ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሕዝብ መልእክት አስተላለፉ !
መስክረም 26 ቀን 2003 ዓ.ም ከቃሊቲ እሥር ቤት የተፈታችሁ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መልእክታቸዉን ትላንት መስክረም 28 ቀን 2003 ዓ.ም አስተላለፉ።
የመጀመሪያዉን እስር ያስታወሱት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የአሁኑ የሁለተኛዉ በጣም አስቸጋሪና መራራ እንደነበረ ገልጸዋል። «አሁን የነበርኹበት የእሥር ኑሮ በጣም ከባድና አስጨናቂ ነበር ብል ሐሰተኛ አልሆንም። ከመንግስት ይቅርታ ጠይቄ መስክረም 26 ቀን 2003 .ዓም እስከተፈታሁበት ጊዜ ድረስ ከቅርብ ቤተሰቦቼ በስተቀር ከማንም ጋራ ሳልገናኝ የአንድ አመት ከዘጠኝ ወራት ሰቆቃና እንግልት ብቻዬን አሳልፌያለሁ» ይላሉ ወ/ት ብርቱካን።
ከሌሎች እስረኞች በተለየ ሁኔታ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚድቅሳ ከስድት ወራት በላይ በጨለማ ቤት ዉስጥ እንዲቀመጡ መደረጉ፣ ከእሥር ቤቱ ዉጭ ሃኪም እንዳያቸው መከልከሉ፣ ፍርድ ቤት ዉሳኔም ቢያሳልፍ ጠበቃዎቻቸዉን፣ ወዳጆቻቸው እንዳይጎበኟቸዉ መከልከሉ ይታወሳል።
በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የደረሰው ሰቆቃ በተመለከተ አስተያየት የሚሰጡት የስለ ልቦና ጠበብት ገዢዉ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የፈጸመዉ የአለም አቀፍ ሕግን የጣሰ የአካልና የስነ ልቦና ቶርቸር እንደሆነ ይናገራሉ። ፕሮፌሰር አሥራት ሊሞቱ ሲሉ እንደተፈቱት ወ/ት ብርቱካንን በአካልና በአስተሳሰብም ተሰብራ ከጨዋታ ዉጭ እንድትሆነ ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሆነም ያክላሉ።
ወ/ት ብርቱካን በአስቸጋሪዉና ሰቆቃ በበዛበት በእሥር ጊዜዋ እርሷ እንድትፈታ ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩ በአገር ዉስጥና ከአገር ዉጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያዉያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉ የምስጋና መልእክቷን ያስተላለፉ ሲሆን በተለይም የአንድነት ፓርቲ አመራሮችና አባላትን «ለቤተሰቤም ሆነ ለእኔ ትልቅ የሞራል ጽናት ምንጭ ሆናችሁ ለቆያችሁት ለመላዉ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ከፍተኛ ያክብሮት ምስጋናዬን አቀርባለሁ» ሲሉም ምስጋባ አቅርበዋል።
በመጨረሻም « ላለፉት ሃያ አንድ ወራት ከመላዉ ዓለም ተለቼ በእሥር የቆየሁ እንደ መሆኔ መጠን፣ የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታም ሆነ የፓርቲዬን እንቅስቃሴ የሚገኝበትን ደረጃ ለማጤን እና ከዚህ በኋላ የእኔ አስተዋጽኦ ምን ሊሆን እንደሚገባ ለመመልከት የራሴን ጊዜ ለመዉሰድ የወሰንኹ መሆኑን በአክብሮት አስታወቃለኹ» ስትል ለትንች ጊዜ እረፍት እንደሚወስዱም ገልጸዋል።