የሐዋሳ ምእመናን የደረሰውን በደል በማስረጃ አቀረቡ፤ አጣሪው ተልዕኮውን ፈጽሞ ተመልሷል
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 25/2010፤ ጥቅምት 15/2003 ዓ.ም):- የሐዋሳ ምእመናን የደረሰውን በደልና ጥፋት የሚያሳይ ባለ 73 ገጽ የጽሑፍ ማስረጃ እና 6 የድምጽ እና የምስል (Audio and Video) ችግሩን ለማጣራት ወደ ቦታው ላቀናው ልዑክ አቀረቡ። አቤቱታ አቅራቢዎቹ ያቀረቡት ማስረጃ በደምሳሳው ሲታይ በሀ/ስብከቱ እና በልዩ ልዩ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተፈጽሟል የሚሉትን የገንዘብ ምዝበራ የሚያሳይ፣ በየዐውደ ምሕረቱ ስለተፈፀሙ አባቶችን የማዋረድና የማንኳሰስ ተግባራት፤ ስለተፈፀሙ የሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጥሰቶች ወዘተ የሚያትት ነው።
የአጣሪ ኮሚቴው አባላት ዝርዝሩን ከሰሙ በኋላ “እንዲህ ዓይነት ነገር ገጥሞን አያውቅም፤ ለመናገር የከበደ፣ የሚያሳፍር” መሆኑን ተናግረዋል ተብሏል። ጉዳዩን ለመከታተል የገቡ የክልሉ የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ደግሞ “የሰማነው ነገር የከበደ ያስቸገረ ነገር ነው። የተወሳሰበ ወንጀል ነው የተፈፀመው” ማለታቸው ተሰምቷል።
በወቅቱ የተከሳሾቹ ቡድን አባል ዲ/ን ያሬድ አደመ በቀረበባቸው ማስረጃዎች ከመደንገጡ የተነሣ “ቤተ ክህነቱን እናውቀዋለን። እንዲህ ማስረጃ ማጠናቀር አይችልበትም። እንዲህ የሚያደርገው ማ/ቅዱሳን ነው። ዐውደ ምሕረቱን ማንም አይከለክለኝም። ነገ እቆምበታለሁ” ሲል ተሰምቷል።