የሰላማዊና ህጋዊ ትግል ብዥታ የጠራበት ክስተት

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከአስከፊዉ የወያኔ እስር ቤት በመፈታቷ የተሰማውን ደስታ በእለቱ ገልጿል። በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችም የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፤ እየገለፁም ነው። ወያኔ ሊያዋርዳት የሞከራትን ጀግና ህዝብ በቄጠማና በቀይ ምንጣፍ ተቀበላት፤ ይገባታልም።

ከወ/ት ብርቱካን መፈታት ጋርም ሰላማዊና ህጋዊ ትግል በኢትዮጵያ የጊዜው ተጨባጭ ሁኔታ ቦታ የሌለው ስለመሆኑ የነበረ አነስተኛ ብዥታም ጨርሶ ተገፏል።

ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሁለገብ ትግልን የትግል ስትራቴጂው አድርጎ የመረጠበት ዋነኛው ምክንያት እየተፋለመው ያለው እኩይ ኃይል ሰላማዊም ሆነ ህጋዊ ትግልን የማያውቅ መሆኑን በመረዳቱ ነው። ሰላማዊ ትግል ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ተፎካካሪው ባላንጣ ቢያንስ:-

  • ሀ) እራሱ ላወጣቸው ህጎች ከበሬታ ያለው፤
  • ለ) ለማዕበራዊ የሞራል እሴቶች (ለምሳሌ ይሉኝታ) ግድ ያለው ሲሆን፤ እና
  • ሐ) ያቋቋማቸው ተቋማት ከአምባገነኑ የዘፈቀደ ትዕዛዝ ነፃ ሲሆኑ ነው።

እነዚህ ሁኔታዎች በተሟሉበት የነፃነት ታጋዮች አስቀድሞ የታወቀን የቅጣት መጠን ለመቀበል ተዘጋጅተው ህግን በመጣስ ተቃሞዓቸውን ይገልፃሉ። በህጉ የተመለከተውን የቀናትም ይሁን የሳምንታት እስርም ይሁን ሌላ ቅጣት ተቀብለው ይወጣሉ። እንደገና ህጉን ሆነ ይጥሳሉ፤ በድጋሚም ታስረውም ይወጣሉ። አንፃራዊ ነፃነት አላቸውና ፓሊስ ታሳሪውን አያሰቃይም፤ አቃብያነ ህግ ታጋዮችን ባልሰሩት ወንጀል አይከሱም፤ ዳኞችም በህግና በማስረጃዎች ብቻ ተሞርኩዘው ይፈርዳሉ። በዚህ ታስሮ የመፈታት ትግል ተሳታፊ እየበዛ ከመጣ አገዛዙ መሠረታዊ ለውጦችን ለማድረግ ሊገደድ ይችላል። ይህ እንግዲህ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል ይሉኝታ ያለው፤ ተቋማቱም አንፃራዊ ነፃነት ያላቸው እና አምባነኑም ቢያንስ የራሱን ህጎች የሚያከብር ሲሆን ነው። እንደዚህም ሆኖ ግን ትግሉ ሰላማዊ ይሁን እንጂ የአምባገነኑን ህጎች መጋፋት እንዳለበት ልብ ይሏል።

ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ባልተሟሉበት የሚደረግ ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ግን የነፃነት ታጋዮችን ለአካላዊም እና ስነልቦናዊ እርድ እንደማቅረብ ይቆጠራል።

በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ዳግም እስር እና ዳግም የይቅርታ ማመልከቻ የተረጋገጠው ሃቅ ይህ ነው። ወ/ት ብርቱካን በእስር ላይ የቆየችበት ጊዜ ከባድ እንደነበር፤ በተለይም የመጀመሪያዎቹ 200 ቀናት መራር እንደነበሩ ገልፃለች። በእነዚህ ጊዜዓት የደረሰባትን ሰቆቃ ከዚህ በላይ ባትነግረንም ይገባናል።

ብርቱካን እንትድፈርም የተሰጣት ወረቀት ደራሲ መለስ ዜናዊ ሲሆን ተደራሲ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው። መለስ የራሱን የእብሪት ድርሰት በብርቱካን ማስነበቡ ሳያንስ የይቅርታ ወረቀቱ ከመፈረሙ በፊት የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ እንድታደርግ ይዘቱን ጭምር ወስኖ አዘዘ፤ “በሽማግሌዎች” አማካይነት ትዕዛዙ ተፈጸመ።

ስለሆነም ብርቱካን ፃፈችው ከተባለው ማመልከቻና ከሰጠችው ቃለመጠይቅ አንዱም ቃል የእርሷ አይደለም። ሁሉም የመለስ ዜናዊ ቃላት ናቸው። ደብዳቤው የተፃፈው ከብርቱካን ለመለስ ዜናዊ ሳይሆን ከመለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም “ሰላማዊ ትግል ገና መቸ ተጀመረ?” ሲሉ ለነበሩ ወገኖቻችን ነው።

የደብዳቤው እውነተኛ መልዕክት ባጭሩ የሚከተለው ነው።

“እኔና ቤተዘመዶቼ በሥልጣን ላይ እስካለን ድረስ ማንኛውን ኢትዮጵያዊ ነፃነትን በሰላማዊና ህጋዊ ትግል አገኛለሁ ብሎ ተስፋ አያድርግ። እኛ ይኸ እንዲሆን ፈጽሞ አንፈቅድም። ያላችሁ ምርጫ ተረግጦና ተዋርዶ መገዛት ብቻ ነው።”

ለዚህ ትዕቢት ምላሻችንስ ምንድነው? ዛሬም የሰላማዊና ህጋዊ ትግል ብዥታ ውስጥ ያለ የምር ታጋይ አለን? ከዚህ በላይ እንደምን ተደርጎ ሊነገረን ይቻላል?

በግንቦት 7: የፍትህ፣ የዲሞክራሲና የነፃነት ንቅናቄ እምነት አገራችንን ከባዕድ ወራሪዎች በባሰ ጭካኔ እየገዛ ካለው የትግራይ ገዥ ጉጅሌ ጋር ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ማድረግ ታጋዮችን ለባሰ አደጋ ማጋለጥ ነው። አሁን በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሁለገብ ትግል ከሰላማዊ ትግል ባነሰ ወጪና ህመም እግባችን የሚያደርሰን ስትራቴጂ እንደሆነ የብርቱካን ዳግም እስር እና ዳግም ይቅርታ ተጨማሪ ማስረጃዎች ነው።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!