አሸባሪው የወያኔ አገዛዝ አሻንጉሊት ፍርድ ቤት፤ በሽብርተኝነት ስም የታሰሩ የስዊድን ጋዜጠኞችን ክስ ውድቅ ሲያደርግ በሁለቱ የኦብነግ አባላት ላይ መፍረዱ አገዛዙ ያለበትን ከፍተኛ ጭንቀት አመላካች ነው ተባለ
ከሁለቱ ስዊድናዊያን ጋራ በሽብርተኝነት ወንጀል ተጠርጥረው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በዋና ወንጀል አድራጊነት የተከሰሱት የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጪ ግንባር (ኦብነግ) አባላት የሆኑት አብዲወሊ መሐመድ እስማኤል እና ከሊፍ ዐሊ ዳሂር የ17 ዓመት ጽኑ እሥራት ሲፈረድባቸው የስዊድን ሃገር ጋዜጠኞች ክስ ግን በቂ መረጃ አልተገኘም በሚል የቀረበባቸው ክስ ውድቅ መሆኑ ታወቀ፡፡ በእለቱ የፍርድ ቤቱን ታዳሚዎች ያስገረመው ነገር የወያኔው አሻንጉሊት ፍርድ ቤት ዳኞች የፍርዱ ዓላማ ጥፋተኛውን ማስተማር፣ ኅብረተሰቡን እና አገርን ደግሞ ከጥቃት መከላከል በመኾኑ ወንጀሉን በመካከለኛ ደረጃ መድበነዋል ማለታቸው እንደሆነ ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ አመልክቱአል፡፡
አጭበርባሪው የወያኔ አገዛዝ እየሰራ ያለውን የማፊያ አይነት ተግባር አስመልክቶ አስተያየት እንዲሰጡት ዘጋቢያችን የጠየቃቸው የፍርድ ሂደቱን የተከታተሉ ሰዎች እንደገለጹት፣ ወያኔ ከምእራባዊያን ያለበትን አስፈሪ ጫና ላለመጋፈጥ ብሎም ደግሞ ፍርድ ቤቱ በስርአት እየተመራ ያለ ህጋዊ ፍርድ ቤት ነው እንዲባልለት በማሰብ የስዊድን ጋዜጠኞችን ክስ ውድቅ ሲያደርግ ንጹሃን አርብቶ አደር ዜጎችን ግን በግፍ እንዲህ አይነት ፍርድ እንዲሰጥባቸው አድርጉአል።
ወያኔ ሥልጣን ላይ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ የፖለቲካ ባላንጣዎቹን በፍትህ ሥም ከርቼሌ ለመወርወር እንዲያስችለው የራሱን የፖለቲካ ሪዮት የሚከተሉትንና በጥቅምና በሙስና ተባባሪ የሆኑትን ሰዎች ስቪል ሰርቪስ ኮለጅ እያስገባ አስመርቆ በዳኝነትና በአቃቤ ህግነት በመሾም ተመሳሳይ ግፍ በመፈጸም ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።