በቢሊየኖች የሚቆጠር ሃብት ባለቤት ለመሆን የበቃው የወያኔ ኩባንያ ኤፈርት፤ የሙስና እናት እየተባለች በምትጠራው አዜእብ መስፍን ሙሉ ቁጥጥር ስር መውደቁ ተዘገበ

ወያኔ በትግራይ ህዝብ ሥም ባቋቋመውና ለጥቂት የህወሃት ባለሥልጣኖች እንደግል ንብረት እያገለገለ ያለው የ ኤፈርት ኩባንያ  ስራ አስኪያጅ አባዲ ዘሙ ከሥራ አስኪያጅነቱ ተነስቶ ድርጅቱ ሙሉ በሙሉ  በዘረኛው ቡድን ቁንጮ መለስ ዜናዊ ባለቤት  አዜብ መስፍን እጅ  መውደቁ ተዘገበ።

አዲስ ቮይስ በመባል የሚታወቀው የመረጃ አውታር እንደዘገበው፤ በህወሓት ውስጥ ረጅም ዓመታት ቁልፍ ቦታዎችን ይዞ ሲያገለግል የቆየውና የአምባገነኑ መለስ ዜናዊ ታማኝ የነበረው የኤፈርት ሊቀመንበር አባዲ ዘሙ ከኃላፊነቱ ተነስቶ “የሱዳን አምባሳደር” ተብሎወደ ካርቱም የተላከ ሲሆን አባዲ ዘሙ ከኃሊፊነቱ የተነሳበት ዋናው ምክንያት የሙስና እናት ተብላ ከምትጠራው አዜብ መስፍን ጋር ባለው ከፍተኛ አለመግባባት መሆኑ ታውቁአል።

በበርካታ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ሃብትና ንብረት በሚያንቀሳቅሰው ኤፈርት፣ የአባዲ ምክትል ሆና በባለቤቷ መለስ ዜናዊ የተሾመቺው  አዜብ መስፍን፤ ሙሉ ኃሊፊነቱን ተረክባ የድርጅቱን ሪፖርት ስታቀርብ መሰንበቷንና አባዲ ዘሙም ለስሙ ያህል በሥራ አስኪያጅነት መደቡ መቆየቱ፤  የሚታወቅ ነው።

ህወሓት አዲስ አበባ ሲገባ የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበረው አባዲ ዘሙ፤ ከዚያም ወደ ትግራይ ክልል ተዛውሮ የክልሉ ም/ፕሬዚዳንት ሆኖ ሲሰራ የቆየ ሲሆን ከዚህም ባሻገር ከኤፈርት ሊቀመንበርነቱ በተጓዳኝ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ሆኖ አገልግሎአል። ይሁን እንጂ ካለፈው የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ድርጅታዊ ምርጫ በኋላ፤ ከክልል ተወካዮች ም/ቤት ተመራጭነቱ እንዲነሳ መደረጉ ይታወሳል።

ከሕወሓት ክፍፍል በኋላ በድርጅቱ ውስጥ ከቀሩት የህወሓት  አመራር አካላት መካከል የመለስ ቁልፍና ታማኝ የነበረው  አባዲ ዘሙ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ  ከሙስና እናት አዜብ ጋር የፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ  በውለታ ቢሱ መለስ- ፊት ተነስቶ እንደነበር ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በህገወጥ መንገድ መቆጣጠሩ እና ከህግ በላይ መሆኑ በስፋት የሚታማው ኤፈርት ሙሉ በሙሉ በአምባገነኑ መለስና በባለቤቱ ቁጥጥር ስር የመውደቁ ጉዳይ፤ በእነ  ስብሃት ነጋና በርካታ የሕወሓት ባለስልጣናት ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ መፍጠሩ ይሰማል። በሕወሓት ባለስልጣናት መካከል መቃቃርና ክፍፍል እየሰፋ መምጣቱንም፤ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።

የሙስና እናት የሆነቺው አዜብ መስፍን በህወሀት ማዕከላዊና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት፣ በወያኔ ኢህአዴግ ማዕከላዊና ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት፣በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት፣ በምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢነት፣በብሔራዊ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የቦርድ ሰብሳቢነት፣ በኢፈርት ሥራ አስኪያጅነትና በሌሎች በርካታ የስልጣንና የሹመት ቦታዎች ተመድባ ያለች ያለችሎታዋና አቅሟ ድርብርብ ሥልጣን ተሰጥቶአት የአገሪቱን ሃብት እየቦጠቦጠች ያለች የዘመናችን ጉድ ሴት ነች።