ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎች ‹‹አልተመረቃችሁም›› ተባሉ

ምዕራፍ ብርሃኔ | ሪፖርተር

በክረምት የትምህርት ክፍለ ጊዜ ለአራት ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. የተመረቁ ተማሪዎች፣ ጊዜያዊ ዲግሪያቸውን ለመውሰድ ሲጠይቁ፣ ‹‹አልተመረቃችሁም›› በመባላቸው ቅሬታ እያሰሙ ነው፡፡ እንዳልተመረቁ የተነገራቸው ተማሪዎቹ የእንግሊዝኛን ቋንቋ ዓብይ፣ የኦሮሚኛን ቋንቋን ደግሞ ንዑስ በማድረግ ለአራት ዓመታት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፣ አልተመረቃችሁም የተባሉበት ምክንያት ‹‹Survey of Oromo Language›› ‹‹አንድ ኮርስ (ትምህርት) አልወሰዳችሁም›› በሚል እንደሆነ ተማሪዎቹ ገልጸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሥነ ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ ኃይለ ማርያም ከበደ በደብዳቤ ቁጥር DELE/187/2002 የዩኒቨርሲቲው የሥነ ትምህርት ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዲን ለዶ/ር ጂሉ ኡመር በላኩት ደብዳቤ እንደገለጹት፣ የኦሮሚኛ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ‹Survey of Oromo Language› የሚባለውን ትምህርት የቀነሰ በመሆኑ፣ ተማሪዎቹ ለመመረቅ የሚያስችለውን የ26 ‹‹ክሬዲት ሃወር›› ዓቢይ ኮርስ፣ የ12 ‹‹ክሬዲት ሃወር›› ንዑስ ኮርስና የ30 ‹‹ክሬዲት ሃወር›› መደበኛ ኮርሶችን በመውሰድ ባጠቃላይ 68 ‹‹ክሬዲት ሃወር›› በመውሰዳቸው ተማሪዎቹ መመረቅ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡

ዶ/ር ጂሉ መስከረም 4 ቀን 2003 ዓ.ም. ለዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ክፍል ዳይሬክተር ለዶ/ር ሮማን ጥሩነህ በላኩት ደብዳቤ መሠረት፣ ተማሪዎቹ ባለመማራቸው አይመረቁም የተባለው ትምህርት በ‹‹Oromo Literacy geners›› በሚባለው ትምህርት ውስጥ ተጠቃሎ እንደተሰጣቸውና ተማሪዎቹ መመረቅ እንደሚችሉ ጠቅሰዋል፡፡

‹‹በዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ውስጥ የመናበብ ጉድለት በመኖሩ እስካሁን ድረስ መፍትሔ አላገኘንም፡፡ ትምህርቱን እንኳን እንውሰድ ብንል ከዩኒቨርሲቲው የትምህርት አገልግሎት ለማግኘት ቢያንስ የስድስት ‹‹ክሬዲት ሃወር›› ኮርስ መውሰድ እንዳለብን ተነገርሮናል፤›› ያሉት ተመራቂዎች፣ ኮርሱን ብቻውን መውሰድ እንደማይቻላቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹ዩኒቨርሲቲው ባለው የአሠራር ጉድለት ምክንያት ለአራት ዓመታት የደከምንበት የልፋታችን ውጤት ከንቱ ሊሆን ነው፤›› ያሉት ተመራቂዎቹ፣ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ስታንዳርድ ክፍል ጉዳዩን እየተከታተለው ነው ብለዋል፡፡