የፊት መብራት ወይስ ጭስ ማውጫ?

መኪና ወደፊት ሲጓዝ የፊት መብራት ወሳኝ አገልግሎት አለው፡፡ መኪናው ገደል እንዳይገባ፣ እንዳይገጭ፣ እንዳይጋጭና ሊያጋጥም ከሚችል አደጋ ራሱን እያዳነ ወደፊት እግዲገሰግስ የሚያደርገው የፊት መብራት ነው፡፡ የፊት መብራት ካለ በጨለማ መጓዝና ያሰቡበት መድረስ ይቻላል፡፡ መንገድን የሚያሳይ መሪ ብርሃን ነውና፡፡

ጭስ መውጫ ያለው ከኋላ በኩል ነው፡፡ የተቃጠለውን ያስወጣል፡፡ ጭስን በአግባቡ በትክክለኛው መጠንና ዓይነት ካላስወጣ ደግሞ ጋዙ አካባቢን ይበክላል፣ ያፍናል፡፡ በሽታም ያመጣል፡፡

ወደፊት እንድትገሰግስ የምንፈልጋትና የምንመኛት ውድ ኢትዮጵያችን የፊት መብራት ያስፈልጋታል፡፡ አገራችን ገደል እንዳትገባ፣ መንገድ እንዳትስት፣ ሊገጭዋት ከሚመጡ ለመጠበቅ፣ ሌሎችን እንዳትገጭና በሌሎችም እንዳትገጭ መንገዷን ብሩህ የሚያደርግላት የፊት መብራት ያስፈልጋታል፡፡

ፓርላማ፣ መንግሥት፣ የምርምር ተቋማት፣ መገናኛ ብዙኅን፣ የመሳሰሉት ተቋማት የአገራችን የፊት መብራቶች ናቸው፡፡

የፊት መብራቶች ናቸው ሲባል ግን የፊት መብራቶች ሆነው አገራችንን ከችግርና ከአደጋ ለመከላከል ኃላፊነት የተሰጣቸው ናቸው ለማለት ነው እንጂ፣ ሁሉም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የፊት መብራት ሆነው እየበሩ እያገለገሉ ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡

እየበሩ የፊት መብራትነት ድርሻቸውን የሚጫወቱ አሉ፡፡ ኃላፊነታቸውን ዘንግተውና ቀይረው ከፊት መብራትነት ወደ ጭስ ማውጫነት ተለውጠው ጋዝ ሲረጩ፣ ሲያፍኑና ሲበክሉ የሚታዩ አሉ፡፡

ስለዚህም ነው ድርሻቸው በሚገባ ተገምግሞ የፊት መብራት ወይም ጭስ ማውጫ መሆናቸው በውል ይለይ፣ ይታወቅ፣ ይፋ ይሁን የምንለው፡፡

ሌላ ጊዜም የነበረና ያለ ቢሆንም በተለይ ከቅርብ ወራት ወዲህ በአገራችን እየወጡ ያሉት ሕጐች፣ መመርያዎችና አሠራሮች ለኅብረተሰቡ ግልጽ እየሆኑ አይደሉም፡፡ ግልጽ ያልሆነ ነገር ትክክል አይደለም ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም ግልጽ የሆነ ነገር ትክክል ነው ማለትም አይደለም፡፡ ነገር ግን አንድን ነገር ትክክል ነው፣ ትክክል አይደለም ለማለት ግን ግልጽነት ያስፈልጋል፤ ውይይት ያስፈልጋል፤ ማብራሪያና ማስረዳት ይጠይቃል፡፡

ይህ ባለመሆኑ ሕዝቡ ሲደናገርና የተለያዩ አመለካከቶችና አስተያየቶች ከሕዝቡ ሲሰነዘሩ እየተሰጠ ያለው መልስ በእጅጉ የሚያሳዝን ነው፡፡ የሚቃወሙ ሁሉ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢዎች›› ናቸው፡፡ እየተቃወሙ ያሉት ‹‹ጥቅማቸው የተነካባቸው ናቸው›› የሚል መልስ ነው ተዘውትሮ የሚሰማው፡፡

‹‹ጥቅማቸው የተነካባቸውና ኪራይ ሰብሳቢዎች›› ሊቃወሙ፣ ሊያጣጥሉና ሊወቅሱ ይችላሉ፡፡ አያደርጉትም አይባልም፡፡ ነገር ግን የተለያዩ አስተያየቶችን የሰጡ ሁሉ፣ ተቃውሞ ያሰሙ ሁሉ፣ ትክክል አይደላችሁም የሚሉትን ሁሉ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢና ጥቅሙ የተነካበት ነው›› እያሉ ማንቋሸሽ፣ መስደብና ማብጠልጠል ግን ኃላፊነታችንን መርሳትና ከፊት መብራትነት ወደ ጭስ ማውጫነት መውረድና መቀየር ነው፡፡

የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 29 በማያሻማ መንገድ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ደንግጓል፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ማለት ወንጀል የመፈጸም ነፃነት ማለት አይደለም፡፡ ነፃነትንም ያካትታል፡፡ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ድንበር የማይከልለውና የመገናኛ ብዙኅን መሆን ብቻ የማይገድበው መሆኑንም ሕገ መንግሥታችን ይደነግጋል፡፡ ይህ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት እንዳይጣስና የማንም መጫወቻ እንዳይሆንም ሕገ መንግሥታችን ነፃነቱ እንዲከበር የሕግ ጥበቃና ከለላ ይደረጋል ይላል፡፡

በእንደዚህ ዓይነት መብትና ሕጋዊ ነፃነት ተመሥርቶ ሐሳቡን የሚገልጽ ግለሰብና ተቋም ግን በተለይም የመገናኛ ብዙኅን ‹‹ኪራይ ሰብሳቢ፣ ጥቅሙ የተነካበት›› እየተባለ ለምን ትናገራለህ? ለምን አስተያየት ትሰጣለህ? እየተባለ ነው፡፡

በተለይ በተለይ በእጅጉ የሚያሳዝነው ሐሳብን ለምን ገለጻችሁ የሚሉት፣ ጭስና ጋዝ እየረጩ ያሉት በኃላፊነት ደረጃ ሕዝብ እንዳይደናገርና እንዳይሳሳት የፊት መብራት ሆነው መንገዱን ያሳያሉ፣ የተሳሳተን ያስተምራሉ፣ ሐሳብ መግለጽን ያበረታታሉ የሚባሉት ተቋማትና መገናኛ ብዙኅን ራሳቸው ጭምር ናቸው፡፡

መገናኛ ብዙኅን የመንግሥትም ይሁኑ የግል ካሉባቸው ኃላፊነቶች አንደኛው ሕዝብን ማስተማር ነው፡፡ ሕዝብን ማሳወቅ ነው፡፡ የተሻለ መንገድና አካሄድ፣ ፖሊሲ፣ ሕግና መመርያ እየጠቆሙ የፊት መብራት መሆን ነው፡፡ ከ‹‹ተደነቀ››፣ ‹‹አበረታች›› እና ‹‹ተወገዘ›› ቃላት ውጭ ሌላ ቃልና ሐሳብ ማዳመጥና ማስተናገድ የማይፈልጉ፣ ‹‹ሂስ ተሰነዘረ››፣ ‹‹ቅሬታ ተሰማ››፣ ‹‹ተቃውሞ ገጠመ››፣ ‹‹ሕዝቡ ተናገረ፣ አጉተመተመ›› የሚሉትን ቃላት ‹‹የኪራይ ሰብሳቢ›› እና ‹‹ጥቅሙ የተነካበት›› ብቻ የሚጠቀምባቸው አድርገው የፈረጁ መገናኛ ብዙኅንና ተቋማት ‹‹የፊት መብራት›› ሚናቸውን በእጅጉ ወደ ‹‹ጭስ ማውጫ›› የቀየሩ ናቸው፡፡

እንደነዚህ ዓይነቶቹ የተለየ የሕዝብ አመለካከትና ሐሳብ የማይቀበሉ ተቋማት፣ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ለምን እንዲህ ትላላችሁ? ታደርጋላችሁ? ሲባሉ የሚሰጡት መልስ የታወቀ ነው፡፡ ‹‹የመንግሥት ደጋፊ ስለሆንን››፣ ‹‹ልማታዊ ስለሆንን››፣ ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነትን ስለምንቃወም›› እንደሚሉም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

በተጨባጭ መንግሥትን የሚያስጠሉ፣ ከሕዝብ የሚነጥሉ፣ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ሙሰኞች እነሱ ራሳቸው ናቸው፡፡ መንግሥት መጠናከር ከፈለገም መጀመሪያ ራሱን ከእንዲህ ዓይነቶቹ ራሱን ማጥራት አለበት፡፡

መንግሥት ይህን ዓይነቱን ዕርምጃ ለመውሰድ ቆራጥና ደፋር መሆን አለበት፡፡ ጥሩነትንና ሀቀኝነትን እያጠናከረ አስመሳዮችን ያስወግድ፡፡ ጭስና ጋዝ ሕዝብ ላይ እየረጩ የሚያፍኑትንና የሚበክሉትን በአስቸኳይ ይጠራርግ፡፡ የፊት መብራቶችን ይግጠም፤ ያጠናክር፤ ያብራ!!