አይን ያወጣ የህዝብ ገንዘብ ዝርፊያ በቤተክርስቲያናትም ተስፋፍቶ መቀጠሉ ታወቀ
ደጀሰላም በመባል በሚታወቀው የመረጃ ድረገጽ በወጣ ጽሁፍ ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ የሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን እያገለገሉ ለሚገኙት ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም የ1.8 ሚልዮን ብር ላንድክሩዘር መኪና ሽልማት እንደተበረከተላቸው ገልጿል።
እንደ ዘገባው ከመኪናው ጠቅላላ ወጪ ገሚሱ የተሸፈነው በሀገረ ስብከቱ ከሚገኙት የደብረ መንክራት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ እና ደብረ ምጥማቅ ጻድቃኔ ማርያም ገዳማት ሲሆን የተቀረው ደግሞ ሀገረ ስብከቱ ለመንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ከሚልከው ፈሰስ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ትእዛዝ ወጪ ተደርጎ ነው ሲል ድረገጹ ዘግቧል።
ብፁዕ አቡነ ኤፍሬም ለፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ 18ኛ ዓመት በዓለ ሢመት በተገለጠው ሐውልተ ስምዕ ላይ በመገኘት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አጥቢያ አብያተ ክርስቲያን በውድ እና በግድ በተዋጣ ገንዘብ ለአቡነ ጳውሎስ የተበረከተላቸውን የ3.5 ሚልዮን ብር የ2010 ሞዴል ባለስምንት ሲሊንደር ቶዮታ መኪና ቁልፍ በሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ አስተናባሪነት ለአቡነ ጳውሎስ ሰጥተው እንደነበር አስተያየት ሰጪዎቹ አስታውሰዋል በማለት ድረገጹ ጥቅሷል።
በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ፋንታሁን ሙጬም ሃያ በሚደርሱ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት አስተዳዳሪዎች እና ጸሐፊዎች እንደተዋጣ በተገለጸ 240‚000 ብር የተገዛች ሃችባክ ሞዴል መኪና በፓትርያሪኩ አማካይነት በሽልማት እንደተበረከተላቸው ተሰምቷል ሲል ደጀሰላም ዘግቧል።
ይህን ዝርፊያ አስመልክቶ የግንቦት ሰባት ዘጋቢ ያናገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አስተያየት ሰጪ እንደተናገሩት የወያኔው አገዛዝ በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለው ውድመት ያልነካካው ተቋም አለመኖሩን ገልጸው እስከዛሬ ታፍራና ተከብራ የኖረቺውን ቤተክርስቲያንም በሚያሳዝን ሁኒታ እያራከሳት እንደሚገኝ በማዘን ገልጸዋል።