ግንቦት 7 በአውሮጳ ከሚገኙ የየአገራቱ አመራር አባላት ጋር ያካሄደው የሁለት ቀን ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ መፈጸሙ ተገለጸ
በአውሮፓ ከሚገኙ 11 አገሮች የተወጣጡ የግንቦት 7 የአህጉርና የአገራት ተወካዩች ባለፈው ቅዳሜና እሁድ እንደፈረንጆች አቆጣጠር ኦክቶበር 22 እና 23 ከአውሮጳ ዋና ከተማ ከብራስልስ 30 ኪሜትር ርቄት ላይ በሚትገኘው የሉቨን ከተማ ተሰባስበው ንቅናቄያቸው ስለሚያካሄደው ሁለገብ ትግል በሰፊው እንደተወያዩና የአቋም መግለጫም እንዳወጡ የንቅናቄው የህዝብ ግንኙነት ክፍል አስታወቀ።
ከስዊድን፤ ከኖርዌዬ፤ ከዴንማርክ፤ ከፊንላንድ፤ ከሲውዘርላንድ፤ ከኢስፔን፤ ከፈረንሳይ፤ ከጀርመን ከእንግሊዝ፤ ከኒዘርላንድስና ከቤልጅዬም የተውጣጡት እነዚህ ተሰብሳቢዎች፤ በየአገሩ በተዘረጋው የግንቦት 7 ድርጅታዊ መዋቅር ውስጥ በሥራ አመራር ኮሚቴ ተመርጠው ትግሉን እያሰተባበሩ ያሉ መሆናቸው ታውቆአል።
በሰሜን አፍሪካ ውስጥ በተቀሰቀሰው የጸረ አምባገነኖች ትግል የተደናገጠው የመለስ ዜናዊ ፋሽስታዊ አገዛዝ፤ ለሁለት አሥርቴ አመታት በህዝባችንና በአገራችን ላይ እየፈጸመ ያለውን ሰቆቃና ወንጀል ይበልጥ በማጠናከር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስላማዊ ዜጎችን፤ ጋዜጠኞችን፤ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባላቶቹን በሽብርተኝነት ሥም እየፈረጀ፤ እራሱ ከሳሽ እራሱ ዳኛና ምስክር በመሆን ምን ያህል እያሰቃዬ እንደሚገኝ በሰፊው የተወያየው ስብሰባ፤ ንቅናቄያቸው ግንቦት 7 ይህንን የወያኔን እብሪት ለማስቆም በምድር ላይ ምን እየሰራ እንደሆነ በንቅናቄው ሊቀመንበር በዶ|ር ብርሃኑ ነጋ አማካይነት ሰፊ ማብራሪያ እንደተሰጠው ለማወቅ ተችሎአል።
ከድርጅቱ ሊቀመንበር ከዶር ብርሃኑ ነጋ በተጨማሪ የንቅናቄው የተለያየ ዘርፍ ሃላፊዎች ተገኝተው ከአባላቱ ለተነሱት የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን እየተሰራ ነው በተባለው ድርጅታዊ ሥራ እርካታ የተሰማቸው የየአገሩ አመራር አባላት፤ ንቅናቄው በምድር ላይ እያከናወነ ያለውን ሁለገብ ትግል በሚያስፈልገው ሁሉ ለመደገፍ ከምንጊዜውም በላይ ቆርጠው መነሳታቸውንና ወደየመጡበት አገሮች ሲመለሱም በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ዕድል ያላገኙትን መላውን አባላትና ደጋፊዎች በማነቃቃት ለትግሉ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የገንዘብ፤ የማቴሪያልና የእውቀት ድጋፍ እንደሚያስባስቡ በማረጋገጥ ባለ 4 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ስብሰባቸውን እንዳጠናቀቁ ታውቆአል።