በነአንዱዋለም ላይ ስለቀረቡት ክሶች – ግርማ ካሳ
ኅዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ የፍትህ ሚኒስቴር፣ ለልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት በ26 ተከሳሾች ላይ ወደ ስድስት የሚደርሱ ክሶችን በይፋ ጥቅምት ሰላሳ 2004 ዓ.ም አቅርቧል።
የፍትህ ሚኒስቴር ከከሰሳቸዉ 26 ተከሳሾች መካከል፣ በአንደኛ ተከሳሽነት የተጠቀሱት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ አንዱዋለም አራጌ፣ በስምንተኛ ተከሳሽነት የተጠቀሱት አንጋፋዉ ጋዜጠኛ አቶ እስክንድር ነጋ ጨምሮ ስምንት በአገር ቤት የሚኖር ኢትዮጵያዉያን ሲሆኑ፣ በ22ኛ ተከሳሽነት የተጠቀሱት፣ የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የሶሊዳሪቲ ንቅናቄ አመራር አባል የሆኑትና በኢትዮጵያውያን መካከል ፍቅር መግባባትንና ሰላምን በመስበክ የሚታወቁትን አቶ ኦባንግ ሜቶን ጨምሮ በአሥራ ስድስት በሚሆኑ በዉጭ አገር በሚኖሩ ወገኖች ላይ ክስን መስርቷል።
አቃቢ ሕግ ያቀረበዉ ክሶሽ ላነበበ ምን ያህል የሕግ መዛባት እንዳለ ከማየት ባሻገር፣ በአገራችን ያለዉ የሕግ ስርዓት ምን ያህል የዘቀጠና በ19ኛዉ ክፍለ ዘመን እንደነበረዉ አይነት የሕግ ሥርዓት ዉስጥ እየኖርን እንዳለ የሚያሳይ ነዉ። ምን ያህል የሰዉ ልጅ የማይከበርበት አገር እንዳለን በድጋሚ ያረጋገጠ ነዉ።
አቃቢ ሕግ በስፋት ግንቦት ሰባት ስለተባለዉ ድርጅትና ስለ ኤርትራ መንግስት ይናገራል። ክስ የመሰረተባቸዉ ተከሳቾሽ ከሞላ ጎደል የተከሰሱት ከኤርትራ መንግስት ጋር ግንኙነት አላቸዉ፣ ሕገ መንግስቱንም በአመጽ/በኃይል ለመናድ ይሞክራሉ በሚል ነዉ።
አህያዉን ፈርቶ ዳዉላዉን እንደሚባለዉ፣ የኢሕአዴግ መንግስት በኤርትራ መንግስት ላይ ምንም አይነት እርምጃ ሳይወስድ፣ የኤርትራን መንግስት ሽብርተኛ የሚል ስያሜ በፓርላማ እንዲሰጠዉ ሳያደርግ፣ ዜጎችን ከኤርትራ ጋር ሆናችሁ ብሎ መክሰስ የሚያስተዛዝብ ነዉ።
አንባቢያን ምን ያህል ኢሕአዴግ ሕግን መቀለጃ እያደረገ እንደሆነ ይረዱ ዘንድ ከተከሳሾች መከካል አቶ አንዱዋለም አራጌን አቶ እስክንደር ነጋን እና አቶ ኦባንግ ሜቶን ላይ የቀረበዉን ክስ እንደ ምሳሌ ለመጥቀስ እሞክራለሁ።
ከነዚህ ከሶስት ኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ ጋር ጥሩ አግባብ አለኝ። የፖለቲካ እምነታቸዉ እኔ ብዙ ለማራምደዉ የፖለቲካ እምነት ጋር የተገናኘ ነዉ። እግዚአብሄርን የሚፈሩ፣ የፍቅርና የሰላም ሰዎች ናቸዉ። ድሃዉ ሲጠቃ አይነተዉ ዝም ማለት የማይወዱ፣ ለፍትህ የቆሙ፣ ተመችቷቸዉ የግል ኑሯቸዉን መኖር ሲችሉ ለአገርና ለሕዝብ ቀና ደፋ የሚሉ ኢትዮጵያዉን የሚወዱ በጣም የማከብራቸዉን የምወዳቸዉ ወንድሞቼ ናቸዉ። መለስ ብለን የጻፉትንና የተናገሩት ብናጠናና ብንመረምር አንዳችም ጊዜ ክፉ ቃላት፣ የአመጽ ንግግሮች ሲወጣቸው አናይም። እንዴት ተደረጎ ከመረብ በስተሰሜን እየኖሩ ያሉ ወገኖቻችን እያስጨነቀና እያረዳ ካለዉ ፣ ከአምባገነኑ የኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ጋር ሊያገናኟቸው እንደቻሉ ሊገባኝ የማይችል ፍጹም እንቆቅልሽ የሆነና በጣም የሚያሳቅ ጉዳይ ነዉ።እነዚህን የሰላም አርበኞች ከሃዲዎች፣ የኤርትራ ሰላዮች፣ መሰረቱ በዉጭ አገር የሆነዉና በዚያም ስብሰባዎች ከማድረግ አልፎ በማያወቀዉ፣ በዉጭ አገር ካሉ ለሰላሳ አርባ አመታት አለን ከሚሉ ከነኢሕአፓ. መኢሶን ከመሳሰሉ በምን የማይለየዉ፣ የግንቦት ሰባት ድርጅት አባል ናቸዉ ብሎ መክሰስ እራስን የሚያስገምት አሊያህም ሕዝብን መናቅ ነዉ።
በርግጥ እነዚህ ሰዎች እንደ ሽብርተኛ ተቆጥረዉ የሚታዩ ከሆነ እንግዲያዉስ ግርማ ካሳን 27 ኛ ተከሳሽ አደርጎ ኢሕአዴግ ክስ ሊመሰረት ይችላል። ፍቅርን ማስተማር፣ ሰላምን መስበክ፣ ኢትዮጵያዊነት ማወጅ ወንጀል ከሆነ እንግዲያወስ እኔም ወንጀለኛ ነኝ።
አቶ አንዱዋለም የተከሰሱትበት የመጀመሪያዉ ክስ
1ኛ ተከሳሽ አንዱዋለም አራጌ በአገር ዉስጥ ሕገ-መንግስታዊ የመደራጀት መብቱን እንደ ሽፋን በመጠቀም፣ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሽብር ድርጊት ለማፍረስ የአሸባሪዉ የግንቦት 7 የአገር ዉስጥ የሽብር ቡድኑ የወጣቶች አደረጃጀት ሃላፊ በመሆን ኤርትራ ከሚገኘዉ የሽብር ቡድኑ ወኪሎችና በተለያዩ ዉጭ አገራት ካሉት የዚህ አሸባሪ ቡድን አመራሮች ጋር ሕቡእ ግንኙነት በማድረግ፣ የሽብር ተለእኮ በመቀበል በአገር ዉስጥ በሕቡእ ከተደራጀዉ የሽብር ቡድን በማቀናጀትና የጋራ በሽብር የተደገፈ ሁሉን አቀፍ ትግል የማድረግ ጥምረት እንዲፈጥሩ ያደረገ፣ የሽብር እቅዶች በመንደፍ በአገር ዉስጥ ሕቡእ የወጣቶች ቡድን እንዲደራጅ ያደረገ፣ የታቀደዉን ሽብር በቀጥታ የመራ፣ ለሽብር ሥራ ሰዎችን ያሰማራ፣ በተለያዩ ዜዴዎች የተለያዩ የቅስቀሳ ጽሁፎችን ያሰራጨ፣ የሚላኩለትን የሽብር አመጽ የቅስቀሳ ጽሁፎችን እየተቀበለ በአገር ዉስጥ ላሉት አባላቱ ያደረሰ፣ የሽብር አላማ ያላቸው ስብሰባዎች የመራና የተለያዩ የሽብር ቅስቀሳዎች በማድረግ፣ ዉሳኔዎችን ያስተላለፈ በመሆኑ
አቶ አንዱዋለም የተከሰሱበት ሁለተኛው ክስ
1ኛ ተከሳሽ የአሸባሪዉ ግንቦት 7 የአገር ዉስጥ የሽብር ቡድኑ የወጣቶች አደረጃጀት ኃላፊ በመሆኑ
አቶ እክስንደር የተከሰሱበት የመጀመሪያዉ ክስ 1፡
7ኛ ተከሳሽ እስክንድር ነጋ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ሕገ-መንግስታዊ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን እንደ ሽፋን በመጠቀም ጊዜው ተለይቶ በዉል ባልታወቀ ሕገ-መንግስቱንና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን በተደራጀ የሽብር ድርጊት ለማፍረስ የአሸባሪዉ ግንቦት 7 አመራሮች ጋር ሕቡእ ግንኙነት በማድረግና የአገር ዉስጥ ወኪል በመሆን የሽብር ተልእኮ በመቀበል በአገር ዉስጥ በሕቡእ ከተደራጀዉ የሽብር ቡድን አባላት ጋር በመተባበር የሽብር እቅዶች በመንደፍ የታቀደዉን ሽብር በቀጥታ ዉጪና አገር ዉስጥ ከሚገኙት የሽብር ቡድኑ አባላት ጋር ሆኖ ያስተባባእረ፣ የሽብር ሁከት ጥሪ ያስተላለፈ፣ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የተለያዩ የቅስቀሳ ጽሁፎችን ያሰራጨ፣ መረጃዎች በመሰብሰብ አሳልፎ በቀጥታ ለግንቦት 7 በተዘዋዋሪ መልኩ ጠላት ለሆነዉ ለኤርትራ መንግስትና ሌሎች አሸባሪዎችና ድርጅቶች እንዲደርስ ያደረገ፣
አቶ ኦባንግ የተከሰሱበት የመጀመሪያዉ ክስ 1፡
22ኛ ተከሳሽ አቶ ኦባንግ ሜቶ የአሸባሪዉ የግንቦት 7 ድርጅት አመራርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን እንዲሁም በአገር ዉስጥ ከሚገኙት አባላት ጋር ህቡእ የሆነ ግንኙነት በመፍጠር የተለያዩ አመጽን የሚቀሰቅሱ ሰነዶችንና ጽሁፎችን ወደ ሃገር ዉስጥ ዓመጽን የሚቀሰቅሱ ጽሁፎችን በኢሜል በማሰራጨት የሽብር ድርጊቱን የመራ በመሆኑ
አቶ አንዱዋለም ፣ አቶ እክስንደር፣ አቶ ኦባንግ ጨምሮ ሁሉልም ተከሳሾች የተከሰሱበት አራተኛዉ ክስ
ተከሳሹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ኢትዮጵያ ሆነዉ ሳለ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ከሚያደርገዉ የኤርትራ መንግስት እና ለኤርትራ መንግስት ጥቅም እዬራ ካለዉ የአሸባሪዉ የግንቦት 7 ጋር በመተባበር ከኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት ጋር በህቡእ በመገናኘትና የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵይ ላይ የሚያራምደዉን የማተረማመስ አጀንዳ ለማስፈጸም ለአሸባሪዎች በ1ኛ ክስ ላይ የተጠቀሰዉን የሽብር ስልጣና ተልእኮ በመስጠት ወደ አገር ዉስጥ በሕቡእ እንዲገቡ ያደረገ፣ ተከሳሾች ለኤርትራ መንግስት ጥቅም ከሚሰራዉ የአሸባሪዉ የግንቦት 7 ድርጅት አመራሮች ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሚስጥራዊ ግንኙነት በማድረግ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምደዉን የሽብርና የትርምስ አጀንዳ ለማስፈጸም በማቀድ በሃገር ዉስጥ ለአሸባሪ ድርጅት አባል በመመልመልና ወደ ኤርትራ በመላክ በ1ኛ ተከሳሽ በኤርትራ ወታደራዊ ባለስልጣናት አማካኝነት በ1ኛ ክስ የተገለጸዉ የሽብር ስልጠና እና እንዲወስዱ ያደረጉ በመሆኑ፣ በአጠቃላይ ተከሳሾች ከኤርትራ መንግስት ባለስልጣናት እና ከግንቦት ሰባት አመራሮች ጋር በሚስጥር በመገናኘት የኤርትራ መንግስት የሽብር አጀንዳዉን ለመፈጸም እንዲመቸዉና እንዲቀናጅ የረዱ በመሆኑ በፈጸሙት ከፍ ያለ ክህደት ወንጀል ተከሰዋል።
አቶ አንዱዋለም ፣ አቶ እክስንደር፣ አቶ ኦባንግ ጨምሮ ሁሉልም ተከሳሾች የተከሰሱበት አምስተኛዉ ክስ፡ከኢትዮጵያ ጋር በጦርነት ሁኔታ ላይ ካለዉና ጠላት ለሆነዉ ኤርትራ መንግስት እንዲሁም ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ለሚንቀሳቀሰዉ ለአሸባሪዉ የግንቦት ሰባት ጥቅምና በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ጉዳት በሚያደርስ ሁኔታ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ እና የወታደራዊ ስለላ ሥራ በማደራጀት መረጃዎችን ሰብስበዉ በማስተላለፍ ኤርትራ መንግስት እንዲቀንዉና እንዲመቸዉ ያደረጉ በመሆኑ በፈጸሙት የስለላ ወንጀል ትከሰዋል።