የፋሽስቱ መለስ ዜናዊ ውድቀት እንደሊቢያው ሙአመር ጋዳፊ እንዳይሆን ስጋት መኖሩን የህዝብ አስተያየት አመለከተ

ተቃዋሚዎቻቸውን አንዴ ሽብርተኞች ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሃሺሺ የደነዘዙ አይጦች በማለት ሲያጣጥሉ የነበሩትን የሙአመር ጋዳፊ የውርደት አሟሟት የተመለከቱ በርካታ ኢዮጵያዊያን የመለስ ዜናዊ የመጨረሻ እጣ ፋንታ ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል በስፋት እየተነበዩ መሆኑን በአዲስ አበባና አጎራባች ከተሞች የሚኖሩትን የህዝብ አስተያየት ያሰባሰቡ የግንቦት 7 ዘጋቢዎች ለዝግጅት ክፍላችን በላኩት ዜና ገለጹ።

ሙአመር ጋዳፊ በዙሪያቸው ያደራጁትን የመከላኪያ ሠራዊት ብዛትና ጥንካሬ በመተማመን በተቃዋሚዎቻቸው ላይ ሲሰነዝሩ የኖሩት ንቀትና ጥላቻ መለስ ዜናዊ ወደሥልጣን ከመጣ ጊዜ ጀምሮ ከሚያሳየው ይመሳሰላል ያሉት አሰተያየት ሰጪዎች ፤የሊቢያው ጦር ሙአመር ጋዳፊና ልጆቻቸው የተጎነጩትን አይነት ውርደት ሊያስቀር እንዳልቻሉ ሁሉ መለስ ዜናዊ የተመካበት ሠራዊት ፊቱን ወደ ህዝብ ዞር ያደረገ ቀን ፍጻሜው ተመሳሳይ እንደሚሆን ፍጹም አንጠራጠርም ይላሉ።

ዘጋቢዎቻችን ካሰባሰባቸው የህዝብ አስተያየቶች አንዱ የሆኑት የደቡብ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፤ በሰጡት አስተያየት እንደተናገሩት፣ ምንም እንኳን በአለም ላይ ያሉ አምባገነኖች ካንድ ውሃ የተቀዱ ቢመስሉንምና አንደኛው ከሌላው መማር አለመቻሉ አዲስ ነገር ባይሆንም፣ አሁን በሙአመር ጋዳፊ ላይ የደረሰው ውድቀትና የሊቢያዊያንም እልህ አስጨራሽ ትግል በተለይም ለአምባገነኑ መለስ ዜናዊና በዙሪያው ለተሰባሰቡ የህወሃት ቁንጮዎች ምናልባት የመጨረሻ እድል ሊሆን ይችል ይሆናል ብለው እንደሚያስቡ ገልጸዋል።

በጉልበትና ወታደራዊ ሃይል አጥብቆ መመካት፣ እንዲሁም በዘመድ አዝማድ ላይ የተመሰረተ የስልጣን ክፍፍል መጨረሻው ምን ሊሆን እንደሚችል ሰሞኑን በሊቢያ ያየነው ክስተት ግልጽ ትምህርት ይሰጣል ያሉት እኒሁ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁር እነመለስ ዜናዊ ይህን ክስተት ቆም ብለው ሊያስተውሉና ሳይጨልምባቸውም ማስተካከል የሚገባቸውን ሁሉ ቢያስተካክሉ ይሻላቸዋል ብለዋል። በመጨረሻም፣ በተለያዩ አፋኝ ዘዴዎችና የጭካኔ ርምጃዎች ህዝብን ረግጦ ለረጂም አመታት መግዛት ያለፈበት የቁማር ጨዋታ በመሆኑ ራሳቸውን የማስተካከያ ጊዜው ካለፈ በሁአላ ሊከተል የሚችለው ውድቀት እንዲህ በቀላሉ መግለጽ የሚቻል አይደለም፣ እናም ለሁላችንም የሚበጀውን ነገር ነገ ዛሬ ሳይሉ  ማስተካከያ ያብጁለት ዘንድ እመክራቸዋለሁ በማለት አስተያየታቸውን አጠቃለዋል።

ሙአመር ጋዳፍ የተቃዋሞዎቻቸው  እየተጠናከሩ መምጣት ተመልከተው እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከእንዲዚህ አይነት የውረደት ሞት የማዳን ሰፊ እድል የነበራቸው ቢሆንም በታሪክ ተደጋግሞ ከታየው የአምባገነኖች ፍጻሜ እጅግ ዝቅ ባለ ውርደት አይጦች በሚርመሰመሱበት የቆሻሻ ማስተላለፊያ ቱቡ ውስጥ እስከመደበቅ ደርሰው የፍጻመውን ሞት የሞቱ መሆናቸው ብዙዎችን አስገርሞአል።

መለስ ዜናዊና ግብረአበሮቹ እንደ ሊቢያው መሪ ህዝብ ሳያስጨርሱ መጨረሻቸውን ለማሳመር ያላቸው ጊዜና ተስፋ ከ እጃቸው እያመለጠ መሆኑን የግንቦት 7 ንቅናቄ ደጋግሞ እየገለጸ ይገኛል።