የመለስ ፕሮፖጋንዳ ሕዝቡ ለብርቱካን ያለዉን ድጋፍ የበለጠ እንዲጨምር እያደረገ ነዉ!
መስከረም 29 ቀን 2003
የወ/ት ብርቱካን ሚድቀሳ ቤት፣ የአንድነት አፕርቲ ጽ/ቤት ከገጠር ሁሉ ሳይቀር ስልክ እየተደወለ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔት እየተጨናነቀ ሲሆን፣ ሕዝቡ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መፈታት የተሰማዉን ደስታ በአንድ በኩል እየገለጸ በሌላ በኩል ግን የአቶ መለስ አገዛዝ፣ በብርቱካን መፈታት ዙሪያ ያቀረበዉ ርካሽ ዘገባ እንዳሳዘነዉና እንዳስቆጣዉ አዲስ አበባ የሚገኙ ዘጋቢዎቻችን ገለጹ። የኢቲቪ ሪፖርት ገዢዉ ፓርቲ ብርቱካንን በመፍታቱ ሊያገኝ የሚችለዉን ትንሽ የምትሆን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ ከማጣቱ በተጨማሪ የበለጠ እንዲጠላ እንዳደረገዉ የደረሰን ዜና አክሎ ይገልጻል።
«እኔም ሆንኩኝ ያነጋገርኳቸዉ ሰዎች ሁሉ የኢቲቪን ዘገባ ስናይ በጣም ነዉ ያዘንነዉ። እንዴት እንደዚያ አይነት አሳፋሪ ዘገባ ያቀርባሉ ? እንዴት እሥር ቤት አስረዉ፣ ቶርቸር አድርገዉ ፣ አሰቃይተዉ የተናገረችዉን ተናገረች ብለዉ ያወራሉ ? » ያሉን አንድ አባት «ይህን በማድረጋቸዉ ለርሷ ያለን ግምት እንዲቀንስ ከሆነ ተሳስተዋል። እንደዉም የበለጠ እንድንወዳትና እንድናከብራት ነዉ ያደረጉን» ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለመጀመሪያ ጊዜ ታስራ ስትፈታ የነበረዉን ያስታወሰች አንዲት ወጣት ደግሞ «አሁን ለሁለተኛ ጊዜ ስትፈታ ፣ በእሥር ቤት ያየችዉ መከራ ከባድ እንደነበረ በጀርመን ሬዲዮ ስሰማ ዉስጤ ገነፈለ። የመጀመሪያዉ ጊዜ ያላለችዉን ነዉ አሁን ያለቸዉ። በጣም አሰቃይተዋታል ማለት ነዉ። ይቅርታ ጠየቅች ብለዉ ማወራታቸዉም ደግሞ ሊያፍሩበት ይገባል። ፕሮፖጋንዳቸዉን ዲስገስት የሚያደርግ ነዉ» ስትል ለወ/ት ብርቱካን ያላትን ክብርና ፍቅር ገልጻለች።
በተገናኘ ዜና የአገር ሽምግሌ ነን ብለዉ በወ/ት ብርቱካን እና በአቶ መለስ መካከል ሲመላለሱ የነበሩት፣ በቅርቡ በመለስ ዜናዊ ፓርላማ ተገኝቶ ንግግር በማድረጉና 99.6% ለተሰረቀዉ ምርጫ በተዘዋዋሪ መንገድ እዉቅና በመስጠቱ ከመቼዉም በላይ የተወደደዉን ያህል እየተጠላ የመጣዉ ሃይሌ ገብረሥላሴ፣ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳእቅና ፓስተር ዳንኤል፣ ሊሰጡት ያሉትን ቃለ መጥይቆች ከመስጠት ተቆጥበዋል። የብርቱካን ጉዳይ የመለስ ጉዳይ አስፈጻሚ እንደሆኑ ተቆጥረዉ በስፋት እንዲነቀፉ እንዳደረጋቸዉ የገለጹልን ዘጋቢዎቻችን፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ያልሰጡት አፍረዉ በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።