በዋካ ከተማ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ መርተዋል በሚል የሃሰት ክስ አንድ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ አባት ከሀላፊነታቸው መባረራቸው ተዘገበ። ባለፉት 2 ቀናት ብቻ ከ80 በላይ ሰላማዊ ሰዎችም ታስረዋል
በአካባቢው ያለውን ጭቆና፣ የመልካም አስተዳዳርና የፍትህ መታጣት በመቃወም እራሱን በእሳት በማጋየት ተቃውሞን የገለጠው የመምህር የኔሰው ገብሬ አስደንጋጭ ዜና የህዝቡ የመነጋገሪያ አጀንዳ በሆነበት ማግስት፣ የአካባቢው ባለስልጣናት፣ “ተቃውሞውን የሚያስተባብሩት በከተማው የሚገኘው የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካህን ናቸው” በሚል ሰበብ፣ የቤተክርስቲያኑዋን አስተዳዳሪ የሆኑትን በኩረ ትጉሀን ይልማ መኮንንን ከሃላፊነታቸው ማባረራቸውን ኢሳት ከትናንትና በስቲያ የዜና እወጃው ዘግቦአል።
እንደ ኢሳት ዘገባ የእገዳውን ደብዳቤ የጻፉት የዞኑ የአገረስብከት ሀላፊ የሆኑት መምህር ወንዶሰን ክፍሌ ሲሆኑ፣ ለበኩረ ትጉሀኑ ከሀላፊነት መነሳት ምክንያት አድርገው ያቀረቡት “ሀይማኖትን ምክንያት በማድረግ መንግስትና ህዝብ እንዲጋጩ አድርገዋል” የሚል ነው።
በቁጥር ዳ/ ካሲ/ 322/ 2004፣ በቀን 24-02-2004 ለበኩረ ትጉሀን ይልማ መኮንን ከስራ እና ከደሞዝ መታገዳቸውን ስለማሳወቅ በሚል ርእስ በተጻፈው ደብዳቤ የሚከተለው ይዘት ሰፍሯል።
“ግለሰቡ በመንግስታዊ ወይም ፖለቲካ አሰራር ጣልቃ ከመግባታቸውም በተጨማሪ ጉዳዩን ሀይማኖታዊ ሽፋን በመስጠት ህዝቡን እና ቤተክርስቲያንን ከመንግስት ጋር ለማጋጨት ከፍተኛ ጥረት ከማድረጋቸውም በላይ የአንድ ሀይማኖት መሪ የሆነ ሰው የአካባቢውን ሰላምና አንድነትን የማስጠበቅ ሀላፊነቱን ወደ ጎን በመተው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የአገሪቱን ሰላምን፣ ጸጥታን እንዲሁም የልማት አጋር በመሆን የነበራትን መልካም ስም እና ዝናን በአካባቢው ጥላሸት እንዲቀባ አድርገዋል፣ ስለሆነም ይህን ጉዳይ እጅግ ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጠው በመሆኑ ሀይማኖታዊ ፖለቲካ ስለማይኖረን አገረስብከቱ አስፈላጊውን ማጣሪያ አድርጎ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ድረስ ከቀን 24-02-2004 ጀምሮ ከስራ ሀላፊነት ከማንኛውም አገልግሎትና ከደሞዝ የታገዱ መሆናቸውን እያስታወቅን የንብረት ርክክብ በቦታው ላለው ካህን እንዲፈጸም ሆኖ ከዛሬ ጀምሮ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እንዳይወክሉ ለሁሉም አካላት በጥብቅ እናስታውቃለን”
እገዳውን ተከትሎ የአካባቢው ፖሊስ ባለፈው እሁድ ወደ ቤተክርስቲያኑዋ በመሄድ መምህር ይልማ ንብረት እንዲያስረክቡ ሲጠይቁ፣ ህዝቡ “መንግስት በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ምን አገባው”፣ የሚል ጥያቄ እንዳነሳና በጽኑ እንደተቃወመው ኢሳት የዘገበ ሲሆን አቶ ተፈራ ታደሰ የተባሉ አማኝ ጥቅምት 14 ከቤተክርስቲያኒቱ ግቢ በፖሊስ ታፍነው ሲወሰዱ ምንም ተቃውሞ ያላሰሙ የአካባቢው ሃላፊዎች ቤተክርስቲያኑዋ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ለፖለቲካ አላማቸው ማራመጃ የ እምነት አባቶችን ማጥቃት መጀመራቸው ክፉኛ እንዳስቆጣቸው እናም በዚህም ምክንያት ተቃውሞ ማሰማታቸውን ገልጾአል።
ወያኔ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ ለፈጣሪያቸው ሳይሆን ለመለስ ዜናዊ አገዛዝ ታማኝ የሆኑትን የፖለቲካ ወገናዊነት ያላቸውን ሰዎች በመሾም ህብረተሰቡ በአምልኮ ቦታ እንዲወዛገብና እንዲጋጪ ሲያደርግ እንደነበረ በተከታታይ ሲዘገብ የነበረ መሆኑ ይታወቃል። ለዘመናት አብሮ የኖረውን የክርስትናና የሙስሊም እምነት ተከታዮችን እርስ በርስ ለማጫረስ በተለያዩ ቦታዎች ሲፈጸም ከኖረው ተንኮል በተጨማሪ በቅርቡ ሙስሊም ህብረተሰብ ለሁለት ጎራ በመክፈል በመካከላቸው ግጭት እንዲነሳ ለማድረግ የወያኔ ሹሞች በግልጽ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸው መዘገቡ ይታወሳል።