የብርትኳን ሚደቅሳን መፈታት ተከትሎ በኢትዮጵያ ከቀጠለው አፈና ላይ ትኩረት እንዳይነሳ ጥሪዎች ቀረቡ
የአንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ብርትኳን ሚደቅሳ ረቡእ ጠዋት ከቃሊቲ እስር ቤት መውጣቷን ተከትሎ በተለያዩ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የሚወጡ መግለጫዎች እና ጽሁፎች በአገሪቱ ከቀጠለው አፈና ላይ ትኩረት እንዳይነሳ ሲያሳስቡ ቆይተዋል።
መግለጫውን ያወጣው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት “ሂውማን ራይትስ ዋች”፥ “…የብርትኳን መፈታት ትርጉም እንዲኖረው [አገዛዙ] ህገወጥ በሆነ መንገድ ያሰራቸውን ሌሎች በርካታ እስረኞች ሊፈታ ይገባል” ብሏል። በኢትዮጵያ ያሉ እስር ቤቶች በሙሉ በገለልተኛ አለማቀፍ ድርጅቶች የሚጎበኙ ባለመሆናቸው ስንት የፖለቲካ እስረኞች በአገሪቱ እንዳሉ መገመት እንደማይቻል፤ ይህም ሆኖ ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በህገ-ወጥ መንገድ ታስረው፣ አንዳንዴም ለሰቆቃ እንደሚጋለጡ ድርጅቱ ገልጿል።
የሂውማን ራይትስ ዋች ተመራማሪ የሆኑት ሌስሊ ሌፍኮ፥ “የብርትኳን መፈታት በኢትዮጵያ ያለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ የከፋ ደረጃ ላይ የመኖሩን ሃቅ አይለውጠውም” ብለዋል።
“አድቮካሲ ፎር ኢትዮጵያ” የተባለው ድርጅት በበኩሉ በዚሁ ቀን በለቀቀው መግለጫ፤ ብርትኳን ከ21 ወራት እስራት በኋላ የተፈታችበት ይህ ቀን ለሁላችንም የደስታ ቀን ነው ካለ በኋላ፤ “ነገር ግን መቼም ቢሆን መጀመሪያውኑ የታሰረችበትን ምክንያት ልንረሳ አይገባም። ያ ምክንያት ደግሞ የነፃነት፣ የዴሞክራሲ እና የህግ የበላይነት አለመኖር ነው፤” ብሏል።
“የጋራ እንቅስቃሴ ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ” የተባለው ድርጅት፤ “ብርትኳን አሁንም ቢሆን ነፃ አይደለችም” በሚል ርእስ ሐሙስ እለት በለቀቀው መግለጫ፦ ብርትኳን ቃሊቲ ከሚገኝ ትንሽ ክፍል ወጥታ የኢትዮጵያ ህዝብ ለሃያ አመታት ያህል በዘውግ አፓርታይድ ስርአት ታስሮበት ወዳለው ተለቅ ያለ እስር ቤት ገብታለች ብሏል።
ከሌሎች ድርጅቶችም ተመሳሳይ መግለጫዎች የወጡ ሲሆን፥ አቶ ይልማ በቀለ የተባሉ ጸሃፊ፥ “የወያኔን አገዛዝ አናመሰግንም” ብለዋል። ታዋቂው የአሜሪካን አገር ጋዜጣ “ታይም”፥ “የብርትኳን ሚደቅሳ መፈታት ለይስሙላ ነው ወይ?” በሚል ርእስ ባወጣው ጽሁፍ፤ የወያኔ አገዛዝ ላለፉት በርካታ አመታት ሲያካሄድ የቆየው አፈና በብርትኳን መፈታት ላይ ጥያቄ ሳያነሱ ማለፍን አስቸጋሪ አድርጎታል ብሏል።