የአውራምባ ታይምስ ማኔጂንግ ኢዲተር ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከሀገር ተሰደደ

የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ባለ አክስዮን ድርሻና የጋዜጣው ማኔጂንግ ኢዲተር ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከሀገር መሰደዱን የመረጃ ምንጮቻችን ገለጹ፡፡ እንደ መረጃ ምንጮቻችን ገለጻ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ሊሰደድ የቻለው “ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ገጥሞት እንደሆነ” ይገልጻሉ፡፡ ምንጮቻችን እንደሚሉት “ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ምርጫ 97 ተከትሎ ከታሠሩት ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነበር፡፡ እድሜልክ ተፈርዶበት በይቅርታ ተፈቶ ነበር፡፡ በጋዜጣ በሚጽፋቸው ጽሑፎች ይቅርታው ተነስቶ ከህዳር 11 ቀን 2004ዓ.ም ጀምሮ በዕድሜ ልክ እስራት ወደ ማረሚያ ቤት እንደሚገባ መረጃ ስለደረሰው አገር ለቆ ሊወጣ ተገዷል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ተገኝተን ስለ ጉዳዩ የሥራ ባልደረበቹን ብናነጋግራቸውም “እንደማንኛውም ሰው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ከአገር ወጣ የሚል ወሬ ከመስማታችን ውጪ ምንም የምናውቀው ነገር የለም” ብለውናል፡፡

ይቅርታው ስለመነሳቱ ጉዳይ ፍትህ ሚኒስቴር ይቅርታ ቦርድ ጽ/ቤት ተገኝተን ጥያቄ ያቀረብንላቸው የሥራ ኃላፊ እንደገለጹልን “የአቶ ዳዊት ከበደ ይቅርታ ጉዳይ በጽ/ቤታችን ተነስቶ አያውቅም፡፡ የይቅርታ አነሳስ አዋጅ አለ፡፡ በድብቅ የሚሰራ ሥራ የለም የሚሰራው በግልጽ ነው” ሲሉ መልሰዋል የጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ ይቅርታ እንዲነሳና እንዲታሰር የመንግስት ሚዲያዎች አፍቃሪ ኢህአዴግ ሚዲያዎች መንግስትን እስከመቼ ትግስት እያሉ ሲማፀኑ መክረማቸው ይታወቃል፡፡

ምንጭ