ጥቅምት 22 ቀን 1998 በአረመኔው የወያኔ አገዛዝ የተጨፈጨፉ ሰማዕታት ስድስተኛ አመት ተዘከረ

ድህረ ምርጫ 97 የሰጠነው የምርጫ ድምፃችን ይከበርልን በማለታቸው ልክ የዛሬ 6 አመት ጥቅምት 22 ቀን 1998 . በአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ጎዳናዎች ላይ በአረመኔው የወያኔ አገዛዝ አጋዚ ጥይት በግፍ የተጨፈጨፉ፤ አካሎቻቸውን ያጡ፤ የተደበደቡ እና የተጋዙት ሰማእታት ወገኖቻችን 6ኛ አመት በሚሊየኖች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ እየተዘከረ ነው።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በወርሃ ጥቅምት 1998 በንጹሃን ወገኖቻችን ላይ የፈጸመውን ያንን ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ ለማስታወስ የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው  አንድ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ አመራር አባል እንደገለጹት መለስ ዜናዊ የህዝብ ፈቃድ በመፈጸም ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር በአገራችን እንዲጀመር ባለመፈለጉ በወሰደው በዚያ ዘግናኝ አረመኔያዊ እርምጃ ምክንያት ተስፋ ተሰንጎበት የነበረው አገራችንን ወደተሻለ የአስተዳደር ምዕራፍ የመውሰድ ጥረት ተቀልብሶ ሁላችንም ከዜሮ ለመጀመር ወደሚከድበት የትግል መስመር ተፍተናል ብለዋል። በዚህም የተነሳ የአገራችንና የህዝባችን ደህንነት ብቻ ሳይሆን ሰላማዊውንና ዲሞክራሲያዊውን ጎዳና በመቀልበስ መለስ ዜናዊ ለራሱና ለቤተሰቦቹ ታላቅ አደጋን ከፊቱ ደቅኖአል በማለት በቅርቡ በቱኒዚያ፤ በግብጽ፤ በሊቢያና በተቀሩት የአረብ አገሮች እየተደርገ ያለውን ሁኔታ አመልክተዋል።

የዛሬ 6 አመት ከተፈጸመው ጭፍጨፋ ባልተናነሰ ወገኖቻችንን በፍርሃትና በሽብር እያርበደበደ እስከወዲያኛው ለመግዛት የሚያልመው መለስ ዜናዊ በአሁኑ ሰዓት አፍንጫው አጠገብ እየሆነ ያለውን አዳድስ ኩነቶች ተመልክቶ ወደሚያዋጣው ሰላማዊ መድረክ እራሱን ከመመለስ ይልቅ ዛሬም በዚያው ድንቁርናና እብሪት እየተመራ ነው ያሉት የአመራር አባል በደመወዝ ተቀጥሮ በሚያገለግል ከህዝብ አብራክ በወጣ ተመንጃ ተሸካሚ ተማምኖና ተኮፍሰው ንቀት ማሳየት ለሊቢያው ሙአመር ጋዳፊም እንዳልበጀው በአይናችን ተመልክተናል ብለዋል።

ከንቀታቸውና ከእብሪታቸው ብዛት የተነሳ ለውጥ ፈላጊ ሊቢያዊያንን “አይጦች፣ በረሮች፣ ሃሽሻሞች፣ ዱሪየዎች ወዘተ ሲሉ የነበሩት ሙአመር ጋዳፊን መጨረሻ የተመለከተ፤ መለስ ዜናዊ ከምርጫ 97 ጀምሮ እያሰማ ያለው ድንፋታና ዛቻ የቁልቁለት ጎዳና ላይ መሆኑን ያመላክታልና የጥቅምት 22 ሰማ ዕታት የህይወት ዋጋ በከንቱ እንዳይቀር ሁላችንም ተባብረን መታገል ይጠበቅብናል ብለዋል።

ይህ በዚህ እንዳለ በመለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ የዛሬ 6 አመት የተጨፈጨፉትን እነዚህን ሰማእታት ለማስታወስ ንቅናቄያችን ግንቦት ሰባት “የማንረሳው ወንጀልና የማንረሳቸው ሰማእታት” በሚል ረዕስ መግለጫ አውጥቱአል።  ግንቦት 7 ባወጣው በዚህ መግለጫ “ የዘንድሮውን 6ኛ አመት የጥቅምት 22 ሰማዕታት ቀን የሚንዘክረው፤ ሰማዕታቱ ህይወታቸውን የተሰውለትን መልካም አስተዳደር በአገራችን ለማስፈን ይቻል ዘንድ ለፍትህ፣፤ ለእኩልነትና ለነጻነት የሚደረገውን  ትግል ከዳር ለማድረስ ያለንን ቁርጠኝነት እንደገና በማደስ፤  የአጋዚን ጦር አሰልጥኖና አስታጥቆ በወገኖቻችን ላይ ፋሽስታዊ ጭፍጨፋ እንዲፈጸም መመሪያ የሰጡውን መለስ ዜናዊንና ጥቂት ግብረአበሮቹን በተባበረ ትግል ህግ ፊት ለማቅረብ ትግሉ የሚጠይቀውን ማንኛውንም መሰዋ ዕትነት ለመክፈል ቁርጠኝነታችንን ዝግጁነታችንን በመግለጽ ነው” ብሉአል።