ወያኔ ለከፋፍለህ ግዛ አላማው የሙስሊሙን ማህበረሰብ ለሁለት መክፈሉና አክራሪ ያላቸውን ወገኖች በማሳደድ ላይ መሆኑ ያስነሳው ውዝግብ ውጥረት መፍጠሩ ተዘገበ
በከፋፍለህ ግዛ የቅኝ ገዥዎች ፖሊሲ የተለከፈው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በብሄር ብሄረሰቦች መካከል የፈጠረው ክፍፍል የታሰበውን ውጤት ስላላመጣለት ፊትን ወደ ሃይማኖት ተቋማት በመመለስ የሙስሊሙን ህብረተሰብ ለሁለት ጎራ የሚከፍል ተግባር እያራመደ መሆኑን በዚህም አብዛኛው የሙስሊም ሃይማኖት ተከታዮች ከፍተኛ የሆነ ቅሬታ እንዳደረባቸው የግንቦት 7 ዘጋቢ ገለጸ።
እንደዘጋቢያችን ሪፖርት በአገራችን ሙስሊሞች ዘንድ ቀደም ሲል እውቅና ያልነበረው አህባሽ የሚባል የእምነት ትምህርት በወያኔ አገዛዝ የገንዘብና የሰው ሃይል ድጋፍ እየተደረገለት በሰፊው እየተሰራጨ እንደሆነና በሌላ በኩል ግን ሌላውን ወገን ዋህቢ በማለት በአክራሪነት ፈርጆአቸዋል። አዲሱን የአህባሽ ትምህረት የሚቃወሙ በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የሚገኙ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ለእስር ከመዳረጋቸውም በተጨማሪ በአዲስ ዘመን ከተማ ነዋሪ የሆኑ የወረዳው የእስልምና ሀላፊ የነበሩት ሰው በታጣቂዎች መገደላቸው ታውቋል።
ወያኔ በሙስሊም እምነት መካከል እያደረገ ያለውን ክፍፍል የዘገበው የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን፤ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በፖሊሲ ደረጃ ቀርጾና በ10 ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ የሙስሊሙ ማህበረሰብ አህባሽን እንዲከተል የማስገደዱን እርምጃ የተቃወሙ በርካታ የሀይማኖቱ ኡላማዎች ለስግደት ወደ ሳውዲ አረቢያ ከሄዱበት እንደማይመለሱ ከውስጥ አዋቂ ምንጮቹ ያገኘውን መረጃ ገልጾ ይፋ አድርጎአል።
ከፋፋዩ ወያኔ ኢትዮጵያዊያንን በሃይማኖት መከፋፈልና ማጋጨት የጀመረው ወደስልጣን ወምበር ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የነፍጠኛው መሸሸጊያ ሆናለች በማለት በውስጥ ችግር እንድትታመስና እንድትዳከም ማድረጉ በስፋት ሲዘገብ የቆየ ሲሆን አሁን ደግሞ ይሄው አባዜው አልለቀው ብሎት ፊቱን ወደ እስልምና ማዞሩ ታውቁአል።
የዘረኛው መለስ ዜናዊ አገዛዝ ሰሞኑን በሙስሊሙ ህብረተሰብ መካከል እያካሄደ ያለውን ክፍፍል አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢሳት የሰጡ የእምነቱ ተከታዮች፤ በምርጫ 97 ወቅት ኢህአዴግ የሙስሊሙ ጠበቃ እኔ ነኝ በማለት ቅስቀሳ ማድረጉን አውስተው፣ አሁን ደግሞ የሀይማኖቱን ተከታዮች ለሁለት ከፍሎ እርስ በርስ እንዲጋጩ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑ አገዛዙ በምን አይነት ሃላፊነት የጎደለው አጥፊነት ሥራ እንደተሰማራ ያስገነዝባል ማለታቸውን ተዘግቦአል።
እነኚሁ አስተያየት ሰጪዎች በማጠቃለያቸው በኢትዮጵያ በሀይማኖቶች መካከል ለዘመናት የነበረው መቻቻል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ በመሄዱ ወያኔ አገሪቱን ሊፈነዳ በተቃረበ የእስተገሞራ አለት ላይ እንድትቀመጥ አድርጓታል ሲሉ ስጋታቸውን መግለጻቸውን ኢሳት ዘግቦአል።
ወያኔ በሰሜን አፍሪካይቷ አገር በቱኒዚያ የፈነዳውና ወደ በርካታ የሰሜን አፍሪቃና መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት በተዛመተው ጸረ አምባገነኖች ህዝባዊ አብዮት እጅግ ስለተደናገጠ፤ በአገራችን ከመቀስቀሱ በፊት ህዝብ በጋራ እንዳይነሳበት የሚችለውን ዜዴ ሁሉ እየተጠቀመ እንደሆነ የሚናገሩት ከዚህም አንዱ በሃይማኖቶች መካከል ጣልቃ እየገባ አማኞችን እርስ በርስ ማጋጨት እንደሆነ ይስመማሉ።