የብርቱካን ሚደቅሳ የ”ይቅርታ” ደብዳቤ በመለስ ዜናዊ መረቀቁ ተጋለጠ

የአንድነት ለፍትህ እና ለዴሞክራሲ ሊቀመንበር ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ከቃሊቲ ለመውጣት አቀረበች የተባለውን የይቅርታ ደብዳቤ ዘረኛው አምባነን መለስ ዜናዊ እራሱ እንዳረቀቀው ለሂደቱ ቅርብ የሆኑ ግለሰብ አጋልጠዋል።

ባለፈው ሳምንት በወያኔ ቁጥጥር ስር በሚገኘው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) አማካኝነት ይፋ የሆነው ደብዳቤ በመለስ ዜናዊ መጻፉ የብዙሃኑ ጥርጣሬ ሆኖ ሰንብቷል። በተለይም ወ/ት ብርቱካን በውጭ አገራት ጫና ላይ ተማምና ጥፋት ማጥፋቷን የሚገልጸው ክፍል በመለስ ዜናዊ በተደጋጋሚ የተባለ ነጥብ መሆኑ በበርካቶች ዘንድ እንደ ማስረጃ ሲጠቀስ ቆይቷል።

ወ/ት ብርቱካንን ከእስር ለማስፈታት በተደረጉት የሽምግልና ሂደቶች ውስጥ ተሳታፊ ከነበሩት አሸማጋዮች መሃል አንዱ ከግንቦት 7 ንቅናቄ አመራር አባል ጋር ባደረጉት የመልክት ልውውጥ፣ የይቅርታ ረቂቁን መለስ ዜናዊ እራሱ አርቅቆ ከሽማግሌዎቹ መሃል ለአንዱ እንደሰጠ አሳውቀዋል።

የዝግጅት ክፍላችን የአመራር አባሉን አነጋግሮ እንደተረዳው፥ ዘረኛው አምባገነን ረቂቁን በገዛ እጁ ጽፎ ለሽማግሌው የሰጠው ከበርካታ ወራት በፊት ነበር። “ይቺ ሴት ከእስር ወጥታ ልጇን ለማየት ከፈለገች ያለምንም ማወላወል በረቂቁ ውስጥ በሚገኙት የይቅርታ ነጥቦች ላይ መስማማት እና መስማማቷንም በፊርማዋና በቃሏ ባደባባይ ማረጋገጥ ይኖርባታል። ይህን ለማድረግ ካልፈቀደች “እስር ቤት እንደምትበሰብስ ንገሯት”” የሚል ማስጠንቀቂያ ማያያዙንም የደረሰን መረጃ ገልጿል።

በወቅቱ ጉዳዩ ሌሎቹ ሽማግሌዎች ጋር በደረሰበት ወቅት የተወሰነ ውዝግብ አስነስቶ እንደነበር የዜናው ምንጭ የጠቀሱ ሲሆን፤ በመጨረሻ ግን አማራጭ ያጣው ቡድን የመለስን ረቂቅ ጽሁፍ ከነማስፈራሪያው ይዞ ወደ ብርቱካን ለመሄድ መገደዱን ገልጸዋል።

የመልክቱን ምንጭ ተአማኒነት በሚመለከት ጥያቄ የቀረበላቸው የንቅናቄው አመራር አባል፤ ምንጩ በአንድ ወቅት በሽምግልናው ሂደት ተሳታፊ ከነበር የቅርብ ወዳጃቸው ያገኙትና መቶ በመቶ እንደሚያምኑት አስረግጠዋል። መለስ ዜናዊ እስከዚህ ደረጃ የወረደ ስራ የሚሰራበትስ ምክንያት ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱም፦ “ግለሰቡ አያቱ የጣሊያን አሽከር ሆነው በማገልገላቸው ከልጅነቱ ጀምሮ “የባንዳ ልጅ” እየተባለ ያደገና በዚህም ምክንያት ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ ብቻ ሳይሆን፣ ለህዝቦቿ ሰብአዊና ባህላዊ እሴቶች ከፍተኛ ጥላቻ ያለው ሰው ነው። ይህ ሰው ኢትዮጵያዊ የሆነን ነገር ሁሉ ለማራከሰ ያለው ጠንካራ ፍላጎት ይሉኝታን ከውስጡ ደምስሶ በየጊዜው ለቅሌታም ድርጊት አጋልጦታል። ዝም ብለን ካየነውም በሃገርና በወገን ላይ የሚያስከትለው ውርደት ገደብ አይኖረውም” ብለውናል።