እግዚአብሔር ኢትዮጵያን በራሱ መንገድ ይጠብቃታል እኛም እንተባበረው !! ብስራት ኢብሳ (ከሆላንድ)

በንግግር ሃሳቤን የመግለጽ ችሎታዬ በጣም ደካማ ስለሆነ አንዳንዴ እንደማንኛውም ሃገር ወዳድ የሚሰማኝን በወረቀት መሞነጫጨር እወዳለሁ። ሁሌ ለንባብ ባላበቃውም አልፎ ኣልፎ ሃሳቤን ለማውቃቸው አካፍዬ ልምድ ለመቀያየር፤ እርስ በርስ ለመማማር የተሻለ መንገድ ሆኖ አግኝቼዋለሁኝ።
ታዲያ የዛሬ ዓምት ግድም እንደ አቅሜ ሃላፊነትን በመውሰድ በዕውነተኛ ስሜ፣ የተሰማኝን፣ የማምንበትን ለውይይት መቀስቀሻ፣ ማበረታቻ፣ ትንሽ ይረዳ ይሆናል ብዬ ባቀረብኩት ምክር አዘል ጽሁፍ፣ አንዳንድ የኢንተርኔት ድህረገፅ ሃላፊዎች፣ ስለ ዲሞክራሲ በዙ ፅሁፍ የሚያወጡ፣ ስለ የሰው ልጆች ሃሳብን የመግለፅ መብት፣ መጨቆንን ሁሌ የሚቃወሙ፤ ለመብት ለኩልነት፣ ለሁሉም
እኩል የቆሙ ይመስሉኝ የነበሩ፣ ፅሁፌን እንዲያወጡልኝ ተጠይቀው ፣ እያነበቡ ትችቱ በአገዛዙ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ እነሱም የሚደግፏቸውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችንም ጭምር የሚነካካ መሆኑን ሲያዩ፣ አንዳንድ ጽንሰ ሃሳቦችን እንድቀይር ሲጠይቁኝ፤ ሳያነቡትም አውጥተውልኝም የነበሩት፣ በ24ሰዓት ከድህረ ገፃቸው ያነሱብኝን “ዲሞክራቶች” ምንነት ለማወቅ ሲረዳኝ፣ ሌሎች
ለንባብ እንዲበቃ የተባበሩኝን የድህረ ገፅ ሃላፊዎችን በዚህ አጋጣሚ ሳላመሰግን አላልፍም። ፅሁፉን በአርስቱ ላይ በሰከነ መንገድ ተወያይተው ድጋፍ፤ ዕርማት፤ ገንቢ ትችት የሰጡኝን፤ ያበረታቱኝን በዚህ አጋጣሚ ምስጋናዬን ሳቀርብ፣ በአንጻሩ በአንድ የፓልትክ ክፍል፣ በፅሁፉ፣ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በግል ህይወቴ፣ በስበዕናዬ ላይ፣ “በጎበዝ አልቆች በተቀነባበረ ዘመቻ “፣ በርግማን፣
በስድብ፣ በዛቻ፣ በስማ በለው አውቀውም ይሁን ሳያውቁ በደቦ የዘመቱብኝንም ጭምር ቢያንስ ፅሁፌን ስላነበቡ፣ ሃሳቤን ስለተጋሩኝና፣ ለፅሁፉም መነበብ አስተዋፆ ስላደረጉልኝ ምስጋናዬን አልነፍጋቸውም። እዚህ ላይ በጣም ግርማሞቴን ሳልገልፅ የማላልፈው፣ እዛ እጨፈጨፍበት የነበርው ክፍል፣ ለዓመታት በሃገር ጉዳይ በክፉም ይሁን በበጎ ለብዙ ዘመን የምንተዋውቅ፣ ብዙ
ቁም ነገር ሰርተን የነበር የመሰለኝ፤ አንድ ቀን እንኳን ተሳስቼ በጎ ሥራ ሥሰራ እንዳላዩ፣ ያ ሁሉ ዱላ ሲወርድብኝ፣ አፋቸውን ዘግተው፣ ነጠላቸውን አፍንጫቸው ላይ ጣል አድርገው ከዘራቸው ላይ ተደግፈው ደቦውን እያስተባበሩ በለው እያሉ፣ ዘመቻውን በከዘራቸው ሲያቀነባብሩብኝ፣ ሳይ፣ ስሰማ ቢገርመኝም፣ ትንሽ ያሳዘነኝ፣ ከነዚህ “ወዳጆቼ” ጋር ያን ያህል ዘመን ያባከንኩት ጉልበትና
ጊዜ ብቻ ነበር፡፡

ሆኖም ያደረኩት አስተዋጽኦ በጎም ይሁን ስህተት አምኜበት፣ ለትግሉ ይጠቅማል ብዬ የሰራሁት ስለሆነ ሞራሌን አይነካውም በተረፈ በሃገር ጉዳይ ላይ የኔ የተራ ግለሰብ ጉዳይ እንደ ትልቅ ነገር ወስጄ ጊዜያችሁን በዚህ አላባክንም። በባህላችን ስለ ራስ ማውራት የተለመደ አይደለም፣ ሆኖም ሁኔታዎች ካስገደዱኝና ገንቢጎን ካለው፣ ችግር የለም ወደፊት አየዋለሁ።
አንዳንዴ የፓልቶክ የምሽት ደንበንኛ ከሆንኩኝ ሰንብቻልሁ። ቴክኒዎሎጂ ምስጋና ይግባውና፤ የሳይበር ዓለም ከተስፋፋ ቦሃላ ምርጫችንም ሰፋ ብሎዋል :: የባለጌዎቹን ክፍል እንተወውና ሌሎች ብዙ ጠቃሚ ልምድ የሚቀያየሩባቸው (ከሃገራችን ውጪም ያሉትን ክፍሎች ያጠቃልላል ) ፖለቲካ፤ ትምህርት፣ ምክር፣ ግብረ ገብ፣ መረጃዎች፣ መዝናኛ ሙዚቃዎችና ቲያትሮች፣ ብቻ ሳይሆን
አንዳንዴም፣ እንደመታዘቢያም፣ መሳቂያም፣ ማኩረፊያም፣ መደበሪያም፤ የትዳር ጉዋደኛም ማፈለጊያ ….ወዘተ ሁሉ ያቀፈ ስለሆነ ግልጋሎቱ ሰፊ ነው። በተለይ እርጅና ተጫችኖንም ይሁን በጤና ምክንያት ደከም ብሎን፤ ወይም የከተማው ጫጫታ ሰልችቶትን እቤት መዋል ለጀመረን፣ የሳይበር ዓለም ትንሽ ማካካሻ ነው። ታዲያ ከአንዳንድ የፓልቶክ ወድጆቼም ጋር የተለያዩ ክፍል
እንደድሮ ጊዜ፣ ጊዮርጊስ፣ እስላም መስጊድ፣ እምዬ ኢትዮጵያ፤ ወይ ፍንክች፣ እሪ በከንቱ፣ ጎንደር አደባባይ፣ ብሶት አደባባይ፣ ጥርስ ማስጫ፣ መሳለምያ፣….…እያልን የዳቦ ስም እያወጣንላቸው፣ መፈላለግ፣ መቀጣጠር ጀምረናል።

ታዲያ ይቺን ትንሽ ፅሁፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ፣ ሰሞኑን በአንድ የዓርብ ምሽት አልፎ አልፎ ጎራ ከምልበት የፓልቶክ ክፍል ስለ ዲያስፖራ ፖለቲካ ሚና፤ ትርጉምና፣ የስደት አጀማመር፣ በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙርያ ተናጋሪ እንግዶች ተጋብዘው ውይይቱን ሳዳምጥ የአንደኛው ተናጋሪ አቀራረብ ከሌሎቹ ለኔ ለየት ባለ መንገድ በተሻለ የአዳማጭን ቀልብ የሳቡ ነበሩ። በአጀንዳው በደንብ
ተዘጋጅተው እንደቀረቡ ግልፅ ነበር። ማለቴም በተለያዩ የአገዛዞች ዘመን ምን ያህል ስደተኞች ከሀገራችን ወጥተው በየአህጉራቱ ተበትነው እንደነበር፤ በአሀዝ እያነፃፀሩ ከማቅረባቸውም በላይ፤ ስደት እራሱ መቼ እንዴት እንደተጀመረ ታሪኩን ከወደ መፅሀፍ ቅዱስም ጭምር እያጣቀሱ ሲያቀርቡ፣ ምናልባትም የአቀራረባችውም መንገድ፣ ሰከን ብለው ሚዛን የጠበቁ፤ ብዙ ጊዜ በየክፍሉ
ከምንሰማው ቅጽል፣ ቅጥያ፤ ስደብ፤ እርግማን፤ የተቆጠቡ ስለነበር እኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ውይይቱ እስከሚያልቅ አዳምጫሁ።
ውይይቱ እንዳለቀ፣ ተናጋሪው ባመላከቱን ጥቆማ፣ መፅሀፍ ቅዱሴን ከፍቼ ከመጀመሪያው ኦሪት ዘፍጥረት ከእነ ሙሴ የስደት ዘመን እስከ መፅሃፈ መሳፍንት አለፍ አለፍ ብዬ ያነበብኳቸው ታሪኮች ለየት ያለ ሃሳብ ስለጫሩብኝና አንዳንድ ከሃገሬ ሁኔታ ጋር ላመሳስል የተገደድኩበትን ጠቃሚ የመሰለኝን ሃሳብ ለወገኖቼ ለማካፈል ሲሆን፤ ምናልባት የሕብረተሰባችንን የዕድገት ጉዞ የሚያዩበት
የራሳቸው የተለየ መንገድ ያላቸው አንባቢዎች፤ ወይም የሃይማኖት መፅሃፍ ብዙም ስሜት የማይሰጣቸው እንዳሉ ብገምትም፤ ብዙዎች እኔ እንደገባኝና፣እንዳየሁት ሃሳቤን ሊረዱልኝ እንደሚችሉና እንደሚሞክሩም በመተማመን ነው፡፡ በተረፈ ታሪኩን በተሳሳተ መንገድ ተርጉሜ የሰዎችን ስሜት ጎድቼ ከሆነ ከወዲሁ ይቅርታ እጠይቃልሁኝ። አልፍ አልፍ ብዬ አጠር ባለ መልክ በመጽህፉ ላይ ያለውን አስቀድሜ፣ ቦሃላ ከፅሁፉ መሰረታዊ ዓላማ ጋር ለማያያዝ እሞክራልሁኝ።

እግዚአብሔር ለሙሴ ከከፍተኛ ተራራ ላይ በሩቁ እያሳየው እንዲህ አለው፣ “….. ለአብርሃም፤ ለይስሐቅ፤ ለያዕቆብ፤ የማልሁላቸው ምድር ይህች ናት በዓይንህ እንድታይ አደረግሁህ ነገር ግን ወደዛች አትሻገርም አለው” ኦሪት ዘዳግም ምዕራፍ34 ቁ 4 “እግዚአብሔር ወተትና ማር የምታፈሰውን ምድር ለኛ ይሰጠን ዘንድ ለአባቶቻቸው የማለላቸውን ምድር እንዳያሳያቸው ከግብፅ የወጡ የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰሙ እነዚያ ሰልፈኞች ሁሉ እስኪጠፉ ድረስ የእስራኤል ልጆች 40 ዓመት በምድረ በዳ ይሄዱ ነበር። ……” መፅሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ መዕራፍ 5 ቁ 6 ሰርዝ የተጨመረ ከላይ በተፃፈው ምዕራፍ ማንም ሊገነዘብ እንደሚችለው፤ ከግብፅ ተነስቶ እስራኤል ለመድርስ እንዳሁኑ ዘመን የተሙዋላ መገናኛ ባይኖርም፣ እንኩዋን አርባ (40) ዓምት ሊወስድ ቀርቶ አርባ ቀንም ሊወስድ አይችልም። ካልተሳሳትኩኝ ለእኔ እንደገባኝ፤ ታሪኩን ወደፊትም ወደኋላም ሄደን 3
በደንብ ካየነው የሚለው ባጭሩ፣ በዚያን ውቅት እግዚአብሔር እስራኤላውያንን ከፈርኦን ጭቆና፣ ከግብፅ ምድር እንዲያመልጡና ቃል ወደተገባላቸው ወደ ከንዓን በሚመለሱበት ጉዞ ላይ፣ አምላካቸው ከጎናቸው ሆኖ ታምር እየሰራላቸው፤ ከሰማይ መና፣ ዳቦ ያዘነበላቸው፤ ጠላቶቻቸውን በቸነፈር፤ በአንበጣ፣ በበሽታ እየመታ ስንት ተአምር እያሳያቸው፣ የሚያሳድዱዋቸውን እየተበቀለላቸው ይህን ሁሉ ተአምር እያዩ፣ እየሰሙ፣ እነሱ ግን በተደጋጋሚ አምላካቸውን በመካድ፤ ፈጣሪያቸውን እየረሱ፤ የወርቅ ጥጃ እየሰሩ ለሌላ እርኩሳን መናፍስት መስገድ ጀመሩ።
ስለዚህ እነዚህ ሀጢያተኞች እንደዚህ በተበላሸ አስተሳሰባቸው፣ እንደዚህ በበዛ ሀጢያታቸው፣ ቃል ወደተገባላቸው ሃገራቸው ገብተው ቢቀላቀሉ ኖሮ ምን ያህ አሳዛኝ ሁኔታ እንደሚፈጠር ጌታ ቀድሞ የማወቅ ችሎታ ስላለው ያ በተለይ ዕድሜው የገፋው ትውልድ፣ ተደጋግሞ ዕድል የተሰጠው ሃገሩ እንዳይገባ ሞቶ እስከሚያልቅ ድረስ በዛች አጭር ርቀት በሚገኙ ጥቂት በርሃዎችና ተራሮች ዙርያ
እያሽከረከረ፣ መንገዱን አጥፍቶባቸው አርባ ዓመት ሙሉ፣ ሲያንከራትታቸው ቆይቶ፣ ቢገቡ ሀገሪቱን ለውድቀት ይዳርጋሉ ብሎ ያሰባቸው ሀጢያተኞች ሰዎች ሞተው እስከሚያልቁ አቅጣጫቸውን አጨለሞባቸው እያንከራተተ ቀጥቶ ጨረሳቸው፡፡ (ትርጉም፣ ሰረዝ የኔ) ልብ በሉ፣ እግዚአብሔር ለሙሴ ቃል ስለገባለት ከተራራ ላይ ከነአንን በሩቁ አሳይቶታል “ለአብርሐም፤ ልይስሐቅ፤ ለያዕቆብ …µቃል የገባሁላችሁ ሃገር እዝያ ማዶ ያውልህ፣ አንተ ግን አንተ አትገባትም “ ነበር ያለው። እንደተነገረውም የእግዚአብሔር ታዛዥ ሙሴ የሞተው ሃገሩ ሳይገባ በሞዓብ ምድር ሲሆን፣የተቀበረውም እዛው ሸለቆ ውስጥ ነው ለሃጢያን የመጣ ለፃአድቃን ይተርፋል
እንድሆን እንጃ፣ ካህናት ወደፊት ያስረዱናል፡፡
እንግዲህ መፅሃፍ ቅዱስ እንደሚነግረን፣ ሙሴ ከሞተ ቦሃላ እግዚአብሔር፣ የሙሴን አገልጋይ የነበረውን የነነዌን ልጅ፣ ኢያሱን ከዓዲሱ ትውልድ ለመሪነት መርጦት፣ “ተነስታችሁ ወደ እስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስን ተሻገሩ“
ብሎ ነግሮዋቸው ነው ቃል ወደተገባላቸው ሃገር የገቡት፡፡ ከላይ በቀላሉ ማየት የሚቻላው ያንን ሁሉ ሃጢያት ይዘው ሃገራቸው እንዳይገቡ ያልፈቀደላቸው እግዚአብሔር በራሱ መንገድ፤ ሃገሪትዋንና፣ የሚፈልጋቸውን አሕዛብ፣ ሊደርስ ከሚችለው አደጋ ለመከላከል፣ ለማዳን እንደነበር ግልፅ ነው።
በእርግጥ ከዚህም ታሪክ ቦሃላ በተለያዩ ጊዜያት ሃገራቸውም ከገቡ ቦኋላም፣ መልሰው መላልሰው አምላካቸውን እየካዱ፤ ወደ ባዕድ አምልኮት እየተመለሱ በጠላቶቻቸው እጅ እንደጣላቸው እና፤ ከስህተታቸው ደግሞ እንደገና ተምረው፣ መንገዳቸውን አስተካክለው፣ ለፈጣሪያቸው ንሰሃ ሲገቡ፤ ይቅርታ ሲጠይቁ እንደገና አምላክ ሲታረቃቸውና ሲረዳቸው በተደጋጋሚ በዝርዝር ተፅፏዋል፡፡
በብዙዎቻችን እምነት እግዚአብሔር ከዚህ ታሪክ በፊትም፣ ሆነ ቦሃላ፣ ወደፊትም፣ ሥራውን እየሰራ ነው።
ይህን የዛን ዘመን ታሪክ በቀጥታ ሙሉ በሙሉ ከሃገራችን፣ ከሕዝባችን ታሪክ ጋር ለማመሳሰል ወይም ለማነፃፀር ባልሞክርም፣ ጊዜውም፣ ምክንያቱም፣ ሃገሩም፣ ሕዝቡም የተለየ ቢሆንም፣ በየትኛውም ዘመን ብዙ ተመሳሳይ ሁኔታዎች የማይቀየሩና፤ በተለያየ ባህሪ በራሳቸው ጊዜና ቦታ ሊገለጹ የሚችሉ ክስተቶች አሉ። ባጭሩ፣ ፈጣሪ፣ ሕዝብ፣ ሃገር፣ መሪ፣ ተከታይ፣ እምነት ክህደት፣ ፅድቅ፣ ኩነኔ፣ ጭቆና ነፃነት …..ወዘተ አብዛኛው በተለያየ ቅርጽ፣ ስም፣ በክርስትናም ይሁን በዕስልምና ተከታዮች፣ በአማኞችም ይሁን በማያምኑ፣ ከእኛ ፍላጎት ውጭ ይኖራሉ።
እነዚህ ተመሳሳይ ክስተቶች ካሉ ደግም ሰው እንደመሆናችን፣ ማመዛዘኛ፣ ማነጻጸርያ አዕምሮ ስላለን፣ ለበጎ ተግባር፣ ያለፈውን ካሁኑ፣ ያሁኑን ከወደፊቱ ማመዛዘን፣ ተፈጥሮ የሰጠን ፀጋ ስለሆነ ልንገለገልበት ይገባል። ከላይ እንደገለጽነው እንደ ሙሴ ዘመን ስራኤላውያን እግዚአብሄርን ክደው ይሰግዱለት እንደነበረው የወርቅ ጥጃ አይነት ሃጢያቶች በኛ ዘመን መጠበቅ ብዙም ከሌለብን፤ በሃገራችን ቢያንስ ላለፉት ምዕተ ዓምታት ስንመኘው፣ ስንታገልለት፣ ስንሞት፣ ስንታሰር ስንሰደድ፣ የቆየንበት ራዕይ ግቡን ሊመታ ያልቻለው ምን ሀጢያት ሰርተን ይሆን? ፈጣሪያችንን ምን አስቀይመነው ይሆን ችላ ያለን? ብለን ራሳችንን ብንጠይቅ፣ ስህተት አይሆንም። ስለ ሃገራችን ችግር በብዙ ምሁራንና ባለሞያዎች በስፋት ከምድራዊ ምክንያቶች ጋር እያዛመዱ ብዙ ትምህርቶች፣ብዙ ትንተናዎች አቅርበው አስተምረውናል፡፡
እስኪ ደግሞ ለየት ባለ መንገድና ምናልባትም ብዙም ባልተለመደ አቀራረብ፣ እንደ አብዛኛው ሰው እንደሚያስበው፣ በኛ ዘመን ሃጥያት ሊባሉ የሚችሉ፣ ስህተቶችን፣ አምላካችንንም ሆነ ሕዝባችንን አስቀይመናል የምንላቸውን ከሞራልም ይሁን ከኤቲክስ፤ ከምድራዊም ይሁን ስማያዊ ምክንያቶች ጋር አዛምደን ሃሳባችንን ዘርዘር አድርገን ሰፋ ባለ መንገድ ምክንያታችንን እንዴት
እንደምናቀርበው ለማየት እንሞክር።
ኢትዮጵያን ክደን በጎሳ ማምለክ መጀመራችን እግዚአብሔር እንደ የወቅቱ የባዕድ አምልኮ ወስዶት ይሆን? ጎሳ፤ ዘር፤ ብሔር፤ የዘመኑ ጣኦት ፈጣሪያችንም ይማይፈቅደው ይሆን? ኢትዮጵያን የሚያህል ሃገር ሰጥቶን ወደ መንደር ማተኮር መጀመራችን አሳዝኖት? የኔ ቡድን፣ የኔ ፓርቲ፣ የኔ ዘር፤ የኔ ሃሳብ፣ የኔ መንገድ፣ የኔ ፕሮግራም፣ የኔ ወንበር የኔ ራዲዮ፣ የኔ ፓልቶክ፤ ግለኝነት፣ እራስ ወዳድነት የኔ ………በዝቶ የኛን፣ ስላሳነስነው? ፣ እልኅኞች ስለሆንን? ፣ ቂም ስለምንቋጥር? ብቀላ ስለምንወድ? ፤ ስለምንፈራ፤ ገንዘባችን ስለ ሚያሳዝነን፤ ነብሳችን ስለሚያሳሳን፣ ህብረትን ስለምንሸሽ? ተሳስቼ ነበርን፤ ይቅርታን፤ አለማወቃችንን፣ ወደ እራሳችን ማየትን ስለምንጠየፍ? ስልትን ከልዩነት፤ ልዩነትን ከጦር፤ ጦርን ከሃጢያት ተምታቶብን ጌታን ስላስቸገርነው? ጠላትና ወዳጅን፤ ግትርነትንና መርህን፤ ዘዴንና አደርባይነትን፣ ፓርቲንና ሃገርን፣ ጓድንና ሕዝብን፤ ታሪክንና ልብወለድን፤ እኛ የምንፈልገውንና መሬት ላይ ያለውን ሃቅ፣ እውነቱን ከውሸት፣ ሀቀኛውን ከሚያምታታው፣ ታታሪውን ከንቶፈንቶው፣ ተደበላልቆብን ሃጢያታችን
እንደዝቋላ ተራራ ራሳችን ላይ ተቆልሎብን ይሆን? እንደዚህ ለመዘርዘር ብንሞክርና ድክመቶቻችንን እንደ ሃጥያት ብንወስደውና ከነሙሴ ዘመን ከነበረው ሃጢያት ብናመዛዝነው የኛ ትውልድ ብቻ ሳይሆን፣ ወደታች እኛም ኮትኩተን ላሳድግናቸውም
ባጠቃላይ ከኛ ጋር ንክኪነት ላላቸው ሁሉ ጦስ እንደምንሆን አምነን መቀበል አለብን። በሙሴ ዘመን እስራኤሎቹ እንደ ዋና ሃጢያት የተቆጠረባችው አምላካቸው እግዚአብሔር በዓይናቸው ስር ብዙ ተዓምር እየሰራላችው፣ ከብዙ ችግር እያዳነ እያሳያቸው እነርሱ ግን፣ጌታ ፈጣሪያቸው መሆኑን አለመቀበላቸውና በሌላ እርኩስ አማልክት በማመናቸው ነው። “የኛ ሃጢያት” ከላይ የተዘረዘሩት
በሙሴ ዘመን ከተሰሩት ስህተቶች ጋር አብሮ ጎን ለጎን ሚዛን ላይ ቢቀመጥና ቢመዘን፣ ምን አይነት ቅጣት ሊጠብቀን እንደሚችል ግምቱን ላንባቢ ብተወው ይሻላል።
አስቡት አሁን ከምናየው ችግር ተነስተን ወደፊት ሊፈጥጠር ለሚችለው አደጋ መተንበይ፣ እንኳን የፈጠረን አምላክ ቀርቶ ማንም ካፍንጫው ትንሽ አርቆ ማሰብ ፈቃደኛ የሆነን ዜጋ ማመዛዘን፣ መገመት ይችላል። ከራሳችን ካለፉት ዓመታት ተመክሮ እንኩዋን ብንነሳ፣ የዛሬ አርባ ዓመት አካባቢ፣ ቢበዛ በሁለትና ሦስት የፖለቲካ ድርጅቶች መሃል የነበሩትን ልዩነቶች ተወያይተን መፍታት
አቅቶን ስንት ችግር እንደደረሰ ብዝዎቻችን እናስታውሰዋለን። ያውም ሁላችንም የማርክስና የሌኒን ደቀመሙሮች ሆነን፣ ያውም እነ ማኦ በሶሻሊስት፣ ኮሚኒስቶች መካከል ያለው ቅራኔ በውይይት የሚፈታ ነው ጦርነት አያስፈልገውም እያሉ እያስተማሩን፣ የማንፈልገውን ክፍል ለመምታት፣ የማይመቸንን ላለመቀበል፤ ከማኦ በላይ ፈላስፋ ሆነን፣ ከሌኒን በላይ አስተማሪ ሆነን፣ በማወቅም
ይሁን ባለማውቅም፤ በወጣትነትም ይሁን በትግል ተመክሮ እጥረት፣ ከበጎ ራዕይ ጎን ብዙ ስህተት ተሳስተን ነበር። ዛሬም ከትላንቱ ስህተታች ብዙ የሚቀረን እንዳለ ይታያል፡፡
ዛሬም የትላንቱን ብቻ በመከላከል ዛሬ ልንሰራ የሚገባንን ጊዜና ጉልበት አላግባብ እያባከነው ነው። ዛሬም የምንወያይበትን አጀንዳ የሚያዘጋጅልን ወያኔ ነው። ሥራ ፈተን፣ በወያኔ ላይ እንዳናተኩር በየሳምንቱ አንዳንድ አጀንዳ እንደ አጥንት ይወረውርልና፤ አንዴ ባንዲራ ጨርቅ ሲል ሌላው ሳምንት የባንዲራ ቀን፤ አንዴ መሪዎቻችንን ያስራል ሌላው ጊዜ ይፈታል፣ እኛም አርዕስት እንዳጣን እንደ
ኳስ በረኛ እነሱ የሚሰሩትን ወሬ እየቀለብን አቧራው እስከሚጨስ ከበሮ እየደለቅን ሌላ አጀንዳ እስከሚቀየርልን ስንጫጭስ እንከርማለን፣ የራሳችን አጀንዳ የለንም ። ወያኔ ድምፁን ያጠፋ ሰሞን ውይይቶች ሁሉ ይቀዘቅዛሉ፣ ክፍሎች ሁሉ መፋዘዝ ይጀምራሉ ወይም እርስ በእርስ ወነጃጀል ይጀመራል። ሥራ የሚያሰራን ወያኔ ከሆነ አዕምሮዋችንንም መቆጣጠር ችሏል ማለት ነው፡፡
በገሀድ እንደታየው አብዛኛው ሕዝባችን የወያኔ የጎሳ አገዛዝ እንደማይደግፍና የስርዓት ለውጥ እንደሚፈልግ በተለያየ አጋጣሚ አሳይቷል። ያጣነው፣ የጎደለን፣ በየቦታው ብልጭ ድርግም የሚለውን ትግል አቀነባብሮ ወደ ድል ጎዳና የሚመሩን፣ አቅጣጫውን የሚያመለክቱን፣ የሃገርን ጉዳይ ከፓርቲ ፖለቲካ ባሻገር ማየት የሚችሉ፣ ሆደ ሰፊና በሁሉም ማእዘን የሚከሰቱትን ችግሮች
ወገናዊ ሳይሆኑ፣ ለጋራ የሃገራችን ጥቅም፣ ጉልበታችንን፣ ገንዘባችንን፣ አመራራችንን በአንድ ማዕከል (የሁሉም ድርጅታዊ ህልውና እንደተጠበቀ ሆኖ) አዋቅረው የሚያስተባብሩንን ነው። ማን ትክክል ነበር? የትኛው ድርጅት ነበር የበደለው? …. ወዘተ በሚል እሰጥ እገባ፣ ሕዝብ ሊወስን የሚገባው፣ የታሪክ ፀሃፊዎችንና የዳኞችን ሥራ ከወዲሁ እየተሻማን፣ በየቀኑ ሥራ ፈተን ጊዜያችንን
ይበልጥ ወደሚከፋፍለንና ወደሚበትነን ተግባር ከመስራት አልተቆጠብንም። የሚያስተባብሩን፣ የሚመክሩን፣ የሚያስተምሩን መሪዎች ማውጣት አቅቶናል። አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ ድርጅቶች ዘወትር ሲፋተጉ የሚውሉት ከሌሎች ተቃዋሚ ድርጅቶች የተሻሉ መሆናቸውን ለማስመስከርና ሌላውን ለማሳጣት ነው። ብዙ ጊዜ ራሣችንን በብረት ከገደብነው ቅጥ ያጣ ድርጅታዊ ፍቅር፤
ጎሳዊ ፍቅር፣ አጥር ሰብረን በጋራ ችግሮቻችን ዙርያ ማተኮር አልቻልንም፣ ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራት ሃገራችን የሁላችንም ናት፣ በዘመን አመጣሹ የጎሳ ፖለቲካ የጎሪጥ እንድንተያይ የሚገፉን ጎጠኞች፣ በማር ለውሰው ሊግቱን የሚፈልጉትን መርዝ መቀበል የለብንም፣ በሃገሪቷ የሚኖሩትን ሁሉንም ሕዝብ በእኩልነት ማክበር፤ ማፍቀር ያስፈልጋል፣ የወያኔ የጎሳ ፖለቲካ እየተቃወምን፣
እራሳችን በጎሳ የምናስብ፤ በዘር የምንቃኝ፣ ከሆነ፣ “ከኛ ውጪ ያለውን” እያልን የምናሰላ ከሆንን እኛም ዘረኞች መሆናችንን አንርሳ። የሚጮህላቸው ድርጀት የሌላቸው ስማቸው የማይታወቅ ድምጻቸው የማይሰማ አስታዋሽ የሌላቸው እልፍ አእላፍ ዜጎቻችን በየስርቻው ሲገደሉ፣ ሲሰቃዩ ሲታሰሩ የፖለቲካ ድርጅት መሪ ስላልሆኑ አስታዋሽ ፓርቲ ስለሌላቸው የትም ተረስተው መከራቸውን
ሲገፉ ይኖራሉ። እነሱም ዜጎቻችን ስለሆኑ እንታገልላቸው እንሰለፍላቸው፣ በዘረኛ ተገንጥይ ድርጅቶችና በሕዝባችን መካከል ልዩነቱ እየተምታታ፣ ከፊሉን ሕዝባችንን በጥርጣሬ የምትመለከቱ ካላችሁ እናንተም ከወያኔ ስለማትሻሉ፣ በሽታው ከራሳችሁ አልፎ ሌላውን ሳትበክሉ እራሳችሁን በጊዜ ብታስተካክሉ ይበጃችኋል። ዘረኝነት በየጓዳው እየተራባ ነው፣ በሃይማኖት፣በልማት፣በእቁብ፣
ዕድር ሰፈሮች እያንዣበቡ ስናይ፣ ኢትዮጵያዊነታችን እየተሸረሸረ መሆኑን ማወቅ አለብን። በቸልታ ልናልፈው የማይገባ፣ የጎሳው ቫየረስ symptomµ µስለሆነ በሽታው እንዳይራባ ወይ አሰተምሩዋቸው እምቢ ካሉ አግልሉዋቸው ።
ወደድንም ጠላንም አንድ ጎሳ፣ወይም ጥቂት ድርጅቶች ብቻ ተሰባስበው የሃገራችንን ችግር ለፈቱ እንደማይችሉ እያየን ነው፡፡ኢትዮጵያዊነትን እስከተቀበሉና ሃገራዊ የአንድነት ራዕይ ኖርዋቸው ሊያስተባብሩን የሚሞክሩ፣ የሁሉም ድርጀት መሪዎች፣ መሪዎቻችን ናቸው፤ ልንደግፋቸው፣ ልናበረታታቸው፣ አይዟችሁ ልንላቸው ይገባል። ሲያጠፉም እንደ ጣኦት ሊመለኩ
ሲከጃጅላቸውም፣ ሰው መሆናቸውን ሳንረሳ፣ ሊሳሳቱ፣ ሊወቀሱ እንደሚችሉ መርሳት የለብንም።
ዛሬ መለስ እንደ የኮርያው kimµ ilµ sungµ እንደ ጣኦት መመለክ ዳር ዳር ብሎት ሕጻናትን መዝሙር እያዘመረ እራሱን እንደሚሸነግለው፣ ትላት ፀሀዩ ንጉሳችን ተብሎ፣ መልከ ኅይለ ሥላሤ እንደ ገብርኤል፣ ሚካኤል፣ የፀሎት መፅሃፍ ሲጻፍላቸው፤ ወይም ከቆራጡ መሪያችን መንግስቱ ኅይለማርያም ጋር ወደፊት ተብሎ፣ አሥር ሜትር ጣቃ መፈክር ሰው የሚለብሰው ቸግሮት በየአደባባዩ ሲያንጠለጥል፣ ከማን አንሼ ብሎ ምስሉን ከሌኒን፣ ማርክስ፣ ኤንግልስ ጎን ሲሰቅል፣ ከሁሉ የምናየው አንድ አይነት በሽታ፣ ነው ፥ የበሽታውን ዝርዝር ተፅፎ ስለማያልቅ፣ የአንባገነኖች ቅሌት ወደ ሲልጣን አወጣጥና አወዳደቅ፣ ብላችሁ ጉግል ወስጥ ገብታችሁ አንብቡ፡፡ እንደሙሴ ዘመን፣ ጣኦት አምላኪዎችና፣ ጣኦት ቀራጮች እንዳንሆንና፣ እንደኛው ሰው ለሆኑት መሪዎች፣
በጀሌነት ብቻ ተሰልፈን ጧት ማታ የራሳችንን አንጎል አቀዝቅዘን ፤ በነሱ አእምሮ ብቻ ያምናስብ ከሆነ፣ ሲሳሳቱ የማንወቅሳቸው፣ የማንመክራቸው ከሆነ፣ እየሸንግልናቸው ነው አንወዳቸውም ለት ነው። የህዝባችንንም ሆነ የራሳችንን የመከራ እድሜ የምናበዛውም፤ የምናሳጥረውም እኛው ነን። በትግሉ ውስብስብነትም ሆነ በዕድሜ መግፋት፣ ከጊዜው ጋር አብሮ ማዝገም ከቸገረ፣ የበባቡሩ ጉዞ በጣም ከፈጠነብን፣ ነገ ሊተኩን፣ ትግሉን ሊቀጥሉ፣ ሊያስቅጥሉ ለሚችሉ አዳዲስ መሪዎች መንገዱን ልንለቅላቸው ይገባል። በራሳቸውም ሃይል ትግሉ የወለዳቸው ሊያግዙን፣ ሊረዱን፣ እኛ ያላየነውን ሊነግሩን የሚቀርቡትን የወደፊት ወጣት መሪዎችን፣ እንቅፋት ሆነን መተላለፍያውን አናጨልምባቸው፣ ገና ብቅ ሲሉ ቀንድ ቀንዳቸውን እየመታን ልናሳቅቃቸው አይገባም። የትኛወም ትውልድ የራሱን መሪ የራሱን ጀግና ይዞ፣ ከራሱ መፍትሄ ጋር ሲወጣ ሊበረታታ፣ ሊደገፍ ይገባል እንጂ እንዲሸማቀቅ ማድረግ አይገባም። እኛ ሞክረን ባቃተን መንገድ፣ እኛ ባበላሸነው ጎዳና ደግመው እንዲጓዙ ተጽእኖ ማሳደር የለብንም። ወጣቶቹም ቢሆኑ ብዙ የዳበረ ተመክሮ፣ ከታላቆቻቸው ስህተት ሊማሩ፣ ልምድ ሊቅስሙ እንድሚችሉ ሁሉ፣ ሁለቱም አንዱ ከሌላው የሚማሯቸው ብዙ ቁም ነገሮች እንዳሉ ተገንዝበው ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈው ለውድ ሃገራቸው መታገል አለባቸው። አለዚያ እንደሙሴ ዘመን ሃጢያተኞች መንገዱ ጨልሞብን የትግል አዙሪት ውስጥ እየተሽከረከርን እዚሁ ዕድሜያችንን እንዳንጨርስ። በተለይ አውሮፓ አሜሪካ፣ ባጠቃላይ ውጪ ሃገር የምንኖር ይህን ትግል ለማስተባበር ሰፊ ዕድል እያላቸው፣ በግለሰቦችና ድርጅቶች፣ ትምክህት፣ ኢጎ፣ ማናለብኝነት፣ ትግሉ ወደፊት መግፋት አቅቶት እንደተፋዘዘን ነው። ጎበዝ፣ እንዲህ የጎሳ ድርጅቶች የታጠቁም ያልታጠቁም እንደ አሽን በፈሉበት ዘመን፣ በኢትዮጵያ አንድነት እንኳን የሚያምኑት መቀራረብና በተወሰኑ ጉዳዮች ዙርያ እንኳ መስማማት
ባልቻሉበትና፣ ባንፃሩ በሚናቆሩበት ወቅት፣ ወያኔ በራሱ ቀውስ እንኳን ቢወድቅ፣ ይሄን ሁሉ ችግር ይዘን ሃገር ውስጥ ብንገባ፣ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ገምቱ እንጂ !! ጎበዝ የቅርብ ችግራችን እንኳን ከጀመረ ወደ አርባ ዓመት ሊጠጋ ነው፣ ብዙ ታጋዮች ወንድም
እህቶቻችን አልፈዋል፣ የዛ ትውልድ አባሎችም በጤናም ሆነ በእርጅና የቀረን ጊዜ በጣም አጭር ነው። ሓገር ውስጥም ወገኖቻችን በተለያዩ አምባገነኖች በረሃብ፣ በበሽታ፣ ጦርነት እያለቁ ነው።
መሪዎቹም ካላፈው ስለማይማሩ፣ ተጎትተው ተዋርደው ወደ እስር፣ ወይ ወደ ስደት እስከሚጓዙ ሃገራችንን እይጎዱብን ሕዝባችንን እያዋረዱት ነው ። ያለን ምርጫ ሁለት ብቻ ነው። ወይ ቢያንስ ለፉት አርባ ዓመታት የተጓዝንባቸው አሉታዊ መንገዶች እንደማያዋጣን አምነን ተቀብለን ባዲስ መንገድና ባዲስ መንፈስ በወያኔ መቃብር ላይ ወደፊት ልንመሰርት በምንፈልገው ስርዓት መሪዎቻችን የጋራ ብሔራዊ ሰነድ አዘጋጅተው ተማምነው ትግሉን አቀናጅተው በጋራ ወያኔን መግፋት፤ ወይም ይህን መቀበል ካልፈለግን እንደ ሙሴ ዘመን እርግማን እርስ በርስ ወያኔ በሚሰጠን አጀንዳና፣ የወያኔ በተቃዋሚ ስም ተከፋፍለውን በሚያራኩቱን Professional provocators በሚነደው እሳት ላይ ቤንዚን ጠብ እያደረጉ፣ እኛም እያራገብን እርስ በእርስ እየተቦጫጨቅን የምንሰራውን ሳናውቅ መንገዳችን ጠፍቶብን ሕዝባችንን እያስጨረስን ማልቅ ነው፡ ምርጫው የራሳችን ነውና ሳይረፍድ በጊዜ
እንዘጋጅ።

“እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃታል” አምላክ በራሱ መንገድ ሓገራችንና ሕዝባችንን ከከባድ አደጋ እየጠበቀ ነው፣ ሥራውንም አቁሞ አያውቅም እየሰራ ነው ስንል፣ ምን ማለት እንደሆነ ለመርዳት አስተርጓሚ አንፈልግ !!! እንደሙሴ ዘመን፣ የኛም ትውልድ ሞተን እንድናልቅ ተፈርዶብን፣ መንገዱን አጨልሞብን እንዲሁ እየተናከስን ሳንውቀው እያልቅን ይሆን? ወይስ እስራኤላውያንን በተደጋጋሚ ንሰሃ ገብተው ይቅር እንዳላቸው፣ እኛንም ካለፈው ተምረን ከጎሳና፣ ከድርጅት ጣኦት አምልኮት ውጥተን ወደ ህሊናችን ተመልሰን፣ በኢትዮጵያዊነት በጋራ ተደጋግፈን ሃገራችንን፣ ሕዝባችንና፣ እራሳችንን እንድንረዳ እስከምንወስን እየጠበቀ ይሆን? መልሱን ለናንተው ልተወው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ሲያግዝ፣ እኛም እንተባበረው !!
ለጽሁፉ ለአስተያየት: [email protected]__