ቆሜ ነው እምሞተው !! አሥራደው (ከፈረንሳይ)
አልጠብቅም ሞትን ተኝቼ ባልጋዬ ፤
እኔው እሄዳልለሁ ፈረሴን ቼ ! ብዬ ፤
በ’ንባ አልታጠብም ቁጭ ብዬ አላለቅስም ፤
ጉልበቴን አጥፌ አልንበረከክም ፤
አልጠብቅም እሱን ወደኔ እስቲመጣ ፤
እኔው እሄዳለሁ ወደሱ እንዳይመጣ ፤
ኩራቴን ይረዳው ድፍረቴን ይወቀው ፤
ተጋድሜ አልሞትም ቆሜነው እምሞተው !!
አልፈልግም ዋሻ የምደበቅበት ፤
አያሻኝም ጢሻ የምሸሸግበት ፤
አልሰብርም አንገቴን አላዞርም ፊቴን ፤
አይዝልም ጉልበቴ አላጥፈውም ክንዴን ፤
እጠብቀዋለሁ ደረቴን ነፍቼ ፤
በኩራት በድፍረት ጋሻዬን መክቼ ፤
አልንበረከክም ቆሜነው እምሞተው ፤
የጀግና ልጅ ጀግና መሆኔን ይወቀው !!
አልጠብቅም ሞትን ማታ በጨለማ ፤
እንዲወስደኝ ብዬ ሰው ሳያይ ሳይሰማ ፤
አለምንም ከቶ ዛሬን እንዲተወኝ ፤
ዘግይቶ እንዲመጣ ዕድሜ እንዲለግሰኝ ፤
ያልጋ ቁራኛ አርጎ እያጨማለቀ፤
ሞት መጥቶ እስቲወስደኝ እያመናጨቀ ::
ጭራሹን !
እጠብቀዋለሁ በጠራራ ፀሐይ ፤
መሃላዬ ይሁን ቃል ለምድር ለሰማይ ፤
ቆሜነው እምሞተው እንደ ክርስቶስ
ዳግም ድል አድርጌ እስክነሳ ድረስ ::
ይጥልልኝ ብዬ ትርፍራፊ እድሜ ፤
አልጠብቅም ሞትን እኔ ተጋድሜ ፤
እሄዳለሁ እኔ ወደሱ እንዳይመጣ ፤
ግንባሬን አላጥፍም የመጣው ቢመጣ ፤
ተኝቼ አልጠብቅም ሞት መጥቶ እስቲወስደኝ ፤
እኔው እሄዳለሁ በቁሜ እንዲያገኘኝ ፤
ለመኖር ጓጉቼ አልንበረከክም ፤
ዛሬን ተወኝ ብዬ አልለማመጥም ፤
አልንበረከክም ቆሜነው እምሞተው ፤
የጀግና ልጅ ጀግና መሆኔን ይወቀው !!
አንድ ቀን
ለወጣት መምህር የኔሰው ገብሬ :
እንዲሁም ፤
የአገራቸውን ውድቀት፤ የወገናቸውን ድቀት፤ እንቢ በማለት : ለእኩልነት፤ ለአንድነት፤ ለዲሞክራሲና ለፍትህ መከበር በመታገል ለወደቁ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በሙሉ መታሰቢያ ትሁንልኝ ::
To Remember the young Ethiopian Teacher Yenesew Gebré and Ethiopian Martyrs of June and November 2005.