የሕወሐት/ኢሕአዴግ ቦንድ ሽያጭ ጥሪ በዳላስ
አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን/ዳላስ ቴክሳስ
በዚህ በያዝነው ሰሞን ከአገርቤት የሚሰማው ሁሉ መልካም ነገር አይደለምና ብዙ ሰው ዳግም ሀዘን ውስጥ ገብቷል። የዚህ ትውልድ ብርቅ ልጆች በመታሰር ላይ ናቸው። አቶ አንዷለም አራጌና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር ሆነው ወደ እስር ዳግም ተወርውረዋል። እነዚህ ለዚህች አገር መልካም አሳቢ፣ ተቆርቋሪ ወጣቶች ይህ የመጀመሪያ ጊዜአቸው አይደለም። ምርጫ 1997 አስታኮ ሕወሐት/ኢሕአዴግ በደነገጠበት ማግስት ለብቀላ ወደ እስር ተጥለው መከራ ካዩት ውስጥ ሁለቱ ወንድሞች ይገኙበታል። ሁለቱም ወጣት በምንለው የእድሜ ክልል ውስጥ ናቸው። በዚህ ጊዜ ደግሞ ወጣትን ማጣት ለዚህች አገርና ለዚያ መከረኛ ሕዝብ እጅግ ጉዳት ነው። ምክንያቱ ግልጽ ነው። ትዝ ይላችሁ ይሆናል ሕወሐት/ኢሕአዴ አገር ሲይዝ ግንባር ቀደም ሆነው የነበሩ፤ መነኩሳት፣የአለም ጉዳይ የበቃቸው ዜጎች ነበሩ። ኮሎኔል መንግስቱ ያነን ጀግና ትውልድ መትሮና የቀሪውን ቅስም ሰብሮ በመሄዱ፤ አገሪቱ የታጋይ ያለህ ብላ የምትጮህበት ወቅት ነበርና ነው። ዛሬም ቢሆን ተመሳሳይ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። እንደነ አንዷለምና እስክንድር አይነቶችን ለማግኘት ሁለት አስረት እንደሚወስድ ጥርጥር የለውምና ነው በየጊዜው በግፈኞች ሲጎተቱብን ጥልቅ ሀዘን ውስጥ የምንወድቀው።
ነገርን ነገር ያነሳል እንዲሉ ከላይ የዘረዘርሁት የመግቢያ ሀሳቤ ዛሬ ዋነኛው ሳይሆን ተያያዥ ነውና በዚህ እንዳለን አዲስ የጦርነት ቀጠና ወያኔ/ኢሕአዴግ መክፈቱን በማስመልከት ነበር ይህችን መጣጥፍ እንዳቀርብ የተገፋሁ።
ሞገደኛው የመለስ መንግስት ሙባረክ ከ32 አመት ስልጣኑ በሕዝብ ተወርውሮ ወደፍርድ ቤት በሬሳ አልጋው ሲቀርብ ሲያይ፤ የሕዳሴ አባይ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፈተብንና፣ በመላው አለም ካድሬወቹን አሰልፎ ወረረን። “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም” ይላል ያገራችን ሰው። በመለስ ጠባብ መንግስት እምነት ሕዳሴው በእውነት የታመነበት ሆኖ ሳይሆን የሕዝብ ቀልብን ከሰሜን አፍሪካ ወኔን እንዳይገዛ ወደሕዳሴው ማስቀየሩ ነበር። ምናልባት የዚያ ዘመቻ ትቂት ወገኖችን ሊያሞኝ ችሎ እንደሆን ባላውቅም። ጭንቀት የፈጠረው መሰሪ መላ መሆኑን ግን ድፍት ጦቢያ ያወቀው ጉዳይ ነው። የመለስ ካድሬወችን ግን አቃሎ መመልከት አይገባም። እንደሚባለው በተለይ ወደሰሜን አሜሪካ ላለፉት ሰባት አመታት የላካቸው በእድሜም ቀለል ያሉ የካድሬ ቁጥር ግን በቀላሉ የሚታይና የሚገመት አይደለም። በእኔ እና በአንድ ወዳጀ የደረሰው በዚያን የህዳሴው ታቡር በሚደቃበት ሰሞን አስይቶኛል። የአንድ ወንድሜ ባለቤት መርዶ ይደርሳትና ወደዚያ እሄዳለሁ። ከሀዘኑ ቤት ከወዳጀ ጋር ተያይዘን ስንገባ የጦፈ የጎን ክርክር ላይ ደረስን። ለጊዜው እኔን ግር ስላለኝ አልፍ ብየ ከአንድ ወጣት ጎን ተቀመጥሁ። ለካ የውይይቱ እምብርት እሱ ኖሮ፤ ሰሞነኛውን ሕዳሴ አባይ መልካምነትና ሊያመጣ የሚችለውን አገራዊ ለውጥ ከምሳሌ ጋር ይደረድራል። ታዲያ እንዲያ አይነት ጠበቅ ያለ አስተሳሰብ በዚያ በወጣት አንደበት ይነገራል ብየ አልገምት ኖሯል ደግሜ ደጋግሜ ልጁን ቀና እያልሁ ተመለከትሁት። ባለፈው ሰሞን ዲያቆን ዳነኤል የተባሉ “በታሪክ ላይ መተኛት” በሚል እርእስ እዚህ ውጭ ያለውን ዜጋ ጠብ እርግፍ አርገው እንደሰደቡ አስታወሰኝና ልጁን እረ ተው ለማለት ሞከርሁ። እሱ ግን የሚመለስ አልነበረምና የሰሜን አሜሪካ ነዋሪ ኢትዮጵያውያንን ጾታ፣ ወይንም እድሜ፣ ወይንም ማንነትና ምንነት ሳይለይ በጅምላ ተሳድቦ ሳይጨርስ ብሔድ ይሻላል ብየ ከወዳጀ ጋር ወጣን።
ዘመቻ ቦንድ በዳላስ
ሰሞኑን የፈረደበት የዳላስ ነዋሪ ሌላ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ቅስቀሳ ተጧጡፎበታል። ግቡ ፖለቲካዊ ቢሆንም፣ ለጊዜው የተተኮረው ለፍተው ደክመው በባእድ አገር ትንሽ ጥሪት የቋጠሩ ወገኖችን፣ስለፖለቲካና አገር ብዙም ዜና የሌላቸውን ንጹሐን ገንዘብ ለመሰብሰብ የተዘየደ መላ ነው። “ያም ሲያማ ለኔ ብለህ ስማ” ይሏልና። ይህ በዳላስ የሚጀመረው ሁለተኛ ዙር የሕዳሴ ቦንድ ሽያጭ፤ በዚሁ የሚቆም እንዳልሆነ ሁሉም በውጭ የሚኖር ዜጋ ሊገነዘበው፣ ብሎም ሊዘጋጅበት ይገባልና፤ የዚህች አጭር ጽሁፍ አላማም ይህንን ለማመላከት ሲሆን። በቴክሳስ የሚኖር ወገኖች በተለየም ሒውስተንና ኦስተን ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ነቅተው እንዲጠብቁ ነው።
እንደተባለው አዲሱ የዩኤስ አሜሪካ የሕወሐት/ኢሓዴግ ወኪል ሆነው የተሾሙት አቶ ግርማ ብሩ ይኸውን ቦንድ ለመሸጥ በሚል ሳቢያ፣ ግና ለመጀመሪያ የተላኩበትን የፖለቲካ አላማ ፍተሻ በኖቨምበር 12/2011 ቀን ወደ ዳላስ እንደሚመጡ ተረድተናል። እንግዲህ የዘመቻ ቦንድ በዳላስ በዚህ ቀን ይጀምራል ማለት ነው። እኛም ቴክሳሶች እንዘጋጃለን ማለት ነው።
አንዳንድ ወገኖች ይህን ተቃውሞ ጽሁፍ ስናወጣ የልማትና እድገት ተቀናቃኝ አድርገው ሊመለከቱት ይችላሉ። ይህም የወያኔ/ኢሕአዴግ ካድሬወች ቅስቀሳ ሲጨመርበት መልኩን ሊቀይር እንደሚችል ሳንገምት አልቀረንም። በጥብቅ የምናሳስበው ማንም አገሩ ብትለማ፣ እህት ወንድሞቹ፣ እናት አባቶቹ መላ ዘመድ አዝማዱ ከድህነት፣ ከእረሀብና ስራ አጥነት ቢላቀቅ የሚጠላም፣ የሚቃወምም ይኖራል ብሎ መገመት እንዴት ይቻላል? ይህ ማለት በውጭው አለም ተበትነን የምንኖር ኢትዮጵያውያን ለፍተን ደክመን ቤተሰቦቻችንን ክፉ ቀን እንዲወጡ የምንረዳ ነንና፤ አገር ሲጠግብ ተጠቃሚ፣ አገር ሲራብ ተጎጅወች መሆናችን ሊዘነጋ አይገባም። የዚህ መልእክት አላማና የተቃውሟችን መሰረትም የተሰበረ ፖሊሲ አይሰራም ይለወጥ፣ አገር ይጎዳል። የግልና የቡድንን ስልጣን ለማስቀጠል ተብሎ ያልተጸና፣ ያልተመረመረና፣ በሕዝብ ተመክሮ ያልታመነበት ፖሊሲ ተግባራዊ ለማድረግ አይሞከር። ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝንና ጉዳቱ ደግሞ በዚያ መከረኛ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ይወድቃል በማለት ነው። ሌላም ጥያቄ እንዲቀርብ እንገፋፋለን። ለምን ዛሬ? በጎን ሕዝብን እያመሱ፣ እያሰሩና መብቱን እየነፈጉ፣ ልማት እንዴት ይቻላል? ብሎ መጠየቅ የሁላችንም ሊሆን ይገባል። ይህ መንግስት አገር የበደሉ፣ አንድ ትውልድ የመተሩ ሲፈታ። ለአገርና ለወገን ለመታደግ የሚያልሙ ወጣትና መንታላ ዜጎችን ወደ እስር እየወረወረ ነው። ለዘመናት የታገሉ፤ አለአገር ወገን ብለው የተንገላቱ ዜጎችን ዛሬም ዳብዛቸውን እንዳጠፋቸው ነው። በእኛ እምነት ይህ ሕዳሴ ተብሎ የሚዘመርለት በአምስት አመት እቅዱ ላይ ያልሰፈረና ሙባረክ ሲወድቅ በድንገት የታሰበና ለገበያ ፍጆታ የዋለው ፕሮፓጋንዳ ነው። በሰሞኑ ደግሞ የጋዳፊ እሬሳ በመሬት ሲጎተት ባኖ ሌላ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መክፈት፤ ንጹሐን ዜጎችን ማሰርና ማንገላታት መፍትሔ ነው ብለን አናምንም። የልቁንም ለግል ውስጣዊ ሰላምና ለቀሪ ታሪክ፣ የባሕር በር ሰጦ ወደብ አልባ ያረጓትን የ80 ሚሊዮኖች አገር ይቅርታ ጠይቆ ስልጣንን በሕዝብ ለሚመረጥ መንግስት ማስረከብ ነው። ይህን የህዳሴ ፕሮፓጋንዳ በሶስት አበይት ጉዳዮች እንቃወማለን። እንሱም ፖለቲካዊ ችግሩ። የሚያስከትለው የኢኮኖሚ እዳና ማህበራዊ ጉዳዩን በመመልከት ነው።
በኢኮኖሚያዊ ችግሩ ለግንዛቤ ይሆን ዘንድ ከዚህ በፊት የተገደቡትን ለአብነት ለማሳየት ያክል። የተከዜ፤ የጊቤ ግድቦች አለማቀፍ ትብብር የተደረገላቸው እንደነበሩ የሚዘነጋ አይደለም። በሕዝብና የመለስን አንባገነናዊ መንግስት በሚቃወሙ ድርጅቶችም ሆነ ዜጎች በነዚህ ግድቦች ላይ ምንም አይነት ተቃርኖ አልደረሰም። ሆኖም ግድቦቹ አልቀው በስራ ከታዩ በኋላ ይህ መንግስት አገር ለማልማት ሳይሆን አለማቀፍ የገንዘብ ተዋጸኦን ወደግል ንብረትነት ለመለወጥ የተደረጉ እንደነበሩ ለመረዳት ተችሏል። የተባበሩት መንግስታት የእድገት ፕሮግራም እንደዘገበው ከታዳጊ አገሮች በተለየም በአንባ ገነን መንግስታት ስር ከሚተዳደሩ የሚወጣው የስርቆት ገንዘብ በአንደጉ አገሮች ባንኮች እንደሚቀመጥ የ ሜይ 2011 ሪፖርቱ ይጠቅሳል። በዚህ ሪፖርት መሰረት ለአለፉት 20 አመታት ከኢትዮጵያ አውሮፓና አሜሪካ ባንኮች $8.3 ቢሊዮን መግባቱን ጠቅሷል። ይህ ገንዘብ ከነጋዴወች ካዝና የወጣ አይደለም። በብድር ወይንም በእርዳታ የሚላከው ተመልሶ ወደመጣበት ባንክ ይገባል ማለት ነው። ወደዋና ጉዳያችን ስንመለስ፤ ለምሳሌ በሳሊኒ የጣሊያን ኩባንያ የእርካሽ ኮንትራት በመውሰድ የተሰሩት ግድቦች ሁሉም የታሰበላቸውን ሙሉ አገልግሎት እየሰጡ ነው ወይ ብሎ መጠየቅ የሁሉም ዜጋ መብት ነው። የግልገል ጊቤ ፕሮጀክት $1.7 ቢሊዮን የወጣበት በአመት $407 ሚሊዮን በኤሌክትሪክ ሽያጭ ያስገኛል ተብሎ የተገመተ የፕሮጀክት ስራ ተመርቆ በተከፈት በሁለት ሳምንት የደረሰበትን አደጋ ታዝበናል (May, 2009 international rivers)። በተመሳሳይ የተከዜ ግድብ የታሰበለትን 300 ሜጋ ዋት ሐይል እየሰጠ ሳይሆን በአሸዋ ደለል መሞላቱ በአሁኑ ሰአት 150 ሜጋ ዋት ሐይል ብቻ እየሰጠ መሆኑን ተረድተናል። በዚህ ተመን የታሰበለትን የግልጋሎት ግብ አልመታም ማለት ነው። የልቁንም ወጭውን ለመሸፈን ሊወስድ የሚችለው የግዜ ገደብ ከግምት መግባትም ሊኖርበት በተገባ። እንግዲህ እነዚህ በአለማቀፍ ድጋፍና በደሐ ሕዝብ ንብረት የተሰሩ አገር ሊጠቅሙ የሚገባቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶች በአልባሌ ጉዳት ሲደርስባቸው እያየን ለሌላ ያውም ያለማቀፍ ይሁንታ የተነፈገውና ሰፊ ጽናት፣ የሁሉም ዜጎች ትብብር የሚፈልግ ፕሮጀክት በጀርባ ተጸንቶ ባንድ ሳምንት ጀንበር ለሕዝብ ፍጆታ ሲቀርብ እንዴት ሊሆን ይችላል ማለታችን የዜግነት ግዴታ መሆኑን ማንም ሊገነዘብልን ይገባል። ይህን የሕዳሴ አባይን ትልቅ ፕሮጀክት ኮንትራት የወሰደው ያው የግልገል ጊቤን ፕሮጀክት የሰራው ሳሊኒ የተባለ ኩባንያ መሆኑን ተረድተናል።
አቶ መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ የህዳሴ ዜና ይዘው ብቅ ያሉት ድንገት የሰሜን አፍሪካ አብዮት አይደፈሬወችን ፈንግሎ መሄዱን ባዩበት ማግስት ነው። መለስና ግበረአበሮች ቀደም ብለው የአምስት አመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የባቡር ሐዲድን የመሰለ ከባድ እቅዶችን ሲያሰፍሩ ይህን ሕዳሴ ያሉትን የት ወስደውት ነበር? በማለት ብዙ ምሁራን ይጠይቃሉ። እኛም ልንጠይቅ መብታችን ነው። በአንድ ቀን 28 ከተሞችን ባዳረሱ አመት ሳይሞላ ዳግም ዛሬም የቦንድ ሽያጭ በሚል ሰበብ የፖለቲካ ስራ ሊሰራ ሲነሳ የመቃወም ግዴታችን ነው። ጉርሻ የሚሸጥበት አገር ተይዞ በምእራብ ከተሞች በከፍተኛ ወጭ ቀስቃሽ ካድሬ ማሰማራት ለሞራል የሚከብድ ተግባርም ነው።
እንደግፋለን የሚሉ ወገኖቻችን በዚህ በዳላስ እያረጉ ያለው የቅስቀሳ ስራ በሚገርም መልኩ እየተካሄደ ነው። ዳላስ ከአምስት አመት በፊት በወጣው ዲያስፖራውን የመከፋፈል ስልት የተጠቃ አካባቢ ሲሆን። በደጋፊነትና በተቃዋሚነት ስር በመሰለፍ የመለስ ካድሬወች ለሦስት አስርት አመታት የተገነቡ የእምነትና የማህረሰብ ተቋማትን ለማጥቃት ችለዋል። ወገን እርስ በእርሱ እንዲናቆር አድርገዋል። ዛሬ ፍትጊያና ተቃርኖው እርስ በእርስ ሆኖ የነሱ ስራ አንድ እርምጃ በማሳደግ፣ ይኸው ከአንድ የቅስቀሳ ወደ ሌላ ስብሰባ እያሸጋገሩ ይገኛል። ለወገን ተቆርቋሪ በሆኑ ወገኖች ላይ የሚካሄደው የስም ማጥፋት ዘመቻ በመንግስት ደጋፊወች ይገፋና ወደ ሰላማዊ ነዋሪ እንዲዳረስ እየሆነ ነው። ዛሬ የሕዝብ ተስፋ ሲጨልም ለአንባ ገነን መንግስት አንፋሽ አጎንባሹ ቁጥር መጨመሩ አስገራሚ ባይሆንም አስተዛዛቢአችን ሆኗል። ዳላሳ ደግሞ ለዚህ ተምሳሌ በመሆን ላይ ነው።
የአቶ ግርማ ብሩን መምጣት አስመልክቶ ከወዲሁ የእራት ምሽት ተካፋይ ለመሆን የ$50.00 ትኬእየተሸጠ ይገኛል። ዝቅተኛው የቦንድ ሽያጭ ዋጋ (መነሻ ማለት ነው) $1000.00 እንደሆነ እየተቀሰቀሰ ነው። ለዚህ በኮሚውኒቲአችን የንግድና መልካም ስራ አላቸው የሚባሉትን በስልክና በገጽ የሕወሐት/ኢሓዴግ ደጋፊወች በመገናኘት የኔ ሽያጭ ይበልጣል በሚል ፉክክር እሬከርድ ለማስመዝገብ በከፍተኛ ዘመቻ ላይ ናቸው። በቆዩት አመታት የሕወሐት/ኢሕአዴግን ደጋፊወች በአንድ የዘር ክልል መመደብ የተለመደ ነበር። ዛሬ እዚህ ዳላስ እንደምንታዘበው፤ይህን ዘረኛ መንግስት አገልጋዮች፤ስብሰባ አዘጋጆች፤ የቅስቀሳው ተዋንያንና ተከራካሪወች ላለፈው መንግስት ያገለገሉና የክልል ቁጥር ከአንድ ውጭ የሆኑት በተለያየ የጥቅም ፍለጋ ተገፋፍተው። ወይንም በተለያዩ መናኛ ምክንያቶች ከባለጊዜው የተጠጉ ግለሰቦች ናቸው። እንዚህ ወገኖቻችን ትናንት ጣሊያኖች አገራችንን ሲወሩ ለማሰልጣን ነው እንዳሉት። እኩልነት በተከበረበት አገር እየኖርን፤ ሕዝብ መሪወቹን በየጊዜው ገምግሞ የሚመርጥበትን ስርአተ አስተዳደር አንረን እየተካፈልን። አንድ አንባገነን ድርጅትና ቡድን ለዘለአለም ይኑሩ ብለው ሲደግፉ ከልብ እናዝናለን። አገርንና ሕዝብን ከሚበድሉ ጋር መሰለፍ። አገርና ሕዝብን አብሮ መበደል ነው እንላለን።