ኢትዮጵያ ህጻናትን ለጉዲፈቻ ወደ ውጭ አገራት በመላክ ከአለም አንደኛ ልትሆን እንደሆነ ታወቀ
ከተለያዩ የአለም አገራት ወደ አሜሪካ ለጉዲፈቻ የሚመጡ ህጻናት ቁጥር እየቀነሰ ሲሄድ፤ ከኢትዮጵያ የሚመጡት ግን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ ነው ሲል አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
እንደ ዜና አውታሩ ዘገባ፥ ከዛሬ ስድስት አመት ጋር ሲነፃጸር፣ ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የሚሄዱ ህፃናት ቁጥር በብዙ እጥፍ ጨምሯል። በያዝነው የፈረንጆች አመት ሁለት ሺህ አምስት መቶ ኢትዮጵያውያን ህጻናት በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ እንደሚሄዱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ እንደሚገምትም ዘገባው ጠቅሷል። ከስድስት አመታት በፊት ግን ይሄ ቁጥር 284 እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ከቀጠለ ኢትዮጵያ በቅርቡ ቻይናን በመቅደም ለአሜሪካውያን ቤተሰቦች በአለም አንደኛዋ የጉዲፈቻ ምንጭ ትሆናለች ተብሏል።
ዘገባው በተጨማሪ በኢትዮጵያ አምስት ሚሊዮን ወላጅ አልባ እና የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት እንዳሉ ገልጿል። የዚህ ችግር መንስኤዎች ድህነት፣ ረሃብ እና በሽታ እንደሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ ወላጅ አልባነት እና ጎዳና ተዳዳሪነት እየጨመሩ መሄዳቸው አገሪቱ ያለችበትን የኢኮኖሚ ሁኔታ አመላካች ነው ሲሉ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ።
ህፃናቱን የሚያሳድጉ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች ሳይገኙ ሲቀሩ በከፍተኛ ቁጥር ወደ ውጭ አገራት መላካቸውም አገሪቱ ስላለችበት የድህነት ደረጃ ተጨማሪ ማሳያ እንደሆነ ይነገራል።
ከዚህ በተጨማሪ፥ የወያኔ ባለስልጣናት የኢትዮጵያን ህጻናት ወደ ውጭ አገራት በጉዲፈቻ መላክ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ስራ መሆኑን በመገንዘብ ትኩረት ሰጥተውት በመቀንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን አንዳንድ ምንጮች ከዚህ ቀደም ለዝግጅት ክፍላችን ባደረሱት መረጃ ገልጸዋል።