የፍቅር ሐዋርያው ቴዎድሮስ ካሣሁን በፍቅር ይበልጣል

ቃላት እየከዱኝ እንዴት እንደምጅምር ተቸገርኩ፡፡ አንዳንዴ ደስታ ያደርጉትን ያሳጣል፡፡ በተለይማ ደስታና ተስፋ በጠፉበት የጨለማ ዘመን ውስጥ አልፎ አልፎ እንደብርቅ የሚታዩ የሃሤት ምንጮች ሲገኙ በደስታ ብዛት ጮቤ ያስረግጣሉ፡፡ ቴዲ አፍሮ ያደረገውን ስሰማ ጆሮየን ማመን አቃተኝ፡፡ በዚህ ዘመን እንዲህ ዓይነት ፍቅር – (Agape, Platonic love,) ሊኖር ስለመቻሉ ጥርጣሬ ስለነበረኝ የአለማመን ስሜቴ አየለብኝ፡፡ ነገር ግን ልጁ – ይህ በኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያ በፍቅር የሚቃጠል ብላቴና ለእምነቱ ሲል የሆነውን ሁሉ ስለማስታውስና ስለማውቅም ማመን ነበረብኝ፡፡ ዘሩ ይባረክ፤ የፍቅር በረከቱ ለኛ ለዘግቶ በሎቹም ይድረሰን፡፡ ይህን የአንድነትና የሰላም ፈርጥ፣ ይህን የመተዛዘንና የፍቅር ሐዋርያ፣ ይህን ጠፍተንም ቢሆን እንዳልጠፋን እንዲሰማን እያደረገ ያለ የቀደምት ኢትዮጵያውያን ተምሣሌት ዕንቁ ልጃችንን ፈጣሪ ይጠብቅልን፤ ለደጉ ዘመንም ያድርስልን፡፡ ቸሩ አምላክ ለዚህ ብላቴና ሩህሩህና ቅን አሳቢ፣ ቸርና ለጋስ ልቦና እንደሰጠው ሁሉ በዚህ ረገድ ብዙ ለሚጠበቅብን ግን ከእርሱም በላይ የገንዘብ ሀብታሞች ለሆንን ንፉግና ራስ ወዳድ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ልቦና ሰጥቶን ከአንድ ግለሰብ በበለጠ ለሚሊዮኖች ለሚደርስ ሱታፌ በረከት እንድንታደልና ስማችን በታሪክ የወርቅ ቀለም እንዲጻፍ ያብቃን፡፡ በእውነቱ በሀገራዊ ጉዳይ በ20 ዓመታት ውስጥ እንዲህ ተደስቼ አላውቅም፡፡

የቴዲ አፍሮን(የተለመደ ስሙ ነው) ሰሞነኛና በጊነስ የድንቃ ድንቅ ክስተቶች መመዝገቢያ መጽሐፍ ሊመዘገብ የሚገባው ዜና ያልሰማ አይኖርም ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ ዜና የወጣው በትናንትናው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው፡፡ ላልሰማችሁ ጉዳዩ ባጭሩ እንዲህ ነው፡፡

ፑንትላንድ በምትባለው የሶማሊያ ግዛት ውስጥ አንድ የዐድዋ ልጅ (ሰሜን ኢትዮጵያዊ) ከሚስቱና ከልጁ ጋር ይኖር ነበር፡፡ በዘረፋ የሚተዳደሩ ሶማሌያውያን የዚህን ልጅ ሀብት ለመዝረፍና ባለቤቱን ለመድፈር በሌሊት ይመጣሉ፡፡ ባልሞት ባይ ተጋዳይነት ልጁና ጓደኞቹ ራሳቸውን ሲከላከሉ የልጁ ሕጻን ልጅና ከሌቦቹ ወገን ደግሞ አንድ ይሞታሉ፤ ዘራፊዎቹና የልጁ ጓደኞች ሲሰወሩ ልጁ ይያዛል፤ ሚስቱም እስካሁን የደረሰችበት አልታወቀም ተብሏል፡፡ ከአንድ ዓመት እሥራት በኋላ የሶማሊያ የጎሣ ጉባኤ ተቀምጦ ባስተላለፈው ፍርደ ገምድል ፍርድ ይህ ኢትዮጵያዊ በሞት እንዲቀጣ ይበየናል፤(ራሱን ከሌቦች በመከላከሉ)፡፡ (ሊያሸልመው በሚገባ ራስን ከዘራፊ የመከላለከል ተፈጥሯዊ ድርጊት የሞት ቅጣት ተበየነበት – የሚገርም ሕዝብ ከሚገርም የፍትሕ ሥርዓት ጋር – ሶማሊያ፡፡ ለዚህ ሁሉ ተዋራጅነት የዳረገን ባንዳውና የኢሣይያስ አፈጥንቢ ተላላኪ ለገሠ ዜናዊ ጥቁር ውሻ (ደጋግሞ) ይውለድ!) በአማራጭ የተላለፈው ተለዋጭ ብያኔ ደግሞ ሞቱ እንዲቀርለት ከፈለገ የ40 ሺህ ዶላር ካሣ እንዲከፍል ይወስኑበታል፡፡ (እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ዓይነት ከመጀመሪያው ያልተሻለ ጭፍን ብያኔ፡፡ ፈጣሪ በዚች ሀገር ላይም ተጨማሪ ግን ፍትሃዊና ሚዛናዊ ፍርዱን ይስጥ) የሞት ፍርደኛው እህት ጉዳዩን እየተከታተለች ነበር፡፡ የወያኔው መንግሥት ከዚህችው እንደፈሳች ዝንጀሮ ከዓለም ተለይታ ከምትኖር የሶማሊያ ግዛት ጋር ጥሩ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አለው እየተባለ ግና ተጨባጭ የሆነ ነገር ሊያደርግ አልቻለም ወይም አልፈለገም ፤ ለዚያውም ልጁ ዘረኛውና አምባገነኑ ኢትዮጵያዊው ጋዳፊ-መለስ በተወለደባት በኢትዮጵያዊቷ ሥርጥ- ዐድዋ ከተማ ላይ የተወለደ መሆኑ ተዘግቦ፡፡ እህቱ ምርጫዋ ሲጠብ በግል ሚዲያ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቿ ታሳውቃለች፡፡ ወዲያውም በሰጠችው የድረሱልኝ አድራሻ አንድ የስልክ ጥሪ ይደርሳታል፡፡ ስሙን አልገለጸላትም፡፡ በተስማሙበት የመገናኛ ሥፍራ በሰዓቱ ይደርሳሉ፡፡ ሰላምታ ይለዋወጣሉ፡፡ ያ ሰው የቀጠራት እንደትናንት ነው፤ የተገናኙት ደግሞ እንደዛሬ፡፡ ስለዚህ ይህ ሰው ሊያደርግ የፈለገውን በጤናማ አእምሮ አስቦበትና ከልቦናው ጋር በደንብ መክሮበት እንጂ በድንገትና በስሜታዊ የደም ፍላት ወይም በስካርና በመሳሰለው ሊሆን እንደማይችል ማንም የሚረዳው ነው – ልብ በሉ፡፡ ያ ሰው አንድ ነገር ይሰጣታል፡፡ ያም ነገር ቼክ ነው፡፡ ያ ቼክ ሲነበብ 700 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይላል – ልድገመው መሰለኝ – ሰባት መቶ ሺህ የኢትዮጵያ ብር፡፡ የዚያ ቼክ ጌታ ደግሞ ቴዎድሮስ ካሣሁን ነው፡፡ ከሕዝብ አገኘ፤ በፈቃዱ ለሕዝብ ሰጠ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ይህ የመጀመሪያው ነው፤ ወደፊትም ሪከርዱን እንደያዘ እንደሚኖር አምናለሁ፡፡

ይህን የምለው ከብዙ አቅጣጫ ነው፡፡ ዐውቃለሁ እነሼህ አላሙዲን ከዚህ በላይ እንዳደረጉና እንደሚያደርጉ፡፡ መታየት ያለበት ግን እነሱ ‹ደግ ሥራ› የሚሠሬት መቼ ነው? ምን ለማግኘት? የነሱ የገንዘብ መጠንና የቴዲ ምንና ምን ነው? አዎ፣ ብዙ መናገር ይቻላል፡፡ አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ባልቴት ከመቀነቷ የቋጠረችውን ሣንቲም አውጥታ በክርስቶስ ሙዳየ ምፅዋት አስገባች፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ግን ስጦታዋን ናቁባትና ተሳለቁባት፡፡ ክርስቶስም አለ፤ ‹ሀብታሞች ካላቸው ሰጡ፤ ይህች ሴት ግን ያላትን ሰጠች!›፡፡ ቴዲ የሰጠው ገንዘብ ትንሽ ነው እያልኩ እንዳልሆነ አመዛዛኝ አእምሮ ያለው ሁሉ ይረዳኛል፡፡ እያልኩ ያለሁት ሌሎች ለጉራና ለፕሮፓጋንዳ ሊያውም በፕሮፓጋንዳው አዋጭነትና መንግሥታዊ ተቀባይነት ላይ በተመሠረተ ሁኔታ ካላቸው እየቆነጠሩ፣ በተለያዬ መንገድ ከሕዝብ ከዘረፉት እየዘገኑ ይሰጣሉ፤ በዚያውም ሊያገኙት የማይችሉትን ሕዝባዊ ፍቅርና አመኔታ ሊያገኙ ይቋምጣሉ፡፡ ይህ ልጅ ግን ከዚያች ካለችው ጥቂት ነገር መንፈሱ ለመራው ግን ለሁላችንም ትምህርት ለሚሰጥ ነገር ገንዘቡን አዋለ፤ ለኔ እንደ ኢንቬስትመንት ልቆጥረው እፈልጋለሁ፡፡ ገቢ የሚያስገኘው በገንዘብ መልክ ሳይሆን በዓይነት ነው – ከሰማይም ከምድርም ለሚገኝ የፍቅር በረከት ገንዘቡን በፍቅር አወጣ፡፡ እኔ ብሆን ለስም ስል ሶማሊያ ድረስ ሄጄ አንዲት በሞት ፍርድ ስቃይ የምትቃትትን ነፍስ እስከማውጣት የሚደርስ የብፅዓት ሥራ አልሠራም፡፡ ብዙ ሳላወጣ በጥቂቱ እዚሁ ማድረግ እችላለሁ፡፡ ይህ የቴዲ ድርጊት ግን ሁላችንንም ለማስተማር ከላይ የታዘዘ መሆን አለበትና ልብ ልንለው ይገባል፡፡

ስንቶች በየምሽት ክበቡና በየዝጉብኚው እየጨፈሩ በመቶና በሺዎች የሚቆጠር ዶላርና ብር ሲመነዝሩ በእሳት መሰል ይሁንታዊ ነዲድም ሲያቃጥሉ ያድራሉ፤ ስንቶች አንዴ ለተኙዋት ሴት መኪናና ቤት ሳይቀር እየገዙ ቀበቶኣቸውን ያስፈታቻቸውን ሴት በየጊዜው ጎጆ ያወጣሉ፤ ስንቶች ላይኖሩበት ሕንጻና ቤት ይቆልላሉ፤ ስንቶች ላይበሉት በሚሊዮንና በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ በሀገርና በውጭ ባንኮች በራሳቸውና በዘመዶቻቸው ስም ያከማቻሉ፤ ስንቶች ከሕዘብና ከመንግሥት በሚመዘብሩት ገንዘብ ይሠሩትን አጥተው በገንዘብ ብዛት ናላቸው ተቃውሶኣል… በዚህ መሃል አንድ ወጣት ተገኘና ተዓምር ሠራ፡፡ የርሱ አይደለም – የፈጣሪ ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ቴዲ በሠራውና በሚሠራው መልካም ነገር ሁሉ አይታበይም፡፡ አንዴውን የልጅ ዐዋቂ አድርጎ ፈጥሮታልና በዚሁ ይቀጥል፡፡ እኛም በመንፈስ እንቅናበት እንጂ እንደዮሴፍ ወንድሞች በሥጋዊ ስሜት አይሁን፡፡ ጀግናና የፍቅር ሰው መውለድ እንደምንችል ሁሉ ማሳደግና ለቁም ነገር ማብቃትንም እንማር፡፡ የሰውን በጎ በጎ ምግባር እየለዬን ማድነቅንም እንልመድ፡፡ ከከንቱ ነቀፋና ከበሬ ወለድ የቅዋሜ ምንጭ ራሳችንን እናግልል፡፡ ከሁሉ ከሁሉም ‹የቄሣርን ለቄሣር፣ የእግዜርን ለእግዜር› በማደላደል ምሥጋና ለሚገባቸው ምሥጋናን፣ ወቀሣና ግሣጼ ለሚባቸውም ያንኑ ዋጋ ከመስጠት አንቆጠብ፡፡ ወኃ በማያነሱ የመተቻቻ መነሾዎች ግን የሰውን ቅስም ለመስበር ከመነሣት እንታቀብ – ብዙ ተጉዘንበት ያላዋጣን በመሆኑ፡፡ የቴዲን አርአያ ለመከተል እንትጋ፡፡ በሚሠራው እንውደደው፡፡ እንምሰለው፡፡ በክፉ ዐይን ግን አንየው፡፡ አንድ ዐይና ባፈር አይጫወትምና!