“ነፃ የሚያወጣኝ መድረክ ነው መሰለኝ”
“ኦነግን ሳላውቅ የኦነግ አባል የሆንኩ መሰለኝ” የሚለውን ቃል የተናገሩት ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት በፊት አንድ ዩኒቨርስቲ መምህር ናቸው፡፡ በ1994 ዓ.ም ክረምት ላይ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊና አቶ ተፈራ ዋልዋ የከፍተኛ ትምህረት ተቋም መምህራንን ረዘም ላሉቀናት ያወያዩ ነበር፡፡ አንድ የዩኒቨርስቲ መምህር የኢህአዴግን የፍረጃ ፖሊሲ መግለጽ
ሲሉ የተጠቀሙበት ቃል ነበር፡፡ “እኔ የማንም ድርጅት አባል አይደለሁም፡፡” አሉ መምህሩ ሲናገሩ “የማንም ድርጅት አባል ለመሆን እቅድም የለኝም፡፡ ሐሳቤን በነፃነት እሰጣለሁ፡፡
የማላምንበት ነገር በነፃነት እከራከራለሁ፡፡ ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ብቻ በመሆኔ የኢህአዴግ አባላት “የኦነግ አባል የኦነግ አባል! እያሉ አሉኝ፡፡ ኦነግን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንጂ በቅርብ አላውቀውም፡፡ ኦነግ የእኔን ሐሳብ የሚያራምድ ድርጅት ነው? ብዬ እንዳስብ እድርጐኛል፡፡ ኦነግን ሳላውቀው የኦነግ አባል ሆንኩኝ እያልኩ አሰላስላለሁ” በማለት ጠ/ሚኒስትሩ ባሉበት መናገራቸውን አስታውሳለሁ፡፡
ዛሬ ይህ ትዝ ያለኝ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ስም እየተሰጣቸው ተከሰው በነፃ ስለሚወጡ ሰዎች ሳስብና እንዲሁም ጐንደር ላይ የገጠመኝ አንድ ገጠመኝ ትዝ ብሎኝ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሥልጣን እንደያዘ አካባቢ አምርረው ኢህአዴግን የተቃወሙ ደርግ ኢሠፓ ቀይ ሽብር እየተባሉ ወህኒ ወረዱ፡፡ በአንድ ወቅት ደግሞ መአህድ ሌላ ጊዜ ሌላ ስም እየተሰጠ ይታሰራሉ፡፡ አልፎ አልፎ የህሊና ዳኛ ሲገጥማቸውም በነጻ ሲለቀቁ እሰማለሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ ጊዜው መድረክ ሆኖአል፡፡ በአንድ ወቅት ደቡብ ጐንደር ደብረታቦር ከተማ የሰማሁትን ገጠመኝ ላካፍላችሁ፡፡
ከአካባቢው ገጠራማ ቦታ የመጡ አንድ አርሶ አደር አግኝቼ ተግባባንና ጫወታ ጀመርን፡፡ ስለ ወቅቱ ዝናብ፣ ስለሰብሉ፣ ስለማዳበሪያው ዋጋ ሌላው ሌላውንም አንስተን በመጨረሻው ወደ ፖለቲካው ገባን፡፡
“ካድሬው አላስቀምጥ አላሰራ አለን፡፡ “አዲሱ እረኛ ከብትም አያስተኛ” እንደሚባለው አንዱን አውርደው አንዱ
ሲሾም ጥዋት ማታ ሰብስባ ወሬ ጭቅጭቅ ነው፡፡ የተስፋ ወሬ ነው፡፡ የማዳበሪያው ዋጋ ሰማይ ወጣ ምንም የሚበጀን ነገር አላገኘንም፡፡ ቅንጅት ይመጣል ብለን ስንጠብቅ በዚያው ቀረ፡ ሰሞኑን ደግሞ መድረክ እየተባለ ነው፡፡ ምናልባት እንግዲህ መድረክ ነፃ ያወጣን እንደሆነ በተስፋ እየጠበቅን ነው፡፡
አሉኝ እኔም ተገርሜ መድረክ እዚህ አለ እንዴ? አልኳቸው “ኽረ የለም” ሲሉ መለሱልኝ፡፡ ለእናንተ የሚበጅ ወይም
የማይበጅ መሆኑን እንዴት አወቃችሁ አልኳቸው “ወያኔ ራሷ ትነግረናለች” አሉኝ፡፡ እንዴት አልኳቸው “ወያኔ ከመጣችበት ዘመን ጀምሮ የተረፈን ወሬዋ እና ውሸቷ ነው፡፡ የተረፈን፡፡ ያገኘነው፡፡ ድህነትና ውርደት ነው፡፡ ሁሉም ነገር ተወደደ፤ ገንዘብ አምጡ አምጡ ነው፡፡ ሰለቸን፤ የሚያሽንፋቸውና ለእኛ የሚበጀን ድርጅት ብቅ ሲል ሬዲዮኑም ካድሬውም ጥዋት ማታ ስም እየጠራ ይሳደባል፡፡ ተጠንቀቁ መጣባችሁ! ሊያጠፋችሁ ነው! እያለ እንደ ልጅ ሊያታልለን ይሞክራል ቅንጅት በነበረ ወቅት ቅንጅትን አውሬ አስመስሎ ሲነገረን ነበር፡ ኋላ ላይ ስንሰማ እንዲያ የጠሉት የእኛን ጥያቄ ስለሚያነሳ ነው አሉ፡፡ አሁን ደግሞ መድረክን እያሉን ነው፡፡ ታዲያ እኛም
ሰማን ሰማንና ጐበዝ ይኽ መድረክ የሚሉት ደግሞ እኛን ነፃ የሚያወጣን ይሆናል ብለን አመንን፡፡ ለዚህ ነው መድረክ ጥሩ ነው ያልኩህ” ሲሉ አጫወቱኝ፡፡ “እነሱ ከጠሉት የእኛ ነው ማለት ነው፡፡” ሲሉ በለሆሳስ ነገሩኝ፡፡