በስዊዘርላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በትናንትናው ዕለት ህዳር 4 ቀን ጄኔቫ በሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጽቤት ፊት ለፊት ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በዘጎች ላይ እየፈጸመ ያለውን ሰቆቃና እንግልት በአስቸኳይ እንዲያቆም አለም አቀፍ ጫና እንዲፈጠርበት ጠይቀዋል።

የታሰሩ ፖለቲካ እስረኞችን ፎቶግራፎችና የተለያዩ መፈክሮችን ይዞ የወጡት እነዚህ ኢትዮጵያዊያን ሰልፈኞች፤ ወያኔ በሽብርተኝነት እየፈረጀ ያሰራቸው የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፤ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ጋዜጠኞች የዲሞክራሲ ለውጥ እርበኞች እንጂ በሽብርና ጦርነት ሥልጣን የተቆጣጠረው ወያኔ በሽብርተኝነት ስለፈረጃቸው ብቻ ሽብርተኞች ሊሆኑ የማይችሉ ናቸው ብለዋል። መለስ ዜናዊ ሽብርተኛ ነው ፤ መለስ ዜናዊ ገዳይ ነው፤ መለስ ዜናዊ ያሰራቸውን የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ይልቀቅ ፤ ሞት ለመለስ ዜናዊ የሚሉ መፈክሮችን ሲያስተጋቡ ውለዋል።

በመጨረሻም የተባበሩት መንግሥታት በአገራችን ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን የስበአዊ መብት ጥሰትና የፖለቲካ አፈና በአግባቡ መርምሮ በወያኔ መሪዎች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቅ በአገራችን ውስጥ እየተፈጸመ ነው ያሉትን ወንጀሎች ዝርዝር የሚያስረዳ ጽሁፍ በማስገባት ሰላማዊ ሰልፉ ተጠናቆአል።

የሰላማዊ ሰልፉ አዘጋጆች ወያኔ ያሰራቸውን የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እስኪለቅና ከህዝብ የቀማውን ሥልጣን እስኪያስረክብ ተቃውሞአቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቆአል።