“የምክር ቤት አባልነቴ፤ በቴሌቪዥን ቢሆንልኝ ይሻል ነበር” ሲሉ የኢትዮጵያው አሻንጉሊት ፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪል መናገራቸው ተዘገበ

ሰሞኑን አምባገነኑ መለስ ለአሻንጉሊቱ የኢትዮጵያ ፓርላማ ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ፤ ከወትሮው በተለየ መልኩ በዘረኛው መለስ አስተያዬት ዙሪያ ሀሳባቸውን ለመስጠት እንዳልተፈቀደላቸው መጥቀሳቸውን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት ዘገበ።

“ይህ ነገር መታረም ካልቻለ  ምናልባትም ለምክር ቤቱ ጥያቄዎቻችንን አስገብተን መለስ መልስ እንዲሰጥና እኛም ሂደቱን በቴሌቪዥን ብንከታተል የሚሻል ይመስለኛል” ያሉት አቶ ግርማ፤ “የምክር ቤት አባል መሆኔ ትርጉም የሚኖረው፤በተሰጡት አስተያዬቶች ላይ ሀሳቤን በማንጸባረቅ ስችል ይመስለኛል”ማለታቸውን ተያይዞ የወጣው ዘገባ አመልክቱአል።

እንደ ኢሳት ዘገባ  አቶ ግርማ አክለው በተደጋጋሚ አምባገነኑ መለስ በተሳሳተ የመነሻ ምክንያት ተንደርድሮ ያሻውን ዓይነት ድምዳሜ ላይ ሲደርስ ‘ሃይ!’ ለማለት እንኳን አልተቻለም።‘የለም! አንተ ያልከውና እኛ የገባን ይለያያል’ ለማለት እንኳ፤ እድሉን አላገኘንም።  ሁኔታው እጅግ አሳፋሪ ነው። የም/ቤት አባልነቴ በቴሌቪዥን ቢሆንልኝ ይሻል ነበር’ ሲሉ መናገራቸው ተገልጹአል።

“ፋሽስቱ መለስ በጋዜጠኞች ላይ የሰነዘራቸውን ትችቶች እንዴት ይመለከቱታል?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ግርማ መለስ ከተሳሳተ መነሻ-ምክንያት ተነስቶ ወደ አደገኛ ድምዳሜ የሚሄድበትን አግባብ የሚያሳይ ሌላኛው ጉዳይ ነው” ያሉ ሲሆን  “ መለስን ያበሳጨው፤ ፍ/ቤት በጉዳዩ ላይ ብያኔ ከመስጠቱ በፊት ‹የግል ጋዜጠኞች ተከሳሾቹን ነፃ ናቸው ይላሉ› የሚለው ነው” ያሉት ብቸኛው የተቃዋሚ ዕጩ፤ ሰዎች በፍ/ቤት ወንጀለኞች መሆናቸው ተረጋግጦ ወንጀለኛ እስከሚባሉ ጊዜ ድረስ ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠ ከመሆኑ አንፃር፤ ይሄ አባባል በሕግ ፅንሰ-ሃሳብም ሆነ ተግባራዊ አሰራር የሚደገፍ እንጂ የሚያበሳጭ  እንዳልሆነ አስረድተዋል።

አያይዘውም በተቃራኒው ግን የወያኔው አገዛዝ ጋዜጠኞች የነዚህ ሰዎች ጉዳይ በፍ/ቤት ሳይረጋገጥ ወንጀለኛ ናቸው ሲሉ ይፈርጇቸዋል። ስለዚህ ‹ጋጠ-ወጥ› መባል ያለባቸው የአገዛዙ ጋዜጠኞች እያሉ፤ ሰዎችን ነፃ ብለው የሚያስቡትን ‹ጋጠ-ወጥ› ማለት ግን ተገቢ አይመስለኝም”ብለዋል። ዘረኛው መለስ ፍርድ ቤት ገና ጥፋተኛታቸውን ሳያረገግጥባቸው ሰዎች “ነፃ ናቸው” ብለው   እየፃፉ ነው ያሏቸውን ጋዜጠኞች “ጋጠ-ወጥ” ካሏቸው፤  በዚያው መድረክ ላይ  ፦”የታሰሩት ወንጀለኞች ናቸው።  አንድም ሰው ያለ ማስረጃ አልታሰረም። ለሁሉም በቂ ማስረጃ አለ” እያለ ዳኛ ሆኖ ፍርድ ሲሰጥና ተፅዕኖ ሲፈጥር የነበረው ራሱ መለስ ምን ይሆን የሚባለው? በማለት ታዛቢዎች መጠየቃቸውን ኢሳት ዘግቡአል።