የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አባላት ሃገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የረጂም ጊዜ ግንኙነት እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በቸልታ እንድንመለከት የሚያደርገን አይሆንም አሉ

የጀርመን ፓርላማ ምክር ቤት አባላት በቅርቡ በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ 09.11.2011 በሰጡት መግለጫ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላት የረጂም ጊዜ ግንኙነት በአገሪቱ እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እያየን ዝም እንድንል የሚያደርገን አይደለም አሉ።

በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጉብኝት ያደረጉት የሊበራል ፓርቲ ተወካዩዋ ወይዘሮ ማርቲና ሹስተር  በጉብኝታቸው ወቅት ያስተዋሉትን እውነታ ሲገልጹ “ህግ ይፈቅድልኛል እያሉ አንድን ሰው ያለወንጀሉ በዘፈቀደ ማሰር ፈጽሞ አይቻልም” ያሉ ሲሆን የኢትዮጵያው አገዛዝ አዲስ ባወጣው የፀረ-ሽብር ህግ ሽፋን ከመንግስት የተለየ አስተሣሰብ የሚያራምዱና  በስርዓቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ሁሉ በግፍ እያሰረ ነው ብለዋል።

“በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ነገር እኛን ሊበራሎቹን እጅግ ያሣስበናል”ያሉት ወይዘሮ ሹስተር፤ በአገሪቷ ለጋዜጠኞች፣ ለተቃዋሚዎችና ለኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ያለው ነፃነት ወደ ፊት ከመሄድ ይልቅ፤ ወደ ሁዋላ ተመልሶ ቀጭጮ ቀርቷል በማለት ተቃዋሚዎችና ጋዜጠኞች በህግ ሽፋን እየታሰሩ መሆናቸውን እንዳረጋገጡ አመልክተዋል።

ወይዘሮ ማርቲና ሹስተር “ማስፈራራት በአገሪቷ ላይ ነግሷል። ያነጋገርኳቸው የተቃዋሚ ፓርቲ ድርጅቶች ሌላው ቀርቶ የሚገናኙበትና የሚሰባሰቡበት እንኳ ቢሮ የላቸውም። የመንቀሳቀሻ ገንዘብና የመገናኛ መስመርም እንደዚሁ የላቸውም። ከሁሉም በላይ መንግስት እየሰራ ስላለው ሥራ ለመጠየቅ፣ለመወያየትና ለመነጋገር ምንም ዓይነት ዕድልና መንገድ የላቸውም” ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ህግ ከሌሎች አገሮች የፀረ-ሽብር ህግ የተለየ እንደሆነ የጠቆሙት ተወካዩዋ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር ታስቦ የወጣውም ህግ  እንዲሁ በአገሪቱ ዲሞክራሲን ለማስፈን የሚደረግን ሙከራ የሚያደናቅፍ እንደሆነ ለህዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባላቱ ገልጸዋል።

በመጨረሻም ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር የጠበቀ የንግድ ግንኙነት እንዳላት ይታወቃል። ነገር ግን “ከኢትዮጵያ ጋር የቆየ ግንኙነት ስላለን ብቻ፤በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝን አስመልክቶ እየተፈፀመ ያለውን ነገር ችላ የምንለው አይደለም”ሲሉም አባላቱ ተናግረዋል።

አፋኙና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ እጅግ በርካታ ለሃገር ተቆርቁአሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን፣ ጋዜጠኞችንና አክቲቪስቶችን እንዲሁም የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አካላትን ሽብርተኞች ናችሁ፣ የሽብርተኛ ቡድን ደጋፊዎች ናችሁ በማለት ወደ እስርቤት ማጎሩ በስፋት መዘገቡ ይታወሳል።