የግል ዩኒቨርሲቲዎች ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ ታወቀ

በኢትዮጵያ ያሉ የግል ዩኒቨርሲቲዎች በየጊዜው ከወያኔ አገዛዝ በሚደርስባቸው ዛቻ የተነሳ ህልውናቸው በከፍተኛ ስጋት ላይ መውደቁን የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ ባስተላለፈው መረጃ ገልጿል።

ዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በመንግስት ተቋማት ላይ ያለውን ቁጥጥር ማጠናከሩ እና ከነዚህም ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዋነኞቹ እንደሆኑ ይታወቃል። አገዛዙ በብዙ ተቋማት ላይ ያለውን ማነቆ በከፍተኛ ሁኔታ ማጠናከር የጀመረው ከ1997ት የምርጫ ሽንፈቱ በኋላ ቢሆንም፤ በትምህርት ተቋማት ላይ ጣልቃ ገብነት ማድረግ የጀመረው ግን ስልጣን እንደተቆጣጠረ ነው።

በዚህም ምክንያት የመማር ማስተማር ነፃነትን በሚመለከት በዋነኛነት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች የተደረጉ ሲሆን፤ ለብዙ ተማሪዎች መገደል፣ መታሰር እና መሰደድ፤ እንዲሁም ለበርካታ መምህራን መባረር እና መሰደድ ምክንያት እንደሆነም ይታወሳል።

ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የወያኔ አገዛዝ ዜጎችን በማስገደድ ወይም በጉቦ በማባበል አባል በሚያስደርግበት ወቅት፣ ከፍተኛ ትኩረቱን ካኖረባቸው ተቋማት ውስጥ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች ግንባር ቀደም ናቸው። መምህራን አባላት ካልሆኑ ስራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ እና ተማሪዎች ደግሞ ወደፊት ስራ እንደማያገኙ በማስፈራራት የነፃ ሃሳብ ማፍለቂያ እና ማንሸራሸሪያ ሊሆኑ የሚገባቸውን ትምህርት ቤቶች ወደ አንድ ፓርቲ ፖለቲካ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ቀይሯቸዋል።

ትምህርት ቤቶች የሰዎች መገናኛ እና የተለያዩ ሃሳቦች መንሸራሸሪያ እንደመሆናቸው የተቃውሞ መነሻ ጣቢያዎች ሊሆኑ ይችላሉ በሚል የሚሰጋው አፋኝ አገዛዝ፤ የግል ትምህርት ቤቶችንም በቁጥጥሩ ስር ለማዋል ሩጫውን መጀመሩ ታውቋል። አንዳንዶቹ ገቢያቸው ሲጎድል ከስራ ውጪ እንደሚሆኑ በማወቅ ጫናዎችን ማድረግ የጀመረው ወያኔ፤ በተቋማቱ ላይ የተለያዩ ማስፈራሪያ እና ማስጠንቀቂያዎችን ማድረግ መጀመሩንም ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ አመልክቷል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ሲደርሰን እንደምናቀርብ ከወዲሁ ልናሳውቅ እንወዳለን።