የሞራል ፈተናውን ወድቋል።

ከለጋሾቹ ቡድን የሰሞኑ መግለጫ ለአብነት እንጥቀስ።

“የለጋሽ ቡድኑ አባላት በሚሰጡት ርዳታ አማካይነት መሠረታዊ የጤና አገልግሎት፣ ትምህርት፣ ውሃ እና የረዥም ጊዜ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ የሚሊዮኖች ድሆች ህይወት ተለውጧል። የኛ ፕሮግራሞች ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች እንድታሳካ የሚረዱ ናቸው።”

ይህ አንቀጽ በርካታ ህፀፆች አሉበት። አራት ጥያቄዎችን ብቻ ጠይቀን እንለፍ።

  1. መለስና ቡድኑ ትምህርትን፣ ጤናን፣ ውሃን አስፋፋሁ እያለ ቀንና ለሊት ሲያደነቁረን “ይኸማ የተሰራው በኛ ገንዘብ ነው” ብላችሁ አንዴም አለመናገራችሁ ከምን የመጣ ነው?
  2. በድሃው ስም ከለገሳችሁት ገንዘብ በርከት ያለው እናንተው አገር ባሉ ባንኮች በግል ሂሳብ መያዛቸውን አታውቁም?
  3. ከገንዘባችሁ ከፊሉ አዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ባህርዳርና አዋሳ ውስጥ ህንፃ እየተገነባበት እንደሆነ አንዳችም መረጃ የላችሁም?
  4. እንዳላችሁት የሚሊዮኖች ድሆች ህይወት የተለወጠ ከሆነ ለምንድነው በያመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ድሆች የሚኖሩት?

የለጋሾቹ ቡድን መግለጫ በመቀጠልም እንዲህ ይላል::

“የራሳችን የሆነ ገለልተኛ ኮሚሽን አቋቁመን ምርመራ አድርገናል ሆኖም ግን ሂውማን ራትስ ዎች እደረሰበት ድምዳሜ ላይ አልደረስንም፤ ሥልታዊ የሆነ መጠነ ሰፊ ምዝበራ አላጋጠመንም።”

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ምርመራችሁ ገሃድ ሃቅን ካላገኘ ምኑን ምርመራ ሆነ? የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ እርዳታን ለፓለቲካ ማዋል የጀመረው ዛሬ አይደለም። አሁንማ እንደ መንጋትና መምሸት የተለመደ ነገር ሆኗል። የለጋሾቹ ቡድን ምርመራ ግን ይኸንን እንኳን ማግኘት አልቻለም።

የለጋሾቹ ቡድን የኢትዮጵያን ህዝብ በመርዳት ላይ ያለ ይመስለው ይሆናል። ሃቁ ግን ህዝቡ ራሱን ከድህነት ነፃ የሚያወጣበትን ጊዜ እያራቀበት መሆኑን ነው።

መለስ በእርዳታ የሚቀበለውን እያንዳንዱን ብር የራሱን ዘረኛ ፓሊሲ በሚጠቅም መንገድ እንደሚያውል የለጋሾች ቡድን ጠንቅቆ ያውቃል ብለን እናምናለን። ቡድኑ የመለስ ምኞት እና የኢትዮጵያ ትንሳዔ ተፃራሪ ነገሮች መሆናቸውን አልተገነዘበ እንደሆነ ምርምራውን በዚህ መንገድ እንዲጀምር እንመክራለን።

ስለሆነም የለጋሾቹ ቡድን በእርግጥ ኢትዮጵያን መርዳት ከፈለገ ርዳታውን ለአገሪቱ መልካም ራዕይ ባለው አካል በኩል ያድርግ። ያን ማድረግ ካልቻለ ግን በገንዘቡ ዋልጌን ባያሰለጥንብን፤ ይህ ራሱ ለኢትዮጵያ ታላቅ ውለታ ነው።

ለለጋሽ ቡድኑ አስረግጠን መንገር የምፈልገው ሃቅ የሚከተለውን ነው። በዘረኛ ፓሊሲው አዋርዶ እየገዛን ያለውን አምባገነን ሥርዓትን የቱን ያህል እያባበላችሁ ብትቀልቡት በኢትዮጵያ ህዝብ የተባበረ ትግል መወገዱ ፈጽሞ የማይቀር ነገር ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!