በአዲሱ የወያኔ ካቢኔ እውነተኛው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብርሃነ ገብረክርስቶስ ነው ተባለ
ዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ በግንቦት 15 2002 የምርጫ ተውኔት አካሄዶ 99.6 በመቶ ማሸነፉን ካወጀ በኋላ፤ ባላፈው ወር አዲስ ካቢኔ እንዳዋቀረ ይታወሳል።
ባለፉት ሃያ አመታት ቁልፍ የስልጣን መቀመጫዎችን በትግራይ ተወላጆች እጅ አኑሮ የቆየው ዘረኛ ስርአት፤ የሌላ ብሔር ሰዎችን ለይስሙላ ለሃላፊነት ቦታዎች በመሾም፣ ከስራቸው ግን ፈላጭ ቆራጭነቱን የሚይዙ የትግራይ ተወላጆችን የማስቀመጥ ልምድ እንዳለው፤ እነዚህ ሰዎችም “ታኮ” በሚል ቅጽል ስም በማህበረሰቡ ዘንድ እንደሚጠሩ ይታወቃል።
በአዲሱ የመለስ ካቢኔ ውስጥ ወያኔ ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረውን ስዩም መስፍንን ተክቷል የተባለው የደቡብ ክልሉ ደሳለኝ ሃይለማሪያም እንደሆነ ተዘግቦ ነበር። ይሁን እንጂ፥ ማክሰኞ እለት ይፋ የተደረገው የሚኒስቴር ዲኤታዎች ዝርዝር እንዳሳየው፤ የህወሃቱ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ከደሳለኝ ስር ተመድቧል።
ብርሃነ ገብረክርስቶስ በአሁኑ ሰዓት በብራሰልስ ቤልጂየም የወያኔ ኤምባሲ ሃላፊ ሲሆን፤ ከዛ ቀደም በአሜሪካ በተመሳሳይ ሁኔታ ዘረኛውን ስርአት አገልግሏል። የመለስ ዜናዊ የቅርብ ሰው እንደሆነ የሚነገርለት ግለሰብ፣ በአምባሳደርነት ስም ውጭ አገራት በቆየባቸው አመታት እውነተኛ ስራው የገዢውን ቡድን ገንዘብ በአለም አቀፍ ደረጃ ማንቀሳቀስ እንደሆነ ለወያኔ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ይገልጻሉ።
የብርሃነን መሾም አስመልክቶ የዝግጅት ክፍላችን ያናገራቸው አስተያየት ሰጪዎች፣ በመጪው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ እውነተኛው ስልጣን የሱ እንደሚሆን ጥርጥር የለም ባዮች ናቸው።