የሙስና ትርጉም፤ ተዛማጅ ክስተቶቹና በአገርና በሕዝብ ላይ የሚያስከትላቸው ጠንቆች፤ በፕሮፌሰር ሰይድ ሃሰን በፍኖተ ጋዜጣ ካሳተሙት

በዓለማችን ውስጥ የተከሰቱትንና እየተከሰቱ ያሉትን የሙስና ጠባዮች የሚከታተሉ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና እንዲሁም ጉዳዩን በጥብቅ የሚከታተሉት ግለሰቦችና ለጋሽ ድርጅቶች እንደ ጎርጐርሳውያን አቆጣጠር ከ1990ዎቹ በኋላ፤ በሁለት ፅንፍ መልክ የሚታዩ ሙስናዎች የተከሰቱ መሆኑን ያስገነዝባሉ፤ ስምምነትም ላይ ደርሰዋል። እነዚህም (1) በመንግሥታዊ አስተዳደር ብልሹነት መስክ የሚሰባሰቡ/የሚገለፁ/የሚከሰቱ ሙስናዎች (administrative corruption) እና፤ (2) የመንግሥቱን የሥልጣን አውታር፤ አስተዳደሩን፤ ህጎቹን፤ ወ.ዘ.ተ. በመማረክ የሚገለፁ የሙስና ጠባዮች (state capture) ናቸው። የአስተዳደሩን ብልሹነት ተጠግተው የሚከሰቱ ሙስናዎች ሕጎቹና ደንቦቹ ሳይደመሠሡ (እንደተጠበቁ ሆነው) ነገር ግን የህጎቹና የደንቦቹን አፈፃፀሞች በድብቅና ህጋዊ ባልሆነ መልክ የግለሰቦችን ጥቅሞች ማካበቻ ማድረግ ነው። እነዚህም ከተራ ጉቦ ጀምሮ እስክ ታላላቅ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያሳተፉ ከፍተኛ ሙስናዎች/ ምዝበራዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የመንግሥትን ሥልጣን፤ ህጎችንና የአስተዳደር ደንቦችን በመማረክ/በመጥለፍ የሚከናወኑ ሙስናዎች ግን ህጎቹን፤ ደንቦቹን፤ ሥርዓቶቹንና ቁጥጥሮቹን፤ (laws, regulations, decrees, and other government policies) በማስቀየርና በመቀየር/በመጥለፍ ላይ ተሣትፈው፤ የራሳቸውን ጥቅሞች በማካበት ላይ ይሳተፋሉ። ማራኪዎቹም (captors) ሥልጣን ተሻሚ ግለሰቦች፤ ተመሳጣሪ ቡድኖች፤ በአምባገነናዊ መልክ ሥልጣን ላይ የወጡ ቡድኖች (oligarchy)፤ ባለጌ ባለሥልጣኖች ሊሆኑ ይችላሉ፡ ፡ እንደዚህ አይነቱ ሙስና የተከሰተው የሶቬት ሕብረት መንግሥት ከመፈረካከሱ አስቀድሞ በሶሻሊዝም/ኮሙኒዝም አይዲዮሎጂ የተዳደሩ አግሮችንና ከዚያ በኋላ ግን የነፃ ገባያን (ካፒታሊዝም) እንከተላለን በሚሉና በአንዳንድ ታዳጊ ሀገሮች ውስጥ ነው። የዚህ አይነቱ ሙስና ወደ ከፍተኛ እና የከፋ ደረጃ ሲደርስ ደግሞ የመንግሥት ሥልጣኑን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልክ በእጃቸው ያስገባሉ። በእኔ አስተሳሰብና ምርምር ለእንደዚህ አይነቱ ሙስና በዋናነት የምትቀርበው ሀገር ኢትዮጵያ ስትሆን፤ በአነስተኛ መልኩም እንደነ ሩዋንዳና ዩጋንዳን ይጨምራል። ይህ ዓይነቱ ሙስና ሚዛኑ የሰፋና ውጤቱ የከፋ ከመኑም በላይ ውጤቱ የፖለቲካ ፓርቲ ሀብቶች የሆኑ ኦሊጋርኮች (oligarchs) እና ክምችት የበዛባቸው ባለሀብቶችን (Business Empires ) መፍጠር ነው። አንባቢ መርሳት የለለበት ነገር ቢኖር ምንም እንኳ በአስተዳደር ብልሹነት፣ህጎችንና ደንቦችን በመማረክ/ በመጥለፍ የሚከሰቱት ሙስናዎች በሥነ- ልቦናና በተግባር ልንለያቸው ብንችልም፤ አብዛኝውን ጊዜ አንዱን ከሌላው መነጠል ያስቸግራል። በተለይም ህጎችንና ደንቦች በመማረክ/በመጥለፍ የሚከሰትው ሙስና (state capture) የከፋ ስለሆነ በአስተዳደር ብልሹነት (administrative corruption) የሚከሰቱት ሙስናዎችንም ይጨምራል።
ከዚህ በታች፤በመጀመሪያ በአስተዳደር ብልሹነት የሚከሰቱትን ሙስናዎችና ጠንቆቻቸውን አቅርቤ፤ በሌላ ጊዚ ደግሞ ሥልጣንን፤ ህጎችንና፤ የአስተዳደር ደንቦችን በመማረክ/በመጥለፍ የሚታወቀውን ታላቅና አስከፊ የሙስናና ጠባዮችና ጠንቆቹን አቀርባለሁ።

ሀ) በአስተዳደራዊ መስክ የሚጠቃለሉ ሙስናዎች ትርጉምና ባህሪያት፤ ከሙስና (Corruption) የመዝገበ- ቃላት ትርጉሞች አንዱ ሙስና “የአእምሮ መዛባት ወይም ብልሽት” ማለት እንደሆነ ይጠቁማል። ከመንግሥታዊ ባህሪና ድርጊት ጋር የተያያዘውና አጠር ያለው አንደኛው ትርጉሙ ደግሞ “የመንግሥት ተቋምን ወይም ሥልጣንን ተጠቅሞ የራስን ጥቅም/ሀብት ማካበት” ማለት እንደሆነ በግልጽ ያመለክታል። በመሆኑም ሙስና በስልጣን መባለግንም ያጠቃልላል። ይህ አግባብ ባልሆነ መልክ ራስን ማበልጸግ የሚገለጸውም በሥልጣን ላይ የሚገኙት ሃላፊዎች በመንግሥት የተያዙ ንብረቶችን በድብቅ በመሸጥ ላይ ሲሰማሩ፤ ለመንግሥት መገልገያ የሚሆኑ ዕቃዎችን እንዲገዙ የተመደቡ ሰዎች ለግላቸው ክፍያ በጓሮ በኩል እንዲከፈላቸው ሲያደርጉ (kick backs via government procurement and false invoicing)፤ የተቀጠሩበትን ሥራ ለመፈጸም በሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች ጉቦ ሲወስዱና ጉቦው ካልተገፋላቸው ደግሞ የተጠየቁትን/የተቀጠሩበትን አንፈጽምም ሲሉ ወይም ሲለግሙና በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች በግዴለሽነትም ሆነ በሌላ ምክንያት የመንግስት ሃብቶች እንዲባክኑ ሲያደርጉ ነው። በተጨማሪም ሙስና አዲስ ሠራተኛ ሲቀጠር በስልጣን ላይ ያሉ ሃላፊዎች አድሎ በማድረግ ዘመዶቻቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን ወይም የራሳቸውን ቡድን ወይም ፓርቲ አባላት ወይም የጎሳ አባላቸውን በማስቀደም ሲቀጥሩ (nepotism and favoritism)፤ በመንግሥት ሥር የነበሩትን ድርጅቶችና ተቋማት ግልጽ ባልሆነ መልክ ለጓደኞቻቸው ወይም ለዘመዶቻቸው በርካሽ ሲሸጡ እንዲሁም በሌሎች በርካታ መልኮቹ ይከሰታል።

አስተዳደራዊ ሙስና በጣም በርከት ባሉ መልኮች የሚገለጥ ሲሆን ከላይ የተጠቀሱት ባህሪያት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። አብዛኞቻችን ግን ሙስና ማለት ጉቦ መስጠት ወይም መቀበል ብቻ ይመስለናል። ጉቦ መውሰድ ወይም መስጠት የሙስና አንደኛው መልኩ እንጂ ሁሉንም ገጽታውን አያሳይም። ስለሆነም ሙስና በገንዘብ ስጦታ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ አገልግሎት በመለዋወጥ፤ ሕጋዊ አገልግሎትን ባፋጣኝ መልኩ ለጥቅም አጋሮች አሳልፎ በመስጠት፤ ወንጀለኛ እስረኛን ያለጊዜው በመልቀቅና ከእስር እንዲያመልጥ በማድረግ፤ የታክስ ክፍያ ለአንዳንድ ሰዎች እንዲቀርና እንዲቀነስ በማድረግ፤ ወይም አግባብ በሌለው መልክ ታክስን በሌሎች ላይ በመጫን፤ በየግል ንግድ ተቋማት መካከል መልካም ውድድርና ፉክክር እንዳይካሄድ በማድረግ፤ መንግሥታዊ ምስጢሮችን ለግል ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች አላግባብ በማካፈል፤ አንዳንድ ጊዜም ምስጢር አሾልኮ በማውጣት፤ እቃ በመለዋወጥና በመሳሰሉት መልኮች ይከሰታል። በውትድርናም መስክ በሠራዊት መዋቅር ውስጥ መሪዎች ለጭፍን ተከታዮቻቸውም ሆነ ለብሄር አባሎቻቸው ባልተገባና ደረጃቸውን በማይመጥን መልክ ከፍ በማድረግ ሂደትም ይከሰታል።

አስተዳደራዊ ሙስና በመንግሥት አውታሮችና ሠራተኞች መካከል ብቻ ሳይሆን በግል ድርጅቶችም ውስጥ ሊከሰት ይችላል። ለምሳሌ፤ በእግር ኳስ ተጫዋች ቡድኖች በሚደረግ ፉክክር አግባብ በሌለው መልክ አንዱ ቡድን እንዲሸነፍ ማድረግ ወይም ሁለት ወይም ከሁለት የበለጡ ኩባንያዎች የዕቃዎቻቸውን ዋጋ ከፍ በማድረግ መመሳጠራቸውም ከሙስና የሚቆጠር ነው። አንዳንድ ጊዜ ሙስና በማስፈራራትና በተራ ግድያም (ማፍያ) መልክ ይከሰታል። እንደነዚህ ዓይነት በግለሰቦችና በግል ድርጅቶች መካከል የሚደረጉ የሙስና ጠባዮች መንግሥታዊ የአሠራር ብልሹነትን የሚያንፀባርቁ ክስተቶች ናቸው፤ በተለይ ደግሞ የኋለኞቹን መንግሥት እያወቀ ዝም ካላቸውና ወይም በተመሣጥሮው ውስጥ እጁን ካሰገባ! ከዚህም በተጨማሪ የህግ አስጠባቂ ፖሊሶች ወንጀለኛ ያልሆነውን ሰው እንደ ወንጀለኛ አድርገው ሲከሱ፤ የፍርድ ቤት ዳኞች በወንጀል የተከሰሰውን ግለሰብ በሆነው ባልሆነው ያለበቂ ምክንያት ሲያጉላሉ፤ የፖሊስ ባልደረቦች የሥራ ባልደረባቸው በግለሰብ ዜጎች ላይ ባደረገው ደባ ወይም ግድያ ለመመስከር ፍላጎታቸው ሲቀንስና በመሣሰሉ ሌሎች ሁኔታዎችም ሙስና ይከሰታል። አንዳንድ መንግሥታት ደግሞ በስልጣን ያሉ ሃላፊዎች የህዝብን ሃብት ለመዝረፍ እንዲያመቻቸው አዳዲስ ህጎችን ጭምር ሲያወጡና ሲደነግጉ ይታያሉ። እነዚህና የመሳሰሉ ህጎችን ሲያወጡም የገንዘብና ሌሎች ጥቅሞች ለማግኘት ብቻም ሳይሆን የስልጣን ጥማቸውንም ለማርካት ጭምር ይሆናል። ይህም ከሙስና የሚፈረጅና ሌላው የመከሰቻ መልኩ ነው።

ምንም እንኳ ሙስና በጣም በርካታ በሆኑ መልኮች ቢከሰትም፤ በአብዛኛው በስውር የሚፈጸም ነው። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ ገሃድ መውጣቱ ግን አይቀሬ ነው። በተለይ ከሙስና መከሰቻ መልኮች ጉቦ መሰጣጣት በድብቅ የሚደረግ ቢሆንም፤ የጉቦ መስፋፋት ጉዳይ ከቶውንም ከህዝብ ሊሠወር አይችልም። ምክንያቱም ጉቦ እንዲሰጥ የሚገደደው ራሱ ሕዝቡ ነውና! ምንም እንኳ ሙስና በየትኛውም ሀገር የሚገኝ ቢሆንም፤ የአንዲት ሀገር በከፋ ሁኔታ በሙስና መጠመድ በሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ነፀብራቅ ነው።
ሙስና በአንዲት አገር ውስጥ የቱን ያህል መስፋፋቱን የሚለኩና የሚመዝኑ እንዲሁም የሚያወዳድሩ መስፈርቶችን አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑና መንግሥታዊ የሆኑ ድርጅቶች መፍጠርም ችለዋል። የእነዚህ መስፈርቶችም ጥቅሞችና ታዓማኒነትም በርከት ባሉ ደረጃዎች ይለያያሉ።

ማወዳደሪያዎቹን ለማቅረብ የግድ በእያንዳዱ ሀገሮች ውስጥ የአሰሳ ጥናት (survey) ማድረግን ይጠይቃል። የአሰሳው ጥናትና የጥራት ውጤትም የገዥውን መንግስትና የተጠያቂዎቹን ትብብር ስለሚጠይቅ፤ የሙስና መለኪያዎቹና ማወዳደሪያዎቹ ላይ ሙሉ እምነትን መጣል ያስቸግራል። በዚህም የተነሳ የአሰሳ ጥናት ውጤቶች በአንዲት ሀገር ውስጥ የሚገኘውን ሙስና ዝቅ አድረገው እንዲገምቱ ይገደዳሉ ወይም የአሰሳ ጥናቱ ከተጨባጭ ሁኔታው ዝቅ ያለ ነው ተብሎ ይገመታል። ትራንስፓሬንሲ ኢንተርናሽናል (Transparency International) የተባለው ድርጅት በቅርቡ ባወጣው የማወዳደሪያው መስፈርቱ ለኢትዮጵያ 2.7 ነጥብ ከ10 በመስጠት፤ ከ178 ሀገሮች መካከል 116ኛውን የያዘችና በሙስና የተዘፈቀች አድርጎ መድቧታል ። ይህ ምደባ እራሱ አሳፋሪ ቢሆንም፤ አንዳንድድ ታዛቢዎች ግን ይህ ምደባ ለኢትዮጵያ ሲበዛባት ነው፤ቸር ሆኖላታል ብለው ያምናሉ። የ “ሞ-ኢብራሂም” (Mo Ibrahim Index) መመዘኛ ደግሞ ኢትዮጵያ ከ53 የአፍሪካ አገሮች መካከል 35ኛውን እንደያዘች አድርጎ አቅርቧል። ሞሪሼስ፤ ሲሼልስና ቦትስዋና ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃን የያዙ መልካም አስተዳደርን የሚከተሉ ሀገሮች አድርጎ መድቧል። የአለም ባንክ በዚህ ሰሞን ባወጣው ንግድና ፋብሪካን ለማቋቋምና ለመሥራት (Ease of Doing Business)፤ የኢትዮጵያ ደረጃ ከ104ኛ ደረጃ ወደ 111ኛ ደረጃ ወርዳለች ብሏል። ፍሪደም ሀውስ (Freedom House, In.) የተባለው ድርጅትም የኢትዮጵያን ደረጃ ዝቅ በማድረግ፤ የሲቪልና የፖለቲካ ነፃነት የተነፈገባት፤ ነፃ ምርጫ በፍፁም የሌለባት፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው የሚዋከቡባት፤ እንዲሸማቀቁ የሚደረጉባት፤ ነጻ የመገናኛና መንገዶችና የማህበራዊ ድርጅት መሪዎች በመንግሥት ሀይል የሚደቆሱባት (clampdown) እና ችግሮቹም በየዓመቱ እየተባባሱ የመጡባት ሀገር ሆናለች ብሎ አስፍሯል።

አንንዳንድ ጊዜ ሙስና በጣም በተቀናበረ የሌብነት መልኩ ይከሰታል። ይህ በተቀናበረ መልክ የሚከሰት ሌብነት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የአፍሪካ አገሮች በጣም ሥር የሰደደ ሲሆን፤ በሌብነቱም በተለይ በመንግስት አስተዳደር ቁንጮ ላይ የሚገኙ ሰዎች በጋራ (in a group) በዝርፊያው ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ይህ ዓይነቱ ዝርፊያ እንደ ናይጀሪያ ባሉ አገሮች ውስጥም በጣም የተስፋፋ ሲሆን አንዳንዶቹን ዘራፊዎች ከሌሎቹ የሚለያቸው ከራሳቸው ቡድን ወጣ ያሉ ሰዎች እንደነሱ መክበርና ሀብት ማድረግ ሲፈልጉና ሲችሉ በጣም መናደዳቸውና በሩንም ጥርቅም አድርገው ሲዘጉ መታየታቸው ነው። ይህ የንዴት ባህሪ ደግሞ በቅናት ላይ የተመረኮዘ ስለሆነ በአንዳንድ ሀገሮች ተከስቶል እንደሚታየው በግድ እገዛሃለሁ ከሚለው አምባገነናዊነት ጋር ይዛመድና ሙስናዉና አገዛዙ መላ ቅጣቸው የጠፋ ይሆናል። ሙስናው ቅጡን ሲያጣና፤ የጥቅም ሽኩቻው ሲበዛ፤ በዝርፊያው የበላይነትን የያዙት የሙስና ጥቅም ተቀናቃኞቻቸውን ነጥለው በመምታት ሊያስወግዷቸው እንደሚችሉና፤ የጠነባውን ሙስና የሚዋጉ አስመስለው ለማቅረብና ሽፋን ሲሰጡ ይታያሉ። በርካታ ታዛቢወች እንደ ጎርጎሪሳውያን አቆጣጠር በ1990ዎቹ የኢሕአደግ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩት በአቶ ታምራት ላይኔ የተወሰደው እርምጃ ይህንኑ የሙስና ተዋጊ አስመሳይነትንና በጥቅም ሽሚያ ቅናት ላይ የተመረኮዘ ነበር ይላሉ። ከዚህም አልፈው እንደጎርጎሪሳውን አቆጣጠር በ2001 ዓ/ም በተፈጠረው የሕወሓት ፓርቲ አመራር አባላት መካከል በተፈጠረው ልዩነትና ሽኩቻ በኋላ የአሸናፊው የአቶ መለስ ቡድን ተቃናቃኞቹን ወደ አስር ቤት ለመስደድ የተጠቀመባቸው የሙስና ክሶችና ታክቲኮች ሙስና እንዴት ተቃናቃኞችን ነጥሎ የመምታት መሣሪያ እንደሚሆን፤ ይህ አይነት ተግባርም በምስራቅ አውሮፓና እንደነ ሩሲያ ባሉ ሀገሮች በድግግሞሽ ተግባራዊ እንደሚተገበርም በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። ሆኖም ግን የጠነባው ሙስና እንዲከሰት ያደረገው ሥርዓት ተፈንግሎ እስካልተወገደ ድረስ እንደውም እንደዚህ ያሉት የይስሙላ እርምጃዎች ሙስናው እንዲስፋፋና እንዲፋፋም ያደርገዋል። ታዛቢዎች እነ ታምራት ላይኔና ሌሎችም ተዘፍቀውበት የነበረው የሙስና ጠባይ አሁን ከመጠን ባለፈ መልኩ ይበልጥ እየተስፋፋ መሄዱን እንደ ዋቢ አድርገው ያቀርባሉ።

አንዳንዱ ሙስናም የህዝብ ንብረቶችን ካንድ ክፍለ ሀገር ወደ ሌላው ከፍለ ሀገር በማዘዋወር የተዘረፈው የሕዝብ/የሃገርን ሀብት ሕጋዊ ሽፋን በመስጠት ላይ ይከሰታል። ይህ ዓይነቱ የሙስና ባህሪና ድርጊት እንደ ናይጄሪያ ባሉ አገሮች ውስጥ በተደጋጋሚ ጎልቶ እንደሚታይ የተከሰተ ሲሆን፤ የሚደረገውን ዓይን ያወጣ ዝርፊያ፤ የውጭ አገር ወራሪ ኃይል በወረራ በያዘው አገር ከሚያደርገው የከፋ ዝርፊያ ይወዳደራል።

በሌላ በኩል ሙስና ዓይን ባወጣ ሌብነት ብቻ ሳይሆን በጣም በተቀናጀ መልክና ሕጋዊነት ሽፋንን የያዘ ዝርፊያም ይከሰታል። ይህም የሚከሰተው በስልጣን ላይ ያሉ ሃላፊዎችን በተቀናጀ መልክ በማግባባት (Lobbying) ሲሆን ይህ ዓይነቱ ሙስና በተለይ ባልሰለጠኑት አገሮች እጅግ ተስፋፍቶ ይገኛል። ድርጊቱ የወጣለት ዝርፊያ ቢሆንም፤ ሃብትን ከህዝብ ወስዶ ለጥቂት ቡድኖች የሚሰጥ ፍጹም ዓይን ያወጣ እኩይ ተግባር ነው። ከተራው ሙስና ለየት የሚያደርገው አንዱ ጠባዩ ግን “ሕጋዊ” መሆኑ ነው። “ሕጋዊ” ቢመስልም ያው እንደ ተራው ጉቦ አንዱን አራቁቶ ሌላውን የሚያለብስ ስለሆነ ያገርንና የህዝብን ሃብት የሚያባክን ሌብነት ነው።

ሙስና ባጠቃላይ ሲታይ ያንዲት አገር የህግ፤ የኢኮኖሚ፤ የባህልና በተለይም ደግሞ የፖለቲካ ባህል ብልሹነት ነጸብራቅ ነው። ሙስና በሁሉም አገሮች የሚገኝ ሲሆን፤ ጨርሶ ለመቋቋምም ሆነ ለማጥፋት አይቻልም። ሙስና በበዛባቸው አገሮች ውስጥ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ተቋማት የተቋቋሙበትን ዋነኛ ተግባር በደንብ እንዳያከናውኑ ያግዳቸዋል። ጉቦ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ያላግባብ ቢያበለጽግም፤ ገንዘቡ ወደ መንግስት ካዝና ስለማይገባ ለህዝብ ወይም ለመንግሥትም ጠቃሚ አይደለም። ጉቦ መሰጣጣት ሲበዛ በሰዎች መካከል አለመተማመንን፤ ጥርጣሬንና ግራ መጋባትን ይፈጥራል። ግራ የገባው ግለሰብም ሆነ ቡድን ወይም ድርጅት ጠንከር ብሎ ሥራውን እንዳይሠራ ይፈራል፤ ይባባል። ዕምነትም ያጣል። ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ሲያወላውሉ፤ ሲፈሩ፤ ሲቸሩና ሲባቡ ምግባረ-ብልሹነት ተባብሶ አገር ወደኋላ ትቀራለች። ሙስና በበዛባቸው አገሮች የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና አውታሮች እንዲሁም ጠቅላላው የሲቪል መስክ ባሠራር ማነቆ/ቀይ ጥብጣብ (ቢሮክራሲ) ውጣ- ውረድን የሚያስከትልና የተበላሸ ነው። ሙስና በተስፋፋ ቁጥር ዓይን ያወጣ ሌብነት ይበዛና የአንድን አገር ክቡር ባህል ጭምር መሸርሸር ይጀምራል። ሙስና ክቡር ባህልን ከለወጠ በኋላ ደግሞ አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል “ጀርባዬን እከክልኝ፤ እኔም እንዳክልህ” በሚለው አመለካከት ውስጥ እንዲዘፈቅና እንዲጠመድ (entrenched) ያደርገዋል። ሙስና ባህልን ካበላሸ እያደር ለልጅ ልጅም ይተላለፋል። ዛሬ በኢትዮጵያችን በገሃድ እንደሚታየዉ ራስ ወዳዶችና ለሆዳቸው ያደሩ በብዛት የመፈለፈላቸውን ያህል ለዛሬው ሕዝብና ለነገው ትውልድ የሚጨነቁ መሪዎች አልበረከቱም። በአኳያው ሙስናው በምስጢርና በረቀቀ ዘዴ መበርከቱ ህብረተሰቡንም ጭምር ምስጢረኛ፤ ሽምቀኛ፤ ተንኮለኛ፣ሃሜተኛና ተጠራጣሪ እንዳያደርገው ያስፈራል። በርካታ ታዛቢዎች እንደዚህ ያለው ብልሹነት በኢትዮጵያችን ተስፋፍቷል ይላሉ።

በቅርቡ ኢትዮጵያን ጎብኝተው የሚመለሱ አንዳንድ ግለሰቦች እንደጠቆሙት፤ በርካታ ግለሰቦች በሥልጣን የሚባልጉት የበላይ አካሎችና መሪዎች በመቅፅበት ከብረው ሲያዩ፤ እነሱን እንደምሳሌ በመቁጠር እንደነሱ በሌብነት ላይ መሣተፍን መርጠዋል፤ “የአባት አገር ሲወረር፤ አብረህ ውረር” መሆኑ ነው መሰል። አንድ ምሣሌ ለመጥቀስ ያህል፤ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ፤ በቁጥር የማይናቁ አንዳንድ ግለሰቦች የግል ኩባንያዎችና የመንግሥት ተቋሞች ለመንገድ፤ ለቤትና የመሥሪያ ቤት መስሪያ መጠቀሚያ የሆኑ ግብዓቶችን ጨለማን ተገን አድረገው ሳያዘውትሩ መስረቃቸውን፤ አንዳንዶች ደግሞ በአውራ ጎዳናዎች ዳር ወይም አቅራቢያ የተዘረጉና በመዘርጋት ላይ ያሉ የብረት ዋልታዎችና የድልድይ ድጋፎችን እየሠረቁ በድብቅ በመሸጥ ላይ መሆናቸውንና በዚህ ክፉ ተግባር የተሰማሩ የሕብረተሰቡ ክፍሎች በርካታ በመሆናቸው ስርቆቱን ለመቋቋም ካለመቻሉ የተነሳ የሚሠሩት ተቋማትን በጊዚው ሠርቶ ሠርቶ ለመጨረስ አልቻል ብሏል ይላሉ። ይህ የሚያሳየው የማይናቅ ቁጥር ያለው የሕብረተሰባችን ክፍል “ለራሴ” እንጂ “ለአገሬ” የሚል ስሜት እያጣ መሄዱን ነው። ይህም የሙስና መስፋፋትንና የክቡር ባህልን ቀስ በቀስ መለወጥ/መሸርሸር በጉልህ የሚያሳይ ነው።

ስር የሰደደ ሙስና እያደር ከልጅ ልጅ የመተላለፉ ጉዳይ በባህላዊና በስነ ልቦናዊ መልክ ብቻ አይወሰንም። ለምሳሌ የግል ድርጅቶች፤ የፍጆታና ቁሣቁስ አምራች ኩባንያዎች አየሩን እንዲበክሉ ያደርጋል፤ ይገፋፋል፤ በዚህም የተነሣ ብዙው የህበረተሰብ ክፍል የአስም በሽታ ተጠቂ እንዲሆን ያደርገዋል። የሣምባ ነቀርሳ ሰለባም ያደርገዋል። በነዚህ ዓይነት በሽታዎች በበለጠ የሚጎዱት ሕፃናት ስለሆኑም፤ ያገሪቱ አበባዎች ሲረግፉና በሽተኞች ሲሆኑ አገሪቱ አምራች ልጆቿን አጣች ማለት ነው። በበሽታው የተለከፈውን የህብረተሰብ ክፍል ጤንነት ለመንከባከብ አገሪቱ ንብረቷን እንድታባክን ትገደዳለች። በሙስና የተዘፈቁ ድርጅቶችና ኩባንያዎች ለጤናና ለሌላም ወጪ የሚጨነቁ አይደሉምና ለጥቅማቸው ሲሉ በሚያደርጉት ተግባር ወንዞችና የውሀ ማመንጫዎች በኬሚካል ሊበከሉ ይችላሉ። የዚህ ውጤቱም ህብረተሰቡን በንፁህ ውሀ እንዳይጠቀም ብሎም በሽተኛ ያደርገዋል። ኬሚካሉም ወደ መሬት ይሰርግና (አሁን እንደ ቻይና ባሉት አገሮች እንደሚከሰተው) የውሀ ማመንጫዎችን በመበከል ቀጣይ ትውልድን በሚያጠፋ መልኩ ለብዙ ዘመን በብክለት ይቀራል።

ሙስና “ባህል” ከሆነባቸው ሁለት አገሮች ታይላንድንና ናይጀሪያን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያችን የተንሰራፋው ሙስና ከነዚህ አገሮች የሚተናነስ አይደለም ይላሉ፡፡ ብዙ ታዛቢዎች። እንደሚታወቀው ናይጀሪያ ከእንግሊዝ ነፃ ከወጣች በኋላ በተደጋጋሚ በሙስና የተዘፈቁ ፅንፈኛ ወታደራዊ አስተዳደሮች የተለዋውጡባት አገር ናት። እነዚህ በስልጣን የባለጉ መሪዎች ለተራው ዜጋ ያሰተማሩት፤ ጠብ-መንጃ ያለው ብዙ ሃብት ማካበት መቻሉን፤ በሙስና ተግባር በመክበር አንዱ ወንበዴ በሌላው እየተተካ ይኸው መፈራረቁን፤ በህጋዊ መልክ ኑሮን ለመግፋት ማቃቱንና በጉልበትና በውንብድና ካልሆነ በስተቀር ሌላው አማራጭ ጨለማ ሆኖ እንዲታየው መሆኑን ነው። በዚህ ዓይነት ያንድ ሃገር ዜጋ ተስፋ ሲቆርጥና በመንግሥቱም ዕምነት ሲያጣ ራሱም በሌብነቱና በዝርፊያው ላይ መሰማራቱ አይቀሬ ይሆናል። አንዳንድ የናይጀሪያ ምሁራን ይህንን ጉዳይ በማስረጃነት ሲጠቅሱ “ያገሪቱ አንዷና ትልቋ ከተማ ከነበረችው ሌጎስ ተስፋፍቶ የነበረውና አሁንም ያልጠፋው በጠራራ ጸሀይ የሚካሄድ የመኪና እና የባንክ ዝርፊያ ወደ ሌሎቹም አነስተኛ ከተሞች መስፋፋቱ የባህል መለወጥ ውጤት ነው” ይላሉ። ጠብ-መንጃ ያለው ወታደርና ቡድን ሀብታም ሲሆን፤ ህዝብም በተራው ጠብ-መንጃውን ይዞ በዝርፊያው እንዲሠማራ ተማረ ማለት ነው። ታይላንድ በምትባለው ወርቃማ አገርም ሙስና እንደባህል ሆኖ አንዳንድ ጊዜም እያንዳንዱ ዜጋ በሙስና ካልተሳተፈ ቅር የሚለው ይመስላል። በእፅ እንደሠከረ ሰው የሱስም ያህል ሆኗል። ይህችን ቆንጆ አገር ሁለት ጊዜ እኔና ቤተሰቦቼ ስንጎበኝም ሆነ የዚች አገር ተወላጅ ጓደኞቼ በመካከላቸው የሚያደርጉትን ቅጥ ያጣ የፍጆታና ያገልግሎት መለዋወጥ ስመለከት የዚያች አገር ባህል እንዴት እንደተበላሸ ተግንዝቤያለሁ፡፡

ሙስና የተስፋፋባቸውን አገሮች በጥልቀት ስንመለከት የሚከተሉትን የጋራ ጠባያት የሚጋሩ ሆነው እናገኛቸዋለን። አብዛኛዎቹ 1) ሕዝባቸው በድህነት አረንቋ የሚዳክር መሆኑ፤ 2) አገዛዛቸው ሶሻሊስትና የሶሻሊስት ፍልስፍና አራማጆች መሆናቸው፤ 3) አስተዳደራቸው ኢዴሞክራሲዊ የሆኑ፤ 4) በኤኮኖሚ መስክም አገሮቹ ህዝቦቻቸው በነፃ ከቦታ ወደ ቦታ ንግድ ለማካሄድ እቀባ የተደረገባቸው፤ 5) ከውጭ አገሮች ጋር ብዙም የነፃ ንግድ ልውውጥን የማያደርጉ፤ 6) ባለስልጣኖቻቸው በሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ ምርጫ ያልተመረጡ፤ 6) ባለስልጣኖቹ ወይም ረዳቶቻቸው በራሳቸውም ሆነ በህዝባቸው ላይ እምነት የሌላቸው፤ 7) ለሥልጣን የተበቃባቸው መንገዶች ጉልበትና ጠብ- መንጃ የሆኑባቸው፤ 7) መሪ ተብዬዎቻቸው በኋላ ቀር አስተሳሰብ፤ በአምባገነንነት፤ በቡድናዊነት፤ በእብሪተኝነትና በተንኮል የተጠመዱ መሆናቸው፤ እንዲሁም 8) አገራዊ አንድነት ሳይሆን ክፍፍል ዓይነተኛ ባህሪያቸው የሆኑ፤ 9) ሙስናቸውን ለመሸፈን ሕብረእሰባዊ ድርጅቶችን በእጃቸውና በፓርቲያቸው መዳፍ ዉስጥ የሚያስገቡና ነጻ የሆኑትንም መፈናፈኛ የሚያሳጡ፤ ናቸው።

ሙስና ከሚያጠቃቸው አገሮች አንዳንዶቹም እንደነዳጅ ዘይትና ወርቅ የመሳሰሉ ውድ የተፈጥሮ ህብቶች ያሏቸው ናቸው። እነዚህን የመሳሰሉ ውድ ነገር ግን በብዛት የሚገኙ ሃብቶች የሃገር ጌጥ እንደመሆን ፋንታ፤ ባለስልጣኖችን ለሙስና ዳርገው ህዝብን ለመከራ ስላበቁ እንደሃገር መከበሪያ ከመቆጠር ይልቅ “የሀብት እርግማኖች” የሚል ስያሜ አትርፈዋል። ይህን ክፉ አጋጣሚ የማይጋሩት ኖርዌይና ቦትስዋና ብቻ ሲሆኑ አንጻራዊ በሆነ አባባል እነዚህ ሁለት አገሮች ሃብታቸውን በተገቢው እየተጠቀሙበት ነው ማለት ይቻላል።

ተከታዩ ክፍል ሳምንት ይቀጥላል፡፡
ምንጭ