በሃዲያ ዞን የሚገኙ የሶስት ወረዳ ህዝቦች ለጥያቄአቸው ምላሽ ካላገኙ አመጽ እንደሚያስነሱ መግለጻቸው ታወቀ

ኢትዮጵያን በዘርና አሃይማኖት ከፋፍሉ የመግዛት አባዜ የተጠናወተው የወያኔ አገዛዝ የከፋፋይነት መርዙን በሃገሪቱ ከረጨ ወዲህ በበርካታ የኢትዮጵያ ክልሎች ግጭቶች እየተከሰቱ ሲሆን ላለፉት 13 ዓመታት “እኛ ሃላባዎች እንጂ ሃድያዎች አይደለንም፤” በሚል የማንነት ጥያቄ ሲያነሱ የቆዩ ናቸው የተባሉ በሃዲያ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሦስት ወረዳዎች፣ ጥያቄያቸው ምላሽ በማጣቱ ወደ ግጭት በማምራት ላይ መሆናቸው ታወቀ።

ቁጥራቸው አሥር የሚደርሱ በሃዲያ ዞን ምሥራቅ ባዳዋቾ ወረዳ የአንደኛ ቄራንሶ፣ የሁለተኛ ቄራንሶና የገገራ ቀበሌ ነዋሪዎች ተወካይ ሽማግሌዎች ለዘረኛው አገዛዝ ቅርበት እንዳለው ለሚታወቀው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ለ13 ዓመታት የማንነት ጥይቄያቸውን ለወረዳው፣ ለዞኑ እንዲሁም ለደቡብ ክልል ከዚያም አልፎ ተርፎ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢያቀርቡም ምላሽ ከማጣታቸውም ባሻገር ወደ ግጭት እያመሩ ነው፡፡

ባህላቸው፣ ታሪካቸውና ቋንቋቸው የሃላባ መሆኑን የሚናገሩት እነዚሁ ሽማግሌዎች፣ “እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የምንማረው፣ የምንዳኘው እንዲሁም ማንኛውንም ማኀበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነታችንን የምናደርገው በምንም መልኩ መናገር፣ መስማትና ማንበብ በማንችለው የሃዲይኛ ቋንቋ ነው፤” በማለት እየተናገሩ እንደሆነ ታውቁአል።

ጥር 20 ቀን 2000 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለክልሉ መንግሥት የላከው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ የሦስቱ ቀበሌ ነዋሪዎች በሃዲያ ዞን የምሥራቅ ወረዳ አመራር አባላት ለጥያቄያቸው ምላሽ ከመስጠት ይልቅ በተወካዮቻቸው ላይ ድብደባና አፈና እያደረሱባቸው መሆኑን፣ ከዚህም ለማምለጥ አካባቢውን ለቅቀው በስደት እንደሚገኙና የማንነት ጥያቄውን ባቀረቡ ተወካዮች ቤተሰቦች ላይ እስራት እንደሚፈጸምባቸው ተወካዮቹ በአቤቱታቸው ማቅረባቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

የማንነት ጥያቄ መነሳት ከጀመረበት ከ13 ዓመታት ወዲህ በብሔረሰቡ ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ ከልክ በላይ መሆኑን የሚናገሩት ተወካዮቹ፣ ዞኑ ለችግሩ መፍትሔ ከማቅረብ ይልቅ ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር እየበደላቸው መሆኑን መግለጻቸው ታውቁአል፡፡ የማንነት ጥያቄ የሚያነሱትን በጅምላ በማሰር፣ በመደብደብና ባልሠሩት ወንጀል በማስፈረድ ተደጋጋሚ እንግልት እንደሚያደርሱባቸው የሚናገሩት ተወካዮቹ፣ በተለይ መስከረም 21 ቀን 2000 ዓ.ም. “ሕገወጥ ስብሰባ አካሂዳችኋል፤” በሚል ወረዳው ባሰማራቸው የፖሊስ ኃይል የደረሰው ጥቃት ችግሩን አስከፊ እንዳደረገው አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ በህዝቦች መካከል ለረጅም ዘመናት አብሮ የቆየው አንድነትና መተሳሰብ እሴት በተለይም የዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የስልጣን ወምበርን ከተቆናጠጠ ወዲህ እየጠፋ፣ የኢትዮጵያ አንድነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እየተዳከመ መምጣቱን በርካታ ምሁራን ሲገልጹ የቆዩ ከመሆኑም በላይ የድህነቱ መባባስና ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የሚከተለው የብሄር ፖለቲካ ለዚህ አስተዋጽኦ ማድረጉም በተደጋጋሚ ስንገልጽ መቆየታችን የሚታወስ ነው።

ይህ በዚህ እንዳለ በዚሁ በደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የሚገኝ የዋካ ከተማና አካባቢ ህዝብ የጀመረው የተቃውሞ አመጽ በተጠናከረ መልኩ የቀጠለ ሲሆን በተለይም ማክሰኞ እለት የተነሳው ተቃውሞ ሌሊቱን በሙሉ አድሮ በማግስቱም ተጠናክሮ መቀጠሉን ከስፍራው ዘጋቢያችን በላከልን መረጃ አመልክቷል።

እንደ ዘጋቢያችን ሪፖርት የአካባቢው እና የክልሉ ፖሊስ ሁኔታውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው በ7 መኪና የተጫኑ የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም የዘረኛው አገዛዝ የክልሉና የፌደራል ባለስልጣናትም በአካባቢው መገኘታቸው ታውቁአል። ከዚሁ የተቃውሞ አመጽ ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ ከ26 ያላነሱ ሰዎች ተይዘው መታሰራቸውንና 4 ግለሰቦች ደግሞ ክፉኛ ተደብድበው መታሰራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

እንደዘጋቢያችን ሪፖርት ከተሳሩት መካከል አቶ አድነው ማሞ፣ ተፈራ ታደሰ ፣ ምትኩ በቀለ፣ ከበደ ኮኑ፣ ግርማ ጌታቸው ፣ ካሰች ተገኝ፣ አብነት አግደው፣ዘነበ ገርገራ፣ ጥረቱ ሀይሌ እንደሚገኙበት የታወቀ ሲሆን ከተለያዩ ቀበሌዎች እየተመመ ወደ ከተማው የጎረፈው ህዝብ የታሰሩት ተወካዮቻችን ካልተፈቱ በስተቀር ተቃውሞአችንን እንቀጥላለን ማለቱን ዘጋቢያችን ያነጋገራቸው የአካባቢው ተወላጆች ገልጸዋል።

በሌላም በኩል ከዚሁ ህዝባዊ አመጽ ጋር በተያያዘ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች ማህበራዊ አግልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በሙሉ የተዘጉ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም  ” ዳውሮ ላይ የመንግስት ስርአት የለም፣ ልማት የለም፣ እስራትና ድብደባ ይቁም፣ የሚሉ መፈክሮችንና “ነጻነት አጣን እኛ የዋካ ልጆች፣ ስርአቱ ገደለን የዋካን ልጆች” የሚል ይዘት ያለው መዝሙር ሲዘምሩ መሰማታቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ዘግቡአል።