የወገን ቤዛ የሆነን ጀግና ሰም ለማጥፋት የአምባገነኖች የተለመደ ቅጥፈት
ከንጉሤ ጋማ
“ፍትህና ዲሞክራሲ በሌለበት አገር አልኖርም” በሚል ምክንያት ራሱን በእሳት አቃጥሎ በገደለው ጀግናዉ መምህር የኔሰው ገብሬ ላይ የመለስ መንግሰት የከፈተዉ የስም ማጥፋት ዘመቻ የህዝብ ቀልብ አልሳበም። ክህደት፤ ዉሸትና ንቀት የአምባገነኑ መንግስት ተብዬዉ መለያ ጠባይ መሆኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ የተሰወረ አይደለም።
ከዚህ አሳፋሪና አስነዋሪ ባህሪይ ጋር ከጠ/ሚር መለስ ጀምሮ እገሌ ከእገሌ ሳይል ሁለት አስርተ አመታትን ያስቆጠረ፤ እጅግ የወረደ የስርዓቱ ባለስልጣናት ገበና እንደሆነ በሚገባ ይገነዘባል።
ህዝብ የሚያዉቀዉ እዉነት የሆነ የአደባባይ ሚስጠር ህሊናቸዉ በማይወቅሳቸዉ የመንግስት ተንበርካኪዎች ባደባባይ ይካዳል፤ ይዋሻል። እናም እንዲህ ያሉ ግለሰቦች በየደረጃዉ፤ በየቦታዉ፤ በየስራ መደቡ በተሰገሰጉባት አገር ምን ትርጉም ያለዉ ስራ ይሰራል? ብሎ ሁሌም በየግሉ እራሱን መጠየቁ የተለመደ ነዉ። ህዝብ የመለስን መንግስት ከማመን የተቆጠበዉ ከሽግግር መንግስቱ ምስረታ ጀምሮ እንደሆነ በርካታ ነጥቦችን መጥቀስ ይቻላል።
አንድ ትዉልድ እዉነት ሳይሰማ አለፈ! ተብሎ እንደዋዛ ቢነገር ሊያስገርም አይችልም። እልባት የጠፋለት ከጊዜ ወደጊዜ እየባሰ በመሄድ ላይ ያለ ነቀርሳነቱ ግን ያሳስባል።
አገራችን ከወደቀችበት ሁዋላ ቀር የኢኮኖሚ ድቀትና ድህነት እንድትላቀቅ፡ ከረሃብና ከምግብ ተመፅዋችነት በዘላቂነት እንድትወጣ ምንም አይነት ሀገራዊ ራዕይ እንደሌላቸዉ የታዘብናቸዉ ጠ/ሚር መለስ፤ አመራራቸዉና ፓርቲያቸዉ ወደ ስልጣን ከመጡ ከ20 አመት በሁዋላ ወገኖቻችን ከተደጋጋሚ ረሃብና ከምግብ እርዳታ አለመላቀቃቸዉ ብቻ ሳይሆን ይብሱኑ የሆቴል ጉርሻ ገዝቶ ከሚቀምስበት፡ ከቆሻሻ ገንዳ ለቅሞ ከሚጎርስበት ዘግናኝ ደረጃ ላይ መድረሱ በአገራችን የተንሰራፋዉ ስርኣት ምን ያህል የዘቀጠ እንደሆነ ያመላክተናል።
በህብረተሰቡ ዉስጥ ከጨበጡት ሃላፊነት በመነሳት የትናንቱን ከዛሬ፤ የዛሬዉን ከነገዉ የለት ዉሏቸዉ አንፃር፤ ተግባርና ማንነታቸዉን መፈተሽ የተሳናቸዉ መሪዎች በተግበሰበሱበትና ለነዚህ መሪዎች ከተንበረከኩበት ግላዊ ጥቅም ባሻገር የአገርና የወገን ጩኸት በፍፁም የማይሰማቸዉ ግዑዛን በተሰባሰቡበት ሁኔታ ዉስጥ ዕድገትና ብልፅግናን ማሰብ ከንቱነቱ በገሃድ ይታያል።
ከራሳቸዉ ጊዜያዊ ጥቅምና ብልፅግና ዉጭ ለታሪክና ለትዉልድ የማያስቡ በጠቅላላዉ ኢትዮጵያዊ ስሜትና ብሄራዊ ፍቅር የሌላቸዉ ….በየጊዜዉ በዕድገትና በልማት ስም በማጭበርበር የስልጣን ዕድሜያቸዉን ለማራዘም የባጥ የቆጡን በመቀባጠር….ከዚያ ባለፈ በደህንነትና በአፈና መዋቅሮች በመታገዝ…. በእስራት ..በማስፈራራት…..በግድያና በሰብኣዊ መብት ረገጣ ለመቀጠል ከመታገል ዉጭ ለዜጎችና ለአገር ዘላቂ ብሄራዊ ክብርና ጥቅም ይቆማሉ፤ ያስባሉ፡ ይጨነቃሉ፡ ይቆረቆራሉ ብሎ ሃያ አመት ካስቆጠረ አብሮ መቆየት በሁዋላ መገመት ከየዋህነት ያስቆጥራል።
አገሪቷ መሽቶ በነጋ ቁጥር ከድጡ ወደ ማጡ እያሽቆለቆለች በመሄድ ላይ መሆኗን የህዝቡ ኑሮ፤ ስደትና እንግልት ጠቋሚ ምልክት ከመሆናቸዉ አልፎ እንደቱኒዚያዉ የ26 አመቱ ጀግና መሃመድ ቡአዚዝ ሁሉ ፍትህና ዲሞክራሲ በሌለባት ኢትዮጵያ የመኖር ፍላጎት የሌላቸዉ ወጣቶች ለጊዜዉ አንገታቸዉን ደፍተዉ መኖራቸዉን ራሱን በእሳት አቃጥሎ የገደለው የወጣት የኔሰው ገብሬ ቆራጥ ዉሳኔ አመላካች ነዉ።
“የዛሬን እስቲ ይሁን!” በማለት ብዙ የኔሰዎች አመቺ ጊዜ፤ ቦታና ሁኔታ እስኪፈቅድላቸዉ ብሶትና ቁጣቸዉን በዉስጣቸዉ ቀብረዉ እንዳሉ ለመረዳት አያዳግትም።
የኔሰዉንና ቡአዚዝን የሚያመሳስሏቸዉ …ሁለቱም ግልፅነት፤ ተጠያቂነትና የህግ የበላይነት በሌለበት ፡ ህዝብ ሃሳቡን በነፃነት እንዳይገልፅ በታፈነበት ፤ በአገሩ እንደዜጋ የመኖርና፡ የመስራት መብቱ በተገደበበት ፍፁም አምባገነናዊ ስርኣት ዉስጥ ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸዉ እየተረገጠ መኖራቸዉ ነዉ።
ሁለቱም በሙያ ዕዉቀታቸዉ የስራ ዕድል አግኝተዉ እራሳቸዉንና ቤተሰቦቻቸዉን ማሳደር እንዳይችሉ ስርአቶቹ ነፃነት የነፈጓቸዉ የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ናቸዉ።
በተንሰራፉባቸዉ አምባገነኖችና ሆድ አደር ደጋፊዎቻቸዉ ምክንያት እነሱና እነሱን መሰል ዜጎች ግፍ፤ ሰቆቃ፤ እስር፤ ግርፋትና ሞት እየተፈራረቁባቸዉ መኖራቸዉን ጤናማ አዕምሯቸዉ መቀበል ባለመቻላቸዉ ፤ ኢ ሰብኣዊ በሆኑ አረመኔ ራስ ወዳዶች ህሊናቸዉ እየቆሰለ ፤ በህይወት መኖራቸዉ ትርጉም እንደሌለዉ ቁርጥ ዉሳኔ ያደረባቸዉ ጀግኖች ናቸዉ።
እናም ሁለቱም በአደባባይ በወገኖቻቸዉ ፊት በእራሳቸዉ ላይ ነዳጅ አርከፍክፈዉ እራሳቸዉን በማቃጠል ያደረባቸዉን ብሶትና ምሬት በመግለፅ በአርአያነት አለፉ።
በህዝቦቻቸዉ ትከሻ ላይ የተንሰራፉት አምባገነን ስርዓቶች የወገኖቻቸዉን ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እየረገጡ መቀጠል እንደሌለባቸዉ፡ ማህበራዊ ፍትህና ርትዕ እንዲሰፍን፡ ዜጎች ቁጣቸዉን በተለያየ መንገድ በማሳየት መብታቸዉን ለማስከበር ቁርጠኛ ዉሳኔ ላይ መድረሳቸዉን እንደችቦ ተቀጣጥለዉ ያበሰሩ ጀግኖች ናቸዉ።
የኢትዮጵያ ህዝብ በደቡብ ክልል ዳዉሮ ዞን ተርጫ ከተማ እራሱ ላይ እሳት ለኩሶ ዉድ ሕይወቱን አሳልፎ የሰጠዉን የ29 አመት ወጣት መምህር የኔሰዉ ገብሬን የትግል ችቦ ከሰሜን እስከ ደቡብ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፤ ዘር፤ ሃይማኖት፤ ፆታ፤…ሳይገድበዉ ተቀባብሎ በማቀጣጠልና በመለኮስ የነመለስን ጠባብ ዘረኛ ቡድን ከማቃጠል ወደሁዋላ እንደማይል ከወዲሁ ግልፅ እየሆነ ነዉ።
ዘወትር ዉሸት ልብስና ጉርሱ የሆነዉ የመለስ ዜናዊ መንግሰት በደቡብ ክልል ዳዉሮ ጀግናዉ መምህር ለእራሱ ህልፈት በእራሱ ላይ የጫረዉ እሳት እነሱን አቃጥሎና አንድዶ አመድ ከማድረጉ በፊት በቀላሉ ሊጠፋ እንደማይችል ከወዲሁ በመገንዘብ ይህን የህዝብ አመለካከት ለማስቀየር ይረዳ እንደሁ በማለት መቀላመድ ይዟል።
ጀግናዉ የነፃነት ተምሳሌት የፓለቲካ ተቃዋሚ ሳይሆን የአዕምሮ ሁከት የነበረበት በሽተኛ እንደሆነ ዋልታ የመረጃ ማዕከል በተባለ የግል አፈ ቀላጤ ተቋሙ አማካይነት የስም ማጥፋት ዘመቻዉን ከፍቷል። ይህ የመንግሰት የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ በግልፅ የሚያሳየን ሃቅ አለ። እብሪት፤ ንቀትና ዉሸት መለያ ባህሪያቸዉ የሆነዉ የእኛዉ አምባገነኖች ምን ያህል ለዜጎቻቸዉ ክብር ደንታ የሌላቸዉ የሆዳም ወራዳ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥርቅም መሆናቸዉን እንዳንዳች ፍንትዉ አድርጎ ያሳየናል።
እራሱን ለሕዝብ ልዕልና አሳልፎ በሰጠዉ ቱኒዚያዊ መሃመድ ቡዓዚዝ ምክንያት የሕዝብ ቁጣ የተቀሰቀሰባቸዉ ፕሬዝዳንት ቢን አሊ ሆስፒታል ድረስ ሄደዉ መሃመድ ቡአዚዝን በመጠየቅ አዛኝ ስብዕና እንዳላቸዉ ለማሳየት የሞከሩና ህዝብን ለማረጋጋት የሞከሩ ናቸዉ። ይህ ተግባር በራሱ ትልቅነት ነዉ።
ጀግናዉ የነፃነት ታጋይ የኔሰዉ ገብሬ የዋካ ከተማ ቀድሞ የነበረዉን የወረዳ አስተዳደር ደረጃ እንዲያገኝ በተደጋጋሚ ጥያቄ ካቀረበዉ የአካባቢዉ ህዝብ ጋር አብሮ የቆመ ሰዉ ነበር። ጥያቄዉን በማንሳታቸዉና በመደገፋቸዉ ምክንያት በዋካ ከተማ መንግስት ካሰራቸዉ ወጣቶች አንዱ ነበር። ከተለቀቀም በሁዋላ ለተቀሩት ባልደረቦቹ ስንቅ ሲያቀብልና እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርግ ነበር ። በምግባረ ጥሩነትና በአርቆ አስተዋይነት በጥሩ አንባቢነት በወጣቶች ዘንድ በአርአያነት የሚታይ እንደነበረና፤ በህዝብ ተቀባይነትና ክብር እንዳለዉ የአካባቢው ነዋሪዎች ምስክርነታቸዉን ሰጥተዋል። ይህንን እዉነት ለማዛባት ለምን አስፈለገ? መንግሰት የመረጠዉ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሆድ አደር መሪዎቻችን ሁሉንም በሚገባ የሚያዉቀዉን የዳዉሮን ህዝብ ምን ያህል እንደናቁት ከማሳየት ዉጭ ሌላ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
የተርጫ ሆስፒታል ዋና ሃላፊ መብራቱ ማሰቦ ፤የዳዉሮ ዞን ፓሊስ አዛዥና፤ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ እስራኤል አታአራ እንዲሁም የሙዋቹን እህት ወይዘሮ ታደለች በቀለን በመጥቀስ በሃሰት ምስክርነት ግለሰቡ እርምጃዉን የወሰደዉ በአዕምሮ ህመምተኛነት እንጂ የፍትህ መጉዋደልና ብልሹ አስተዳደርን በመቃወም እንዳልሆነ ለማስተባበል መሞከር እራሱን በመንግሰት ደረጃ ካስቀመጠ ቡድን ሳይሆን ከአንድ ተራ፤ ከሃዲ የወሮበላ ቡድን የሚጠበቅ መቀላመድ ነዉ። በደረሰበት ቃጠሎ ሆስፒታል በተኛበት ወቅት ህክምናዉን የተከታተሉትን ባለሙያ ዶክተር ሳይቀር የሙያ ስነምግባራቸዉን የሚፈታተን ሁኔታ ዉስጥ በመጣል ዘወትር በዘቀጠ ዉሸትና የሃሰት ተግባር ለተዘፈቀዉ የመለስ መንግሰት ይህን ፀሃይ የሞቀዉ እዉነት ማዛባት የሚሰጠዉ ጠቀሜታ የታሰበበት አይመስልም።
ዋልታ የመረጃ ማእከልና ሬዲዮ ፋና የአምባገነኑ መንግስት አፈቀላጤ በመሆን ዘረኛዉ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የአገሪቱን አንድነትና ሉኣላዊነት የማፈራረስ ቅዠቱን ተፈፃሚ ለማድረግ በዜጎች ላይ ቀጥተኛ የስነ ልቦና ጦርነት በመክፈት በግንባር ቀደምነት በመዋጋት ላይ ያሉ፤ ኢትዮጵያዊያን በስርኣቱ ግፍና በደል፡ እስራትና ግድያ እንዲፈፀምባቸዉ በመሳሪያነት የሚያገለግሉ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም።
አገርንና ወገንን ሽጠዉ ለዉጠዉ የከበሩ፡ ከመንግስት በሚያገኙት ድጋፍና ክልሎች በተለያየ ዘዴ ከአመት በጀታቸዉ እንዲደጉሟቸዉ እየተደረገ ስዉር በሆነ ሙስና በማይታመን ፍጥነት የተደራጁ የገዢዉ ፓርቲ የንግድ አካላት ናቸዉ። ዋልታም ሆነ ራዲዮ ፋና ለህዝብ ሚዛናዊ መረጃ የመስጠት ድርጅታዊ ተኣሚኒነት የሌላቸዉና የተቋሞቹ ሰራተኞችም ቢሆኑ ከጅምሩ እስካሁን ባለ ታሪካቸዉ ዉስጥ ከሚያቀርቡት ሚዛናዊነት የጎደለዉ የመረጃ ስራ አንፃር ሙያዊ የሞራል ብቃት የጎደላቸዉ፤ እዉቀትና፤ ስብዕናቸዉ በአሳዳሪዎቻቸዉ በባለቤትነት የተያዘ ቁሳቁሶች፡…እንደ ኒዉ ዮርክ ታይምሱ ጆን ስዌይንተን አገላለፅ ፤ ለእለት እንጀራቸዉ የተንበረከኩ ዝሙት አዳሪዎች ናቸዉ። ስለሆነም የአሳዳሪዎቻቸዉን ስሜትና ፍላጎት ለማርካት እዉነቱን ከማሳወቅ ይልቅ እዉነቱን ለማዛባት በጉልበትና በክንዶቻቸዉ ቢንበረከኩ፡ ሲቃ እየተናነቃቸዉ ቢጮሁ ቢለፈልፉ አይደንቅም፤ ሕዝብ እዉነቱን ያዉቃልና።
ዋልታ እንደቻይናዉ የዜና አገልግሎት / Xinhua/ ሁሉ በገዢዉ ፓርቲ ዉስጥ ተሸጉጦ የህዝብን እዉነተኛ መረጃ የማግኘትና የማወቅ መብት ለማዛባት የሚታገል መሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል። ይህ የሚያስታዉሰንን አንድ አጭር ጉዳይ ልጥቀስ። እኤአ በጃንዋሪ 23 2001 በቻይና የአዲስ አመት ዋዜማ በማእከላዊ ቤጂንግ ቲያናንሜን አደባባይ ላይ አምስት ሰዎች በእራሳቸዉ ላይ እሳት ይለኩሳሉ፤ ሁለቱ ይሞታሉ፤ ሶስቱ ይተርፋሉ። እነሲህ ሰዎች እነማን እንደሆኑና ለምን እርምጃዉን እንደወሰዱ እስካሁን አወዛጋቢ ሆኖ ቢቆይም መንግስት የወጠነዉ ማስመሰል እንደነበረበት ፍንጮች ጠቁመዋል። በስፍራዉ የነበረዉ የሲ ኤን ኤን የጋዜጠኞች ቡድን ሁኔታዉን በፊልም ሲቀርፅ የቻይና ፖሊሶች ደርሰዉ ይይዟቸዋል፤ ካሜራቸዉን ይነጥቋቸዋል፡ በመጨረሻ እስር ቤት ይከቷቸዋል።
የቻይና የዜና አገልግሎት Xinhua ግለሰቦችን ቃለ መጠይቅ በማድረግ ያቀናበረዉ ዜና ግን በዉሸት ላይ የተመሰረተ፤ መንግስት ፋለን ጎንግ የተባለዉን በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ያገኘ የመንፈሳዊ እምነት ተከታዮችን ለማጥቃት የወጠነዉ ተግባር መሆኑ ዋሺንግተን ፖስት ጋዜጣ ከሁለት ሳምንት በሁዋላ ባቀረበዉ የምርመራ ማስረጃ ከመጋለጡም በላይ እነሆ በአለም አቀፍ ደረጃ እስከዛሬ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።
በተመሳሳይ መንገድ በምስራቅ ቲቤት በኪርቲ ገዳም ቲቤታዊያን በሆኑ የሀይማኖት ተከታዮች ላይ የቻይና መንግስት የሚፈፅመዉን በደል በመቃወም እራሱን በማቃጠል ህይወቱን ባጠፋዉ ፈንትሶከ በተባለ መነኩሴ ላይ የተደረገዉ እዉነቱን ለማዛባትና የህዝቡን አመለካከት ለመለወጥ የተሞከረዉ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደእኛዉ ሁሉ በዘቀጠ ሞራል የተፈፀመ አሳፋሪ ድርጊት እንደነበር መጥቀስ ይቻላል።
በግንቦት 97ቱ ምርጫ የተዘረፈ ድምፁን ለማስመለስ አደባባይ የወጡትን ህፃናት፤ወጣቶችና አዛዉንቶችን በጠራራ ፀሓይ ጨፍጭፎ “ ባንክ ሊዘርፉ ነበር “ በማለት ስም የሚያጠፋ፡ የአገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት በማፍረስና ለባእዳን አሳልፎ በመስጠት ላይ መገኘቱን፡ በመንግስትነት የመቀጠሉ ህልዉና አደጋ ዉስጥ የሚወድቅ መስሎ ከታየዉ በሚያራምደዉ በዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ምክንያት በአንድነት አብረዉ የኖሩ ህዝቦችን በሊቢያ፡ በሶሪያና በየመን ከሚታየዉ በከፋ ሁኔታ ግጭት በመጫር ደም ለማፋሰስ መቆሙን፡ አስነዋሪ በሆነ የሙስና ተግባር ዉስጥ መዘፈቁን፡ የህዝብን ዲሞክራሲያዊና ሰብኣዊ መብት ለማስከበር ያልቆመ፤ በአንፃሩ ግልፅነት፤ ተጠያቂነትና የህግ የበላይነት በሌሉበት መልክ ህዝብን ረግጦ ለመግዛትና የአንድ ጠባብ ቡድን የበላይነትን ከ90 በመቶ በላይ በሚሆነዉ ህዝብ ላይ ለመጫን የሚያደርገዉን ጥረት አልፎ ተርፎ የአገሪቱን የሶስት ሺህ ዘመናት ታሪክ ለማዛባት ትንቅንቅ መያዙን በመረዳት ተስፋ ባለመቁረጥ አምርረዉ የሚተቹትን፤ የሚታገሉትን የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች፤ ጋዜጠኞችና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች “ ሽብርተኛ “ በማለት በሃሰት የሚከስና ስም ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚሰራ መንግሰት በመሆኑ “ፍትህና ዲሞክራሲ በሌለባት ኢትዮጵያ ለመኖር አልፈልግም ” በማለት እራሱን በአደባባይ ነዳጅ ለኩሶ በማጋየት መስዋዕት የሆነዉን ጀግና ስም ለማጥፋት መነሳቱ ማንንም ሊገርም አይችልም። ታዋቂ የአለም የመገናኛ ብዙሃንና ከ60 ሺህ በላይ በሆኑ ድረገፆች፤ ታዋቂ ግለሰቦች፤ ፀሃፊዎችና ገጣሚያን ዘንድ የየኔሰዉ አላማ፤ ማንነትና ጀግንነት ታላቅና ህያዉ ስፍራ እንደተሰጠዉ ሁላችንም ልብ እንለዋለን።
በመሃመድ ቡአዚዚ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ከ5000 ያላነሱ የቱኒዚያ ዜጎች” መሃመድ ደህና ሁን! የበደሉህን እንበቀላቸዋለን! ዛሬ ላንተ እናለቅሳለን፡ ለሞት ያበቁህን ግን እናስለቅሳቸዋለን!” በማለት ያሰሙት ድምፅ በቱኒዚያ እዉነት ለመሆን ወራት አልወሰደም ነበር። ይኸዉ የቱኒዚያ ዜጎች ፉከራ በተመሳሳይ ትርጉም በዳዉሮና በኢትዮጵያ ህዝብ ዉስጥ እንደሚያቃጭልና ጊዜ ጠብቆ እዉነት እንደሚሆን አምባገነን መሪዎቻችን የተገነዘቡት መሆኑን ዛሬ በየኔሰዉ ቤተሰቦችና በአካባቢዉ ላይ ተሸብረዉ የሚፈፅሟቸዉ የማሸበር ተግባሮች ብዙ ይናገራሉ።
ዘወትር ዉሸት፡ ዘወትር ክህደት… ሕዝብ በሚገባ የሚረዳቸዉ…. ነገር ግን መሪዎች ገደብ በሌለዉ ምግባረ ብልሹነት ተሸክመዉ የሚጓዛቸዉ ደካማ ባህሪዎች…..
አገርና ህዝብ የሚያዉቀዉን እዉነት ገድሎና ቀብሮ እስከመጨረሻዉ በህዝብ የመንግስት ስልጣን ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ መቀጠል ይቻላል ወይ ነዉ? መመለስ ያለበት ጥያቄ….
እግዚአብሄር ነፍሱን ይታደጋት! ለቤተሰቦቹ መፅናናትን ይስጣቸዉ!
የየኔሰዉ ገብሬ አርማ ከፍ ብሎ ይዉለበለባል!
Email: [email protected]