ኢትዮጵያ ሶማሊያን በመዉረር አልሼባብን አጠናክራለች ሲሉ አንድ ብሪታኒያዊ ተመራማሪ ገለጹ
በብሪታኒያ ጥልቅ የፖለቲካ የምክክር መድረክ የሆነዉ ቻታም ሃዉስ የአፍሪቃ ፕሮግራም አማካሪና ተመራማሪ ሮጀር ሚድልተን ኢትዮጵያ ሶማሊያን በመዉረር አልሼባብን አጠናክራለች ሲሉ ገለጹ። ተመራማሪው ይህንን የገለፁት ባለፉት አምስት ቀናት ዉስጥ የኬንያ ወታደሮች በሶማሊያ ዉስጥ ጣልቃ መግባታቸዉን በማስመልከት በሰነዘሩት አስተያየት ነዉ።
ሮጀር ሚድልተን ይህን መሰል ያልታሰበበትና አሉታዊ የሆነ ጣልቃ ገብነት የሚያስከትለዉን ዉጤት ካለፈዉ የኢትዮጵያ ወረራ ያለመማር ስህተት እንደሆን በመግለፅ ፣ በ2006 የተደረገዉ የኢትዮጵያ ወረራ የብዙዎች ጥምረት የነበረዉንና ህዝብ የተቀበለዉን የእስልምና ፍርድ ቤቶች ምክር ቤትን በማፍረስ ብቻዉን የቆመ፤ ብዙ አካባቢዎችን የተቆጣጠረ አክራሪ ሃይል የሆነዉን አልሸባብን የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ በዩናይትድ ስቴትስ መንግስትና በኢህ አዴግ መራሹ የወያኔ አገዛዝ በ2006 በሶማሊያ ዉስጥ የተደረጉት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶች በጠቅላላዉ በአካባቢዉ የነበረዉን ሁኔታ ከማሻሻል ይልቅ ለእራሳቸዉም አገር ሆነ ለሶማሊያ ህዝብ ይበልጥ መጥፎ ችግርችን የፈጠሩ መሆናቸዉን ሮጀር ሚድልተን መግለፃቸዉን ኦል አፍሪካን ኒዉስ አመልክቷል።
የዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ቁንጮ መለስ ዜናዊ በራሱ ውሳኔ በሶማሊያ ላይ ወረራ እንዲፈጸም ሲያደርግ እጅግ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ምሁራን፣ በወቅቱ በነበረው ፓርላማ መቀመጫ የነበራቸው ተቃዋሚ ፓርቲ ተመራጮችና ሰፊው ህዝባችን ድርጊቱን በጥብቅ አውግዘው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን በወያኔ ጣልቃገብነት የተቆጣው የሱማሊያ ህዝብ ሆ ብሎ በመውጣት ወያኔ ያሰማራውን የኢትዮጵያ ጦር እንደወጋና የሞቱትን ዜጎች አስከሬን ጎዳና ለጎዳና በመጎተት ነዳጅ እያርከፈከፈ ሲያቃጥል በርካታ የአለም ዜና አውታሮች በምስል በተደገፈ ዘገባ ሲዘግቡት እንደነበር ይታወቃል።