ሼክ ሙሃመድ አላሙዲ የቀን ሰራተኞችን ከውጭ አገራት ወደ ኢትዮጵያ እያስመጣ መሆኑ ተዘገበ

በትውልድ ኢትዮጵያዊ እና በዜግነት ሳውዲ የሆነው ቢሊየነር ሼክ ሙሃመድ አላሙዲ ከፊሊፒንስ አገር የቀን ሰራተኞች ማስመጣቱን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት – ኢሳት – ዘግቧል።

ኢሳት የአዲስ አበባ ዘጋቢውን ጠቅሶ እንደዘገበው ሰራተኞቹ በመዲናይቱ በሚገኘው እና አራዳ ጊዮርጊስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ስራ ጀምረዋል። ፊሊፒናውያኑ ሰራተኞች የመድህን ሽፋን እና ከፍተኛ የውሎ አበል፤ እንዲሁም መኖሪያ ቤት እንደተሰጣቸው የገለጸው ዘገባ፤ በሁኔታው የተበሳጩ የአዲስ አበባ ወጣቶች በአንዳንዶቹ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ተስተውለዋል ብሏል።

ቀን ሰራተኞችን ከውጭ ማስመጣት ለምን እንዳስፈለገው በሸገር ሬድዮ የተጠየቀው አላሙዲ “የኢትዮጵያ ወጣቶች ሰነፎች ናቸው” የሚል መልስ መስጠቱንም የኢሳት ዘገባ ገልጿል።

ኢትዮጵያ በአለም ላይ ከፍተኛ የስራ አጦች ቁጥር ካሏቸው አገራት ተርታ የምትመደብ ሲሆን፤ በ15 እና በ30 አመት እድሜ መሃል ካሉት የከተማ ወጣቶች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ስራ አጦች እንደሆኑ አንዳንድ ጥናቶች ይጠቅሳሉ።

ሼክ ሙሃመድ አላሙዲ የዘረኛው ስርአት ደጋፊ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ወያኔ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃንን ገድሎ እና በአስር ሺሆች የሚቆጠሩን ባሰረ ማግስት አምስት ሚሊዮን ብር ለገዢው ቡድን በስጦታ ማበርከቱ ይታወሳል።