በቤልጂዬም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የኢድ-አልፈጥርን በዓል በደማቅ ሁኔታ አከበሩ። በበዓሉ ላይ ተጋብዘው የነበሩት በቤልጂዬም የወያኔ ኤምባሲ ሰራተኞች የግንቦት7 አመራር አባል ባለበት ቦታ መገኘት ያስጠይቀናል ሲሉ አዳራሹን ጥለው ፈረጠጡ

ዕሁድ ጥቅምት 26 ቀን ተከብሮ የዋለውን የኢድ-አልፈጥርን በዓል በቤልጂዬም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች አንድ ላይ በመሰባሰብ በደማቅ ሁኔታ ማክበራቸውን የግንቦት 7 ዘጋቢ ከስፍራው በላከልን ሪፖርት ገለጸ።

በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየአመቱ በደማቅ ሁኔታ በሚከበረው በዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ሥነሥርዓት ላይ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መካከል እልቂት ሊያስነሳ የሚችል ክፍፍል ሆን ብሎ እየፈጠረ መሆኑን በድምጽና በቪዲዮ ማስረጃ የተደገፈ ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦበታል።

በቤልጂዬም የሚገኘው የወያኔ ኤምባሲ በዚህ በአል አከባበር ላይ ተገኝቶ የሙሲሊሙ ህብረተሰብ የተሰማውን ቅሬታና ስጋት እንዲያዳምጥ በቤልጂዬም የሉቁማን ኢትዮጵያዊያንና ቤልጂየማዊያን ሙስሊሞች ማህበር ጋብዞት እንደነበረና በግብዣውም መሰረት ከኤምባሲው 3 ተወካዮች ተልከው የምሳ ግብዣው እስኪጠናቀቅ ድረስ በቦታው እንደነበሩ የደረሰን ዘገባ አመልክቶአል። ሆኖም የምሳ ሥነስረዓቱ አብቅቶ በበአሉ ላይ የተጋበዙት እንግዶችና ምዕመናን በተዘጋጀው አዳራሽ ውስጥ ቦታ ቦታቸውን መያዝ እንደጀመሩ በዓሉን ለማክበር በግል የተጋበዙት የግንቦት 7 አመራር አባል እስፍራው በመድረሳቸው 3ቱም የወያኔ ተላላኪዎች እርስ በርሳቸው በጆሮ ከተንሸኳሸኩ ቦኋላ አዳራሹን ለቀው እንደወጡ ለማወቅ ተችሎአል።

በአገሩ ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 7 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ይከሄዳል በተባለው በዚህ የኢድ አልፈጥር በአል ላይ ለመሳተፍ መጥቶ የነበረው የወያኔ ኤምባሲ ቡድን ዋናው የበዓሉ ዝግጅት ሊጀመር ሲል አዳራሹን ጥሎ በመውጣቱ የተገረመው ምዕመንና ግብዣ የተደርገላቸው እንግዶች ወደ ኋላ እንዳረጋገጡት፤ መንግሥታቸው ሽብርተኛ ብሎ ከፈረጃቸው ፓርቲ አመራር አባል ጋር በአንድ መድረክ መሳተፍ ሊይስጠይቃቸው እንደሚችል ስጋት ገጥሞአቸው ጥለው ለመውጣት እንደተገደዱ ለአስተባባሪዎቹ መግለጻቸውን ለመረዳት ተችሎአል።

የበአሉ አዘጋጅ ኮሚቴ የዕለቱ ዝግጅት ከታላላቆቹ የእስልምና ሃይማኖቶ የበአላት ቀናት አንዱ የሆነውን ኢድ አልፈጥርን በጋራ ከማክበር የተለየ ፖለቲካዊ ይዘት እንደሌለው በማስረዳት ልኡካን ቡድኑን ለማረጋጋት ቢሞከርም እንዳልተሳካ  የደረሰን ሪፖርት ያስረዳል።

በቦታው የተገኙት የንቅናቄያችን አመራር አባል ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት ወያኔ በራሳቸው እውቀትና ልምድ የሚተማመኑ ፤ በየትኛውም የመንግሥት ሥራ ዘርፍ ላይ ተሰማርተው የሚሰጡት አገልግሎት ለአገራቸውና ለወገናቸው ጥቅም መሆኑን በሚገባ ለመረዳት አቅም ያላቸው ባለሙያዎችን ሆን ብሎ አንድ ባንድ ካባረረ ቦኋላ በሚከፈላቸው ደመወዝና በተመቻቸላቸው የአገር ሃብት ዘረፋ ሂሊናቸውን አደንዝዘው የታዘዙትን ሁሉ ለመፈጸም ዝግጁ በሆኑ ዘመናዊ ሎሌዎች የተሞላ ድርጅት ለመሆኑ ይህ የብራስልሱ የወያኔ ኤምባሲ እርምጃ አሳይቶአል ብለዋል።