አቡጊዳ – አቶ አሳምነዉ ብረሃኑ እና አቶ ዘመኑ ሞላ ተፈቱ !

በሽብር ተግባር ተሰማርታችኋል በሚል ክስ ከነ አቶ አንዱዋለም ጋር ታስረዉ የነበሩ አቶ ዘመነ ሞላ እና አቶ አሳምነዉ ብረሃኑ ፣ ትላንት ማክሰኞ ኖቬምበር 15 ቀን የተፈቱ ሲሆን፣ አቶ ደበበ እሸቱና አቶ ስለሺ ሃጎስ ደግሞ፣ ዓርብ ኖቬምበር 11 ቀን እንደተፈቱ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያለመክታል።

እነዚህ ወገኖች በምን ምክንያት እንደተፈቱ ለጊዜዉ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ገዢዉ ፓርቲ በሽብር ተግባር ተሰማርታችኋል እያለ ዜጎችን የሚያስረዉን ድርጊቱን ለማሳመን የሚረዳዉ መረጃ ብዙ እንደሌለዉና፣ ካለዉም ደግሞ ያሉት መረጃዎች በጣም የሳሱ መሆናቸዉን የሚያሳይ እንደሆነ የደረሰን ዘገባ አክሎ ያትታል።

በዛሬዉ እለትም ደግሞ አቶ አንዱዋለም አራጌ፣ አቶ እስክንድር ነጋ እና አቶ ናትናዔል ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፣ ሌላ ቀጠሮ ለሚቀጥለዉ እሮብ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ችለናል። ሶስቱም ጠበቃ ያቁሙ ሲሆን የተመሰረተባቸዉን ክስ ለመከላከል የተዘጋጁ እንደሆነም የደረሰን ዜና ያትታል።

በምንም አይነትና መልኩ ለሰላም ከመቆምና ከመታገል ዉጭ በሌላ አንዳችም ተግባር ላይ ያልተሰማሩ፣ በሰላማዊ ትግል አርበኝነታቸዉ የሚታወቁት እነዚህ ወገኖች፣ ከዚህ በፊት በሚጽፏቸዉ ጽሁፎች፣ ባደረጓቸዉ ንግግሮች ሁሉ ይህን ሰላማዊ አቋማቸዉን የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ያታወቃል።

የፍትህ ሚኒስቴር በነአቶ አንዱዋለም ላይ የግንቦት ሰባት አባላት ናችሁ፣ የኤርትራን መንግስት ታገለግላላችሁ በሚል የክህደትና የስለላ ክስ ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል።