የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተቀማጭ ገንዘብ ቀውስ ጫፍ ላይ መሆኑ ታወቀ

በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተቀማጭ ገንዘብ ቀውስ ጫፍ ላይ እንደሚገኝ ለአገዛዙ ቅርብ የሆነው ሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ አመልክቷል።

ባንኩ በተቀማጭ ከያዘው 57 ቢሊዮን ብር ውስጥ ዘጠና በመቶ በላይ የሚሆነውን በብድር መስጠቱ እና ከዛም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የተበደሩት የመንግስት ተቋማት እንደሆኑ ዘገባው አሳይቷል። የወያኔ አገዛዝ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ተብዬውን እቅድ ይዞ በተነሳበት እና ከምንም ጊዜ በላይ ገንዘብ በገፍ በሚሻበት አመት ከፊት ለፊቱ የተጋፈጠውን ቀውስ የተረዳው ባንክ ችግሩን ለመቅረፍ እየጣረ እንደሆነም ታውቋል።

ከዚህም አኳያ 83 ቅርንጫፎችን እየከፈተ እና ሰራተኞቹም እስከ እቁብና እድር በመውረድ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱ የማግባባት ስራ እንዲሰሩ መርሃግብር አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የወያኔ አገዛዝ በማህበር የተደራጁ ተቋማት ተንቀሳቃሽም ሆነ የማይንቀሳቀስ ገንዘባቸውን በንግድ ባንክ በኩል ብቻ እንዲያንቀሳቅሱ የሚል መመሪያ በነሐሴ ወር መጨረሻ 2002 ማስተላለፉን ባለፈው ወር መዘገባችን ይታወሳል።

ጉዳዩን በሚመለከት ካናገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ የሪፖርተር ዘገባ ንግድ ባንክ በቀውስ ዳርቻ ላይ እንደሚገኝ አመላካች ነው ብለዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ ባንኩ በሚሰጣቸው ብድር ላይ የሚመረኮዙት ሴክተሮችም እንደዛው ቀውስ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ አስረድተዋል።