አቡጊዳ – ለሳካሮቭ ሽልማት ብርቱካን ከመጨረሻ ሶስት እጩዎች መካከል ተመረጠች

ኦክቶበር 18 ቀን 2010

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሳካሮቭ ሽልማት ከተመረጡት የመጨረሻ ሶስቱ መካከል እንደምትገኝ ተገለጸ። የሳካሮቭ ሽልማት ከኖቤል የሰላሙ ሽልማት ቀጥሎ በአዉሮፓ ሕብረት የሚሰጥ ትልቁ የሰላምና የሰብዓዊነት ሽልማት ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከበርካታ እጩዎች ዘጠኝ ብቻ ቀርተዉ እንደነበረ ይታወቃል።

ከዘጠኙ ዉስጥ ትገኝበት የነበረችዉ ወ/ት ብርቱካን፣ ቁጥሩ ከዘጠኝ ወደ ሶስት ሲቀነስም፣ ለሽልማት ሊበቁ ከሚችሉ ከሶስቱ የመጨረሻ እጩዎች መካከል መገኘቷ በራሱ፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለሰላማዊ ትግል ትልቅ ድል እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።

ከወ/ት ብርቱካን ጋር ለመጨረሻ እጩነት የቀረቡት ዚሌርሞ ፍሬናሶ የተባሉ የኩባ አምባገነን መንግስትን የሚቃወሙ የሳይኮሎጂ ምሁር አንደኛዉ ሲሆኑ፣ እሥራዕል በጋዛ ላይ የዘረጋችዉን እገዳ በመጣስ በዚያ ለሚገኙ ፍልስጤማዉያን መድሃኒትና ምግብ ለማመላለስ ከእሥራዕል ወታደሮች ጋር ግብግብ ፈጠሮ የነበረዉ «ብሬኪንግ ዘሳይለንስ» የሚባለዉ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሁለተኛዉ ነዉ።

የሽልማቱ አሸናፊዎች ከሶስት ቀናት በኋላ ኦክቶበር 21 ቀን ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። ወ/ት ብርቱካን ሚድቀሳ የዚህ ሽልማት አሸናፊ ከሆነች 50000 የእንግሊዝ ፓዉንድ ትቸለማለች። በስትራትስቡርግ በአካል ተገኝታ ንግግር የምታደርግ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት የሳካራቮ ተሸላዊ ከሆኑት ከነ ኔልሰን ማንዴላ ከአን ሳን ሱኪ ምድብ በይፋ መቀመጧንም የሚያረጋግጥ ይሆናል።

ከብርቱካን ጉዳይ ሳንወጣ ብዙ ጊዜ ከወያኔና ከአላሙዲ ጋር ይሰራል ተብሎ የሚተቸዉ የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያዉያን እግር ኳስ ፌደረሽን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን የክብር እንግዳዉ አደርጎ መምረጡን ኢትዮጵያ ሪቪዉ ዘገበ። ፌደረሽኑ ያለፈዉ አመት ሳን ሆዜ ካሊፎርኒያ በተደረገዉ የኢትዮጵያዉያን እግር ኳስ ዉድድር ወቅት ከብርቱካን ትፈታ ግብረ ኃይል ጋር በቅርበት የሰራ ሲሆን የብርቱካን ጉዳይ በተቻለ መጠን በሕዝብ ዘንድ እንዲታወቅ የበኩልን ድርሻ ያደርግ እንደነበረም ይታወቃል።

«ብርቱካን ሚደቅሳ እረፍት ላይ ናት። እረፍት ላይ ሆናም፣ ምንም ሳትናገርም ይኸዉ እየበጠበጠቻቸዉ ነዉ። እነርሱ ሊያዋርዷት፣ ቅስሟን ሊሰብሩ ሞከሩ። ነገር ግን እርሷ ዝም ብትልም፣ አለም ምላሽ ሰጣቸዉ። በዉጭ አገር የሚኖረዉ ኢትዮጵያዊ ምላሽ ሰጣቸዉ» ያሉን በሳካሮች ሽልማትና በፌደረሽኑ ዉሳኔ ዙሪያ ያነጋገርናቸዉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ብቻ ሳይሆን መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊደሰት እንደሚገባዉ አስረድተዋል።