ፓትርያርክ መርቆሬዎስ የት ነሁ? ብጹእ መልከ-ጼዴቅስ? ካምፓላም ታመመ፡ ታመሰ እኮ !! ተክለሚካኤል፡ አበበ፡ ቶሮንቶ

የዛሬ አስር ወር አካባቢ ለግል ጉዳይ ወደ ዩጋንዳ ተጉዤ ነበር። አንድ የፌብሩዋሪ 2011 የመጀመሪያ ሰንበት ጠዋት ወካምፓላ መካነሰላም መድሀኔዓለም ቤተክርስቲያን አመራሁ። ባጋጣሚ ከአገልግሎት በኋላ ምርጫ ነበርና አስመራጭ ኮሚቴ ምርጫ ሲያደርግ፡ ሪፖርት ሲቀርብና የሰዎች ስም ዝርዝር ቀርቦ፡ ሰዎቹ በቤቱ ሲጸድቁ ታዝቤያለሁ። በሰዓቱ፡ በገንዘብ ሪፖረት እንዲሁም በቀጣይ አመት በጀት ላይ ከተነሱ አንዳንድ ጥያቄዎች በስተቀር፡ ምርጫውን ተቃውሞ ምንም አይነት የሚያነታርክ ነገር ተነስቶ ሀሳብ ሲሰጥ ወይንም ሲከራከሩ አልተመለከትኩም። እነሆ ጉዳዬን ጨርሼ ወደሰሜን አሜሪካ ከተመለስኩ በኋላ ግን፡ ቤተክርስቲያኑ ውስጥ ብጥብጥ እንደተጀመረና፡ ሰዉ በሁለት ተቧድኖ እየተነታረከ እንደሆነ ሰማሁ። ችግሩ ምንድን ነው ስል፡ “የቀድሞው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስልጣን አናስረክብም ብሎ ነው” የሚል ነገር ሰማሁ። የአውሮፓና የአፍሪካው ሊቀ-ጳጳስ፡ ብጹእ አባታችን፡ አቡነ ኤልያስም ይሁኑ፡ ሕጋዊው የውጭ ሲኖዶስ፡ ችግሩን ባጭሩ መፍታት ሲችሉ፡ እንዲያውም ብጹእ አባታችን ባለማወቅ ጋዝ ቸልሰውበት ችግሩ ሲንከባለል፡ ሲንከባለል ቆይቶ፡ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ግን ወደባሰ ደረጃ አድጎ፡ ሰዎች እስከመታሰር፡ እስከመደባደብና፡ እስከመፈነካከት እንደደረሱ ሰማሁ።

ባለፈው ሳምንት፡ አንድ ሳሙኤል ጴጥሮስ የተባለ ሰው ሳልቀደም ልቅደም ይመስላል፡ ችግሩን ወያኔ የፈጠረው አስመስሎ የጻፈው ዘገባ ሀሰትና መሰረተ ቢስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። እንደኔ እንደኔ ከሆነ፡ ከዚህ ብጥብጥ ወያኔ ሊጠቀም የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም (ምክንያቱም፡ ስደተኛው ህብረተሰብ ለሁለት ይከፈላል፤ ይዳከማልና)፡ ችግሩን ወያኔ አልፈጠረውም። በችግሩ በሁለቱም በኩል ያሉት ሰዎች በወያኔነት የሚታሙ አይደሉምና ችግሩን በወያኔ እንደተፈጠረ አድርጎ የሚመጣው ሀሳብ እንደው ገና ለገና ሰዉን አስበርግጎ ጸጥ ለማሰኘት የተዘየደ ሴራ ነው። በወያኔ መጠርጠር ከመጣ ግን፡ ችግሩን በወያኔ እንደተፈጠረ አድርጎ የሚያስወራው ወገን ለዚያ ጥርጣሬ የተጋለጠ ነው። ምክንያቱም፡ ክብረአብ አንድነት የተባለ አንድ ጸሀፊ፡ የችግሩ አንድ ወገን ከሆኑት ወይዘሮ ወርቄ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ከዩጋንዳ በላከው ወረቀት መሰረት፡ የቤተክረስቲያኒቷ አንጋፋ መስራችና የአካባቢው ባለሀብት ባልቴት፡ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው፡ ከ2010-2011፡ አንድ አመት ቆይተው እንደመጡ ዘግቧል። እሳቸውም በአምቦ፡ በደብረ ዘይት መሬት ተሰጥቷቸው የመዝናኛና የመኖሪያ ቤቶች ገንብተው እንደመጡ በኩራት ሲናገሩ ተሰምቷል። ስለዚህ በዚህ ጭቅጭቅ ውስጥ፡ የባልቴቷ ወገኖች፡ አንደኛውን ወገን ወያኔ እንደገዛው መክሰስ ከጀመሩ፡ ለወያኔነት ክስ የተጋለጡት በሳቸው ወገን ያሉት ይሆናሉና፡ ይሄንን “ወያኔ ቤተክርስቲያኗን ሊወስድ” የሚለውን ክስ ቢተዉት ይሻላል።

ኢትዮጵያ ሄዶ የሚገነባ ወይንም መሬት የሚመራ፡ ወይንም ወደኢትዮጵያ የሚመላለስ ሁሉ የኢህአዴግ ደጋፊ ነው ወይንም የወያኔ ወገን ነው የሚለው ሀሳብ ደካማና ብላሽ ነው። እንደውም እኔ፡ አስገዳጅ ፖለቲካዊ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር፡ በውጭ የሚገኙ ሰዎች ከአገራቸው የሚርቁበትን ነገር አጥብቄ እቃወማለሁ። ያለለት፡ አገሪቱን ለሕወሀት/ኢህአዴግ በግላጭ ከሚተው፡ በአገሪቱ ውስጥ በተለያየ መልኩ፡ ሀብትም በማካበት መሳተፉን እደግፋለሁ። ምክንያቱም፡ ሁሉንም ነገር ለጠላት ለቀን ከወጣን እነሱ የሚፈልጉትን ነገር አደረግን፡ በዚህም አንጀታቸው ቅቤ ይጠጣል። ይሰታሉምና። ይሁን እንጂ፡ አሁን ባለው ሁኔታ፡ አንዱ አንድኛውን በወያኔነት መክሰስ ከጀመረ፡ በስደተኝነት ከሚኖሩት ይልቅ፡ በኢትዮጵያ መዋእለ ንዋያቸውን አፍስሰው የሚሰሩ ሰዎች ለወያኔ ሰለባነት የበለጠ የተጋለጡ ናቸው። ስለዚህ፡ ካንድ በስደተኛ ፓስፖርት ወይንም ወረቀት ከሚኖር ሰው ይልቅ፡ በኢትዮጵያ ፓስፖረት የሚንቀሳቀስና እንደልቡ ወደ ኢትዮጵያ ገባ ወጣ የሚል ኢትዮጵያዊ የበለጠ ወዳለው ስርአት የቀረበ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለኝ። እዚያ ውስጥ ከገባን ማለቴ ነው። ለስርአቱ ይቀርባል ባንልም እንኩዋን፡ ቢያንስ ባደባባይ ያንን ስርአት ተቃውሞ ለመቆም፡ የሰጠው አሻራውና የተከለው ንብረቱ ሊያግደው ይችላልና። ስለዚህ፡ በዚያ ካምፕ የሚገኝ ሰው ቀድሞ ሌሎችን በወያኔነት መክሰስ አግባብ አይደለም።

በኔ አመለካከት፡ ለጊዜው ዋንኛው ችግር፡ በሁለት ወያኔን አጥበቀው በሚጠሉ፡ ”ሀ” እና ”ለ” በተባሉ ቡድኖች መካከል ነው። “ሀ” ለረጅም ግዜ በቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ውስጥ ስለቆየ፡ ምናልባትም በሌሎችም ባልተጣሩ ተጨማሪ ምክንያቶች ለውጡን አልፈለገውም። “ለ” ደግሞ የለም የህዝብ ድምጽ ይከበርና፡ ስልጣን አስረክቡ ነው። ከዚያ፡ የታላቁ አባታችን፡ የብጹእ አቡነ ኤልያስ፡ የሁለቱንም ወገን ፍላጎት ያላገናዘበ ስህተት ታከለበት። ስለዚህ፡ የችግሩ መሰረት የመፍትሄውም ቁልፍ ያለው፡ በውጭ የሚገኙ የህጋዊው ሲኖዶስ አባቶቻችን ላይ ነው። ይሄ በዩጋንዳ የተከሰተው፡ የመጀመሪያም የመጨረሻም አይደለም። ከዩጋንዳ እስከ ካናዳ፡ ከቡታጅራ እስከ ቦምብ ተራ በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ህዝብ ይታመሳል፡ ያለቅሳል፡ ይከፋፈላል። ብኡአን ጳጳሳቱና ኤጲስ ቆጶሳቱ ግን፡ ህዝቡን ሊያጽናኑት፡ ሊመሩትም አልቻሉም። ባገር ውስጥም ካገር ውጪም ያለችው ቤተክርስቲያናችን ጉዳይ ያቃጠለው አንድ ወዳጄ፡ በቅርቡ “ሶስተኛ ፓትሪያርክ ያስፈልገን ይሆን እንዴ?” የሚል ጽሁፍ እያሰናዳ ሳለ ነው ይሄ የዩጋንዳ ጉዳይ የተከሰተው። በዩጋንዳ በተከሰተው ችግር ውስጥ፡ አንጋፋው አባታችን፡ አቡነ ኤልያስ በካምፓላ ትኬታቸውን ከፍሎ፡ ሆቴላቸወን ችሎ የሚያስተናግዳቸው ህዝብ እያለ፤ ከሩቅ በስማ በለው፡ ሁለቱንም ወገን ሳይሰሙ፡ “የለም ይሄንን ሾሜያለሁ፡ ይሄንን ሽሬያለሁ” ያሉት ነገር፡ ብዙዎችን እንዳስከፋ ነው መረጃዎቼ የሚጠቁሙት። ምርጫው አግባብ ካልሆነ፡ የለም ይሄ ስህተት አለው፡ ስለዚህ እንደገና ምርጫ አድርጉ ወይንም እስከዚህ ጊዜ ድረስ ቆዩ፡ እኔ እስክመጣ ማንም ምንም እንዳያደርግ ማለት ሲችሉ፡ በሩቁ አንዱን ወገን አስቀይሞ፡ አንዱን ወገን ባንዱ ላይ ድል እንዲጎናጸፍ የሚያደርግ አካሄድ መከተላቸው አግባብ አይደለም።

በዚህ በዩጋንዳው ጸብ ውስጥ፡ በኢትዮጵያ ፓስፖርት የሚንቀሳቀሱት ወ/ሮና ባለቤታቸውም ይሁኑ፡ በስደተኝነት በዩጋንዳ ወረቀት የሚኖሩት ሰዎች ቤተክርስቲያኑን በመገንባት፡ በማሳደግ፡ በመምራትና ከውጭው ሲኖዶስ ጋር ያለውን ትስስር ጠብቆ እንዲቆይ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ይሄ ቤተክርስቲያን እንዲገነባና ነጻነቱ እንዲጠበቅ፡ የእስልምናና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ሳይቀር ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ታሪኩ ይናገራል። ይሄ ቤተክርስቲያን ሲገነባና የቦታው የባለቤትነት መብት ማስረጃዎች ለአቡነ ኤልያስ ሲሰጡ፡ ብዙ ሰዎች፡ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን ገንዘባቸውን በዚህ ጉዳይ ላይ አፍስሰዋል። በወቅቱ በዚያ አካባቢ የነበረውና ይሄ ችግር ሊመጣ እንደሚችል ያኔም ተንብየው የነበሩት ዲባቶ ካሳ ከበደ አንዱ ህያው ምስክር ናቸው። ይሄንን ሁሉ የህዝብ ድካምና ፈተና የሚያውቁትና አደራ የተሰጣቸው አቡነ ኤልያስ ጉዳዩን መርምረው፡ ሲሆን ሲሆን አዚያው ተጉዘው መፍትሄ ማበጀት ሲችሉ፡ በርቀት ሆነው፡ “ብያለሁ ብያለሁ ተቀበሉ” ብለው፡ ብዙሀን ይመውኡ የሚለውን ህግ ጥሰው፡ ህዝብ ድምጽ የሰጠበትን ጉዳይ፡ ያለምንም አጥጋቢ ምክንያት መሻራቸው አግባብ አይደለም። ሕዝብ በህጋዊው ሲኖዶስ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ፡ እንዲያምጽም ይገፋፋል። በመሰረቱ፡ አቡነ ኤልያስም ይሁን የውጪው ሲኖዶስ በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ያላቸው ስልጣን የሚመነጨው ከህዝቡ ነው። ህዝቡ አዝኖና ተበሳጭቶ ወደሌላ አቅጣጫ እንዳይሄድ፡ ማድረግ ነው እንጂ፡ህዝብን የሚያሳዝን ውሳኔ መወሰን አግባብ አይደለም።

የኛ አባቶች፡ የሚያስታርቅና ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መንገድ እንጂ አንድ ወገን ብቻ እንዲያሸንፍ የሚያደርግ መንገድ ቢከተሉ መልካም ነው። በታላቅ ትህትናና አርምሞ የምናገረው፡ በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም ያሉት አባቶች የማስተውልባቸው ችግር፡ አንደኛ ህዝቡን አያደምጡም ወይንም በሕዝቡ አይተማመኑም። እንደውም ካንድ ጳጳስ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ስነጋገር፡ ህዝቡ “አመጸኛና ስርአተ አልበኛ ነው” ብለውኛል። ሁለተኛ፡ አባቶቻችን ፈሪዎች ሆነው ፈራ ተባ እያሉ ነው የሚመሩት። አሁንም ህዝቡን ሰምቶ ቢቻል አስታርቆ፡ አለበለዚያም ጉዳቱን በሚቀንስ መልኩ መወሰን ነው እነጂ፡ በሩቅ ሆኖ፡ “ህዝቡ አባታችን አረ ስለእግዚአብሄር፡ ተበደልን” እያለ፡ የብዙሀኑን ሀሳብ የሚጻረር ውሳኔ መወሰን፡ አግባብ አይደለም። ህጋዊው በውጭ የሚገኘው ሲኖዶስና ፓትሪያርክ ጽህፈት ቤት፡ ከቫንኩበር እስከ ዲሲ፡ ከዩጋንዳ እስከ ካናዳ፡ ከዴንቨር እስከ ኦሀዮ፡ ያለውን ችግር እየመረመረ፡ ሳይባባስና ችግሩ ሳይከፋ፡ ሰዉም ሳይቋሰል በፊት፡ ጠላትም ሳይበረታ፡ ውሻ በቀደደውም ጅብ ሳይገባ ችግሩን መፍታት ነው እንጂ፡ አንዱን አስደስቶ፡ ሌላውን አስቀይሞ፡ በሩቁ መወሰን አግባብ አይደለም።

በዚህ ወር የሚሰበሰበው ቅዱስ ሲኖዶስ (ተሰብስቦም እንደሁ አላውቅም፡ ምክንያቱም ስለሲኖዶሳችን እንቅስቃሴ ምንም አይነት ተከታታይ መረጃ የለንምና) ይሄንንና ሌሎች መሰል ችግሮችን ሊወስንባቸው ይገባል።