በሊቀመንበራችን መፈታት ስንደሰት ቀጣዩን ትግል አምርረን ለመታገል ለራሳችን ቃል በመግባት ነው!!
አንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማሕበር
በቅድሚያ ለአለፉት 20 ወራት በእስር ስንትገላታ የከረመችው መሪያችን ወይዘሪት ብቱካን ሚዴቅሳ ከእስር ተፈታ ከቤተሰቦቿና ከደጋፊዎቿ ስለተቀላቀለች የተሰማንን ከፍተኛ ደስታ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ አዛውንት እናቷን ሕጻን ልጅዋን ቤተሰቦቿንና መላው የአንድነት ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎቿን እንኳዋን ደስ አላችሁ እንላለን፡፡
ላለፉት 20 ወራት በተለይ በብርቱካንና በቤተሰቦቿ ላይ የደረሰው ጭካኔ ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ጭካኔው አስከፊ እንደነበረ ይህንንም ከራስዋ አንደበት አረጋግጠነዋል። በተለይም የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት አቶ መለስ የመሪያችን ወይዘሪት ብርቱካንን ቅስም ለመስበር የተጠቀመበት የጠባብ ጭለማ ቤት ውስጥ ግዞት (dark solitary confinement) ማንነቱን በግልጽና በሰፊው ለስረአቱ ደጋፊዎች ሳይቀር ያጋለጠበት ክስረቱ ነበር፡፡ ወደፊትም በታሪክ ከሚጠቀሱ አስከፊ የፖለቲካ በደሎች እንደ አንዱ ሲጠቀስ ይኖራል። ባንጻሩ መሪያችን ወይዘሪት ብርቱካን በአቶ መለስ የፍርድ ጭካኔ የማትሸማቀቅና ከአላማዋም ፍንክች ያማትል መሆንዋን እንኳን የሚወዳት የኢትዮጲያ ህዝብ ይቅርና የዚህ ስራአት ደጋፊዎችም ተረድተውታል::
በተለይም የአቶ መለስ የፍትህ ሚንስቴር ተብዬ በፍርድ ቤት የወሰነውን የቤተሰቦችንና የወዳጅ አዝማዶን የመጎብኘት መብት እንኳን ማስፈጸም ሳይቻለው ቀርቶ ሲንገዳገድ ማየት የፍትህንም ሆነ የውሳኔው ስልጣን በአቶ መለስ ዜናዊ እጅ ብቻ እንደሆነ በግልጽ ያየንበት አጋጣሚም እንደነበረ ልናስታውስ እንወዳለን። ይህ ታዲያ ብርቱካን ብቻ ሳትሆን መላው ሕዝባችን በዘቀጠ የፍትሕ ስረአት ውስጥ እንዳለ ሌላው ማስረጃ በመሆኑ ለፍትህና ለዲሞክራሲ የምናደረገውን ትግል አምርረን እንድንታገል ያደርገናል።
አቶ መለስ በየግዜው የተነሱትን ተቃዋሚ ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ የድርጅት መሪዎች፣ የሲቪክ መሕበራት መሪዎች ለመርገጥና ለማዋረድ ያደረገው አፀያፊ ድርጊቶች የምናውቃቸውና የቅርብ ግዜ ትዝታዎቻችን ናቸው፡፡ በወይዘሪት ብርቱካን ላይ ያደረገው የተለያ እንዳልሆነ ለመገንዘብ የግድ የፖለቲካ ምሁር መሆን አያስፈልገውም፡፡ ከዚህ በፊት ላደረገው የስም ማጥፋትና የሰው ልጅን ሰብአዊነት የማጥፋት ዘመቻ ሕዝባችን በምን መልክ እንዳስተናገደው ስለምናውቀው አሁንም በወይዘሪት ብርቱካን ላይ የሚያደርገውን የዘቀጠ ፕሮፖጋንዳ ለመስማት ለጥቂትም ደቂቃ እንኳን ጆሮ እንደማይሰጠው ሊያውቀው ይገባል፡፡
የሰሜን አሜሪካ የአንድነት የድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ማሕበር ለእንደዚህ አይነቱ ድርጊት ሰለባ ማነው ባለተራ በማለት የምንጠብቅ ሳንሆን ይልቁንስ ለሕዝባቸው መብት በመነሳታችው ብቻ ወደ እስርቤት የተወረወሩትን ወንድምና እሕቶቻችን ነፃነታቸውን እስኪያገኙ ድረስ ትግላችንን ማጠናከር እንደሚገባን ተገንዝበናል፡፡ በመሆኑም የወየዘሪት ብርቱካን ክእስር ተፈተው ወደ ትግል መመለስ የኢትዮጲያን ትንሳኤ የሚያቃርበው በመሆኑ ማህበራችን ይህ አስከፊ ስረአት እስኪወገድ ድረስ ለሊቀመንበራችንና ለፓሪቲያችን የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንደምንቀጥል ቃልኪዳናችንን በማደስ ቆርጠን እንደተነሳን ሳንገልጽ አናልፍም፡፡
በመጨረሻም መሪያችን ወይዘሪት ብርቱካን በእስር በቆየችበት ወቅት እሷን ለማሰፈታት ያላሰለሰ ጥረት ላደረጋችሁ እንዲሁም በገንዘብና በቁሳቁስ ቤተሰቧንና የብርትኳን ትፈታ ግብረ ህይልን ለረዳችህ በሙሉ ልባዊ ምስጋናችንን እያቀረብን፡፡ በዚህ አጋጣሚም የብርቱኳን ትፈታ ግብረ ሃይል አመራርና አባላት ለሰሩት ታሪካዊ ስራ ማሕበራችን ከፍተኛ ልባዊ ምስጋና ያቀርባል።
አንድነት ሰሜን አሜሪካ የድጋፍ ድርጅቶች ማሕበር