የቀድሞው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፕሬዚዳንት የነበረው ያረጋል አይሸሹም ንብረት በወያኔ ፍርድ ቤት ታገደ። የግለሰቡ ሃብት ባለሥልጣናቱ የተዘፈቁበትን ሙስና መጠን አመልካች ነው ተባል
በያረጋል አይሸሹምና በህወሀት ባለስልጣናት መካከል በተነሳው የፖለቲካ ውዝግብ ምክንያት ቀደም ሲል ታማኝነቱንና ታዛዥነቱን ለማግኘት ሲባል በተከፈተለት የሙስና በር በራሱና በቤተሰብቹ ስም እስከዛሬ ያከማቸው ሃብትና ንብረት እንዳይንቀሳቀስ የወያኔ ፍርድ ቤት ማገዱን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ በላከልን ሪፖርት ገለጸ።
ፍርድ ቤት ተብዬው የወያኔ የማጥቂያ መሳሪያ፤ በያረጋል አይሸሹም፤ በባለቤቱ በትግስት በቃልና፣ በልጆቹ ስም ተመዝግበው የሚገኙ ንብረቶችን ያገደው፤ በአሶሳ በ1200 ስኩየር መሬት ላይ የሰፈረ የግል መኖሪያ ቤትና ሌላ ተጨማሪ 1000 ካሬ ሜትር ቦታ፣ በአዲስ አበባ ከተማ በቦሌ አካባቢ የሚገኝ 500 ካሬ መሬት፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚገኝ 4132 ካሬ ቦታ፣ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ 500 ስኩየር ሜትር ላይ የሰፈረ በአለአንድ ፎቅ ህንጻና አንድ ሌላ የኮንዶሚኒየም ቤት፣ ምግብ ቤት እንዲሁም በልጁ ስም የተመዘገበ 1490 ካሬ መሬት ቦታ እንደሆነ ታውቆአል።
ወያኔ ወደስልጣን በመጣበት ወቅት ለእግራቸው መቀየሪያ ጫማ ያልነበራቸው እንደ ያረጋል አይሸሹም አይነቶቹ ሆድ አደሮች፤ የአገሪቱን ሃብት በመዝረፍ አሉ ከሚባሉ ከበርቴዎች ተርታ መሰለፋቸው ተደጋግሞ ሲዘገብ የቆየ ቢሆንም፤ 8 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዘርፎ በሲዊዝ ባንክ አስቀምጦአል ተብሎ ለአመታት እስር ቤት ተወርውሮ ከነበረው የቀድሞው የብአዴን መሪ ታምራት ላይኔና የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት አባተ ኪሾ ክሶች ወዲህ የሃብቱ ዝርዝር አደባባይ የወጣ የወያኔ ባለሥልጣን እንደሌለ ይታወቃል። ለዚህ ይመስላል የአሁኑ የያረጋል አይሸሹም ሃብት ዝርዝር ይፋ መውጣት ከህወሀት ባለስልጣናት ጋር የገባበትን የፖለቲካ ውዝግብ ተከትሎ የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ በርካታ የህዝብ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።
ያረጋል አይሸሹም ወያኔን ከመቀላቀሉ በፊት የአንደኛ ደረጃ ትምህረት ቤት መምህር የነበረ ሲሆን በወገንና በአገር ኪሣራ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ላለፉት 20 አመታት የመለስ ዜናዊ ቡድን ተጠናክሮ ስልጣን ላይ እንዲቆይ አቅማቸው የቻለውን ሁሉ አስተዋጾ ካበረከቱት ታማኝና ታዛዥ የወያኔ ሎሌዎች አንዱ እንደነበር ይታወቃል።
የመለስ ዜናዊ ቡድን በስፋት እያራመደ ላለው የአገር ሃብት ዘረፋ ተባባሪ ለማብዛት ሂሊናቸው ከግላቸውና ከቤተሰቦቻቸው የማቴሪያል ጥቅም በላይ አርቆ ማየት የማይችል አቅመ ደካማ ሰዎችን በዙሪያው በማሰባሰብ እንደሚገለገልባቸው ሲዘገብ ቆይቶአል።
ወያኔ በበላይነት በሚያስተዳድረው የኢህአደግ አባል ድርጅቶች ውስጥ አባል በመሆናቸው የየክልላቸውን ሃብት ዘርፈው እንዲያዘርፉ ሥልጣን የተሰጣቸው ግለሰቦች፤ በዘረፋ የሚበቃቸውን ሃብት ካከማቹ ቦኋላ በሎሌነት ከሚያገለግሉዋቸው የህወሃት ባለሥልጣናት ጋር ሲጋጩ እንደሚፈረደባቸው የጥፋት አይነት በውስጥ ግምገማ የዘረፉትን ሃብት ይዞ ይባረራሉ፤ ጥቂቶች ደግሞ እንደ ያረጋል አይሸሹም ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት ተመርቶ እሥር ቤት ይወረወራሉ። ይህ ሁሉ ሲሆን ህወሃት ለሁለት በተከፈለበት ወቅት ለፖለቲካ ብቀላ በነ አቶ ስዬ አብረሃ ላይ ከተመሰረተው ውንጀላ በቀር እስከዛሬ አንድም ሰው ከህወሃት በግምገማ መባረሩ አደባባይ ስላለወጣ ሁሌ በግምገማ በሚታመሱ የኦህዲድና የብአዴን አባላት መካከል ከፍተኛ ቅሬታ ማስከተሉን ምንጮቻችን ይናገራሉ።
የመለስ ዜናዊ ባለቤት አዘብ መስፈን በአገሪቱ ካሉት ባለሥልጣናት ሁሉ ከፍተኛ ድርሻ ባለው ሙስና ብዙ ሃብት ያፈራች መሆኗ ሲታወቅ ከአገር አልፎ በቅርቡ አንድ የስፔን ጋዜጣ ከአፍሪካ የመሪዎች ሚስት ተወዳዳሪ የሌላት ከበርቴ እንደሆነች መዘገቡ አይዘነጋም።